አደባባዮቹ
የማን ናቸው?
ዜና ሐተታ
ዋለልኝ
አየለ
በአራቱም
አቅጣጫ እየተዟዟርኩ አየሁት፡፡አደባባዩ
የተሰየመበት ስም አይታይም፡፡ በአንድ የንግድ
ድርጅት ማስታወቂያ ዙሪያውን ተሸፍኗል፡፡
አደባባዩ የዚያ ድርጅት አደባባይ መስሏል፡፡
ልብ ብዬ ሳይ ግን ከላይ በኩል በትንሹ በእንግሊዝኛ
ቋንቋ ‹‹Diaspora
Square›› የሚል
ጽሑፍ አለ፡፡ ጽሑፉ በአገር ውስጥ ቋንቋ
እንኳን አልተጻፈም፡፡ አንድ እንግሊዝኛ
የማያነብ ሰው ይህ አደባባይ ምንድነው ተብሎ
ቢጠየቅ አንብቦ እንኳ ማወቅ አይችልም፡፡
ዋናው ችግር ግን እንግሊዝኛ ማንበብ ለሚችሉትም
ቢሆን የሚታየው የአደባባዩ ስም ሳይሆን የንግድ
ማስታወቂያው ስም ነው፡፡
ወጣት
አሰፋ ተመስገን መገናኛ ‹‹ዳያስፖራ››
አደባባይ ከጁስ ቤቶች አጠገብ አገኘሁት፡፡
አደባባዩ ምን እንደሚባል ስጠይቀው ‹‹ዳያስፖራ››
አደባባይ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ከአሰፋ ጋር
ጭውውታችን በዚህ አላበቃም፡፡ ‹‹ዳያስፖራ
አደባባይ መሆኑን በምን አወቅክ?››
ብዬው
ነበር፡፡ ወጣቱ የአደባባዩን ስም የሚያውቀው
ሲባል ስለሚሰማ ብቻ ነው፡፡ አደባባዩ ላይ
ያለውን ጽሑፍ ሳሳየው እየሳቀ ነበር፡፡
አይቶት አያውቅም፤ የዘፍመሽን ማስታወቂያ
ግን በርቀት ያየው ነበር፡፡ ‹‹ዳያስፖራ
አደባባይ›› ሲባል ስለሚሰማ ግን ዘፍመሽ
አደባባይ ይሆናል ብሎ አላሰበም፡፡ የአደባባዩን
ስም ያወቀው በአካባቢው ስለሚኖርና ሲጠራ
ስለሚሰማ ብቻ ነው፡፡
አንድ
ከአዲስ አበባ ውጭ የመጣ ሰው ይህን አደባባይ
እንደማጣቀሻ መጠቀም አይችልም ማለት ነው፡፡
አጠገቡ ሆኖ ‹‹ዳያስፖራ አደባባይ የሚባለው
የቱ ነው?››
ብሎ
ለመጠየቅ ይገደዳል፡፡ ዳያስፖራ አደባባይ
መሆኑን የሚያመላክት ምንም ነገር የለም፡፡
እንዲያውም ከአዲስ አበባ ውጭ የመጣ ሰው
‹‹ዘፍመሽ አደባባይ›› ሊመስለው ይችላል፡፡
ያ እንደዚያ የተዋበ አደባባይ ማንነቱን አጣ
ማለት ነው፡፡
የዚህ
አይነት ተመሳሳይ ችግር የሚታይበት ሌላም
አደባባይ እንጨምር፡፡ ጎፋ ገብርኤል ያለው
አደባባይ ነው፡፡ የሱ ደግሞ የአንድ ንግድ
ድርጅት ማስታወቂያ ብቻ እንኳን አይደለም፡፡
የብዙ ድርጅቶች ማስታወቂያ ነው የሚታይበት፡፡
ስያሜውን ከማጣቱ በላይ ውበቱንም አጥቷል፡፡
ለዓይን እንኳን የሚረብሽ እይታ ነው የያዘው፡፡
እንግዲህ ይህ አደባባይ ምን ተብሎ ይጠራል?
ደራሲ
አንዱዓለም አባት(የአጸደ
ልጅ)
‹‹የሕሊና
መንገድ›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ አንድ ታሪክ
አስቀምጧል፡፡ ታሪኩ በአጭሩ አባትና ልጅ
እየሄዱ አንድ አደባባይ አጠገብ ይደርሳሉ፡፡
አደባባዩ በአንድ የንግድ ድርጅት ዓርማ
ተሸፍኗል፡፡ ልጁ ስለአደባባዩ ጠየቀ፤ አባትየው
ምን ብሎ እንደሚያስረዳ ግራ ገባው፡፡ የአደባባዩን
ስም የሚያሳይ ምንም ነገር የለም፤ ያለው
የንግድ ድርጅቱ ስምና ዓርማ ነው፡፡
ደራሲ
አንዱዓለም አባት(የአጸደ
ልጅ)
በተለይም
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት
አደባባይ ማለት ለኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ለባለሥልጣናትም
ሆነ ለነዋሪዎች ትልቅ ቦታ ነው፡፡ አደባባይ
አንድን ባለውለታ ከመገናኛ ብዙኃን በላይ
ያስተዋውቃል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ
አይስተዋልም፡፡ አደባባዮች የሚሰየሙት
በዘፈቀደ ነው፤ ለዚያውም የተሰየሙበት ስም
ተደብቆ በንግድ ድርጅት እስከመጠራት እየደረሱ
ናቸው፡፡
በሌላ
በኩል ደግሞ የአንዳንድ አደባባዮች ስያሜ
ለምን እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡ ዳያስፖራ
አደባባይን እንደ ምሳሌ ያነሳል አንዱዓለም፡፡‹‹ዳያስፖራ››
ማለት «አገር
የሌለው»
ማለት
ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አገር የሌላቸው
አይደሉም፡፡ቃሉ በአማርኛ ቢተረጎም የባሰ
አስቸጋሪ ስለሆነ ነው እንግሊዝኛውን የተጠቀሙት፡፡
በውጭ አገር የሚኖሩና አገራቸውን በልማትም
ሆነ በየትኛውም ነገር የሚደግፉትን ለማሰብ
ከሆነ ብዙ አማራጭ መጠሪያ መጠቀም ይቻል
ነበር፡፡
የንግድ
ድርጅቶችን ማስታወቂያ በተመለከተም አንዱዓለም
አስተያየት አለው፡፡ «የንግድ
ድርጅቶቹ የአደባባዩን ዙሪያ ይንከባከቡታል፤
ያጥሩታል፡፡ ይሄ ደግሞ የአደባባዩ አካባቢ
መጸዳጃና የቆሻሻ መጣያ እንዳይሆን ይጠብቀዋል፡፡
ይህን የሚያደርጉት ገንዘባቸውን አፍስሰው
ነው፡፡ በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ይሄ ሲሆን
ግን የድርጅቱ ዓርማና ስም ከአደባባዩ በላይ
መሆን የለበትም፡፡ ጭራሽ አደባባዩ ምን
እንደሆነ እስከሚጠፋ መፍቀድ የለባቸውም»
በአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥናት ከፍተኛ
ባለሙያ የሆኑት መምህር መክብብ ገብረማርያም
እንደሚሉት አንድ አደባባይ ለመሥራት ሲታሰብ
ዋና ዓላማው በዚያ አደባባይ እንዲታሰብ
የተፈለገውን ነገር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ከዚህ
በላይ የንግድ ማስታወቂያ የሚተዋወቅበት
ከሆነ አደባባዩ ምንም ነው ማለት ነው፡፡
አደባባይ በሚመለከተው አካል ተመርጦና በምክር
ቤት ጸድቆ የሚቋቋም ነው፡፡ አደባባይ በግለሰብ
ደረጃ ሊሰራ አይችልም፤ ሀብታም አደባባይ
ማሰራት አይችልም፡፡ ስለዚህ አደባባዩን
ያሰራው አካል የንግድ ማስታወቂያዎቹ የአካባቢው
ስያሜ እስኪሆኑ ድረስ ዝም ማለት አልነበረበትም።
ቁጥጥር ማድረግ ነበረበት፡፡ ስለአደባባዩ
ከሚዘክር ነገር ይልቅ የንግድ ማስታወቂያ
በልጦ ሲታይ የሚመለከተው አካል ማሳወቅ
አለበት፡፡ አደባባይን በማስታወቂያ መሸፈን
በፍፁም መፈቀድ አንደሌለበት ነው መምህር
መክብብ የተናገሩት፡፡
እዚህ
ላይ ግን አንድ ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡
እርግጥ ነው እነዚህ የንግድ ድርጅቶች ራሳቸውን
ቢያስተዋውቁበትም እያጠሩና እየጠበቁ ነው፡፡
ግን አደባባዩን የሰራው አካል ይህን ማድረግ
አይችልም ነበር ማለት ነው?
እነዚህ
የንግድ ድርጅቶች ባይኖሩ አደባባዩ የቆሻሻ
መጣያ ይሆን ነበር ማለት ነው?
የአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ሌላ የሚመለከተው
አካል አያሳስበውም ማለት ነው?
እነዚህ
ጥያቄዎች ይመለሱ ዘንድ ወደሚመለከተው አካል
መሄድ የግድ ነው፡፡ ለመሆኑ የሚመለከተው
አካል ማነው?
እኔም
በመጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አቀናሁ፡፡ አንዱ ወደሌላው
እየመራ ይመለከተዋል የተባለው አካል ላይ
ስደርስ ጉዳዩ እንደማይመለከተው ተነገረኝ፡፡
ይመለከተዋል ወደተባለው የውበት መናፈሻና
ዘላቂ ማረፊያ ልማት ኤጀንሲም አመራሁ፡፡
እዚህም ከአንዱ ክፍል ወደ አንዱ ክፍል
ሲያሸጋግሩኝ ከቆየሁ በኋላ እነርሱም
እንደማይመለከታቸው ነገሩኝ፡፡ በድጋሜ ወደ
ከተማ አስተዳደሩ እንድመለስ ተነገረኝ፡፡
ምልልሴ ሁሉ ከንቱ ልፋት ሆነብኝ። ታዲያ
የእነዚህ አደባባዮች ባለቤት ማነው?
ስል
እራሴን ጠየኩ።
No comments:
Post a Comment