ጋዜጣ
የሠራት ቻይና
ጽጌረዳ
ጫንያለው
ባለፈው
ሳምንት ቻይናን በወፍ በረር ማስቃኜቴ ይታወሳል።
እንደውም ከወጣሁበት118ኛ
ፎቅ ሳልወርድ ነበር ቅኝቴን የቋጨሁት። ስወርድ
በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጌ እንደማስቃኛችሁ
ቃል ገብቸ ነበር። እናም በቃሌ መሰረት አንድ
ጉዳይ መርጫለሁ። ቻይናን ስለሰሯት ጋዜጦች
አወጋችኋለሁ። ስለዚህ ከወጣሁበት 118ኛው
ፎቅ ልውረድና
ቅኝቴን ልጀምር።
አሁን
አንጋፋ ጋዜጣ ለመጎብኘት ከሻንጋይ ወደ ቤጂንግ
ገብቻለሁ። ቀኑ ደግሞ በቻይና አቆጣጠር
ማክሰኞ መስከረም 25
ቀን
2018 ሆኗል።
መግቢያው ላይ ‘People’s
Daily’ የሚል
ጽሁፍ በትልቁ ተጽፏል። የምንጎበኘው አንጋፋ
ጋዜጣ ነው። ልክ እንደኛው አዲስ ዘመን ጋዜጣ።
ብዙ ወጣት ጋዜጠኞች ይሰሩበታል። በእኛ አገር
ልምድ ትምህርት ቤት የሚገቡ ነው የሚምስሉት።
ምክንያቱም አብዛኞቹ የወጣቶች ናቸው።
ወደ
ውስጥ ሲዘለቁ አንጋፎች ያያሉ። እንደኛ አገር
እስከ ጡረታ አድሜ ድረስ ሳይሆን በዛ ከተባለ
40 ዓመት
ቢሆናቸው ናቸው አንጋፋ ጋዜጠኛ የሚባሉት።
ሁሉም ጋዜጠኞች በጠባቡ በተከፈለ ቦታ ሆነው
የራሳቸውን ያዘጋጃሉ። እጅግ ዘመናዊና የአማረ
አሰራር አላቸው። ከህንጻው ጀምሮ ያለው
አደረጃጀትም በጣም ውብ ነው። ባህር ዳርቻ
ያሉና ለመዝናናት የወጡ እንጂ መስሪያ ቤት
ሆነው ሥራ የሚሰሩ አይመስልም። በየደረጃው
መዝናኛ ክበቦችና መስተንግዶዎች፤ የመወያያ
ጠረጴዛዎች፤ የእንግዳ መቀበያዎችም ፤ ማንም
ሰው ራሱን ማስተናገድ የሚችልበት ኪችን
ይታያል። ይህ ደግሞ ለጋዜጠኞቹ ምን ያህል
ምቹነት እንዳለው የሚያመላክት ነው።
ከበር
ወደ ውስጥ ስንገባ መጀመሪያ የተቀበለን ጋዜጣው
ለቻይና ብልጽግና ምን ያህል አበርክቶ እንደነበረው
የሚያትት ታሪክ ነው። መረጃው የሚታየው
በሰክሪን አማካኝነት ሲሆን፤ ግድግዳ ላይ
የተለጠፈ ነው። በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሽከረከረ
የተፈጥሮ ሀብታቸውን ከጋዜጣው ታሪክ ጋር
እያደባለቀ መረጃ ያስተላልፋል። እዚህ ጋር
አንድ ገጠመኜን ላጫውታችሁ።
«ውዱ
አፋችን»
ብለን
የሰየምነው ባልደረባችን አለ። ለምን እንዳልነው
ከታች አጫውታችኋለሁ። ከአስጎብኛችን ጎን
ነበር እየተጓዘ ያለው። ድንገት አንድ ጥያቄ
ቀረበለት ግድግዳው ላይ የተለጠፈውን መሳሪያ
እያመላከቱ«እስኪ
ይህንን ንካው»
የሚል።
እርሱም ፈጠን ብሎ ምላሽ ሰጠ። በፊት የተለያዩ
የተፈጥሮ ገጽታዎችን ሲያሳይ የነበረው እስክሪን
በመነካቱ ተለወጠና ጋዜጦቻቸውን ደርድሮ
ማሳየት ጀመረ። ቀጠሉናም «የተወለድክበት
ቀንና ወር እንዲሁም ዓመተ ምህረት ንገረን»
አሉት።
እየመለሰ ሳለም ስክሪኑን ነካክተው «በአንተ
ልደት ቀን ይህ ጋዜጣ ወጥቷል። የነበረው
ይዘትም ይህንን ይመስላል»
በማለት
በዝርዝር አስረዱት። አንድ ነገር በአዕምሮዬ
አቃጨለ።
ጋዜጣው
በቻይና ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ሚዲያዎች
ቀዳሚ ነው። የመጀመሪያ እትሙም እ.አ.አ
በ1948 ነበር
ለንባብ የበቃው። ግን ያለው እድሜ ከእኛው
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ሲወዳደር በእጅጉ
ይራራቃል። ነገር ግን የዓመታት ቆይታው
በቴክኖሎጅ ታግዞ እጅን በመሰንዘር ብቻ
ይገኛል። የ1933ቷን
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በቅጡ ያስቀመጣት ካልሆነ
በቀር ከድርጅቱ
ቤተመፃህፍት ውጭ
ማግኘት አስቸጋሪ ነው። «በቴክኖሎጅ
ታግዞ በዓመታትና በቀናት እንዲሁም በወራት
ይህንን አውጥተናል፤ ይዘቱ ይህንን ይመስል
ነበር ማለት ምንኛ መታደል ነው»
አልኩ
በውስጤ። ግን ምኞት ብቻ ሆነብኝና ጉዞዬን
ወደሌላኛው ክፍል አደረግሁ። ጋዜጣው ግን
አሁንም ማስደነቁን አላቋረጠም።
ከ2ሺህ
በላይ ሠራተኞች አሉት። 1ሺህ
የሚሆኑ የአዲሱ ሚዲያ፣ የኦንላይንና
የማኅበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኞች ስራቸውን
በብቃት ያከናውናሉ። ምንም የተዝረከረከ
ነገር ተቋሙ ውስጥ አይታይም። በቻይንኛ ቋንቋ
በ32
ቅርንጫፎቹ፤
በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ በ11
ቅርንጫፎቹ
እየተዘጋጀ ያሰራጫል። ሲሰሩ የሚታዩት ሰዎች
ክፍሉ ሸፍኗቸው የት እንዳሉ ለማወቅ እንኳን
ይቸግራል። በፊት አዲሱ ሚዲያ የሚባል ነበር።
አሁን ግን ከነባሮች ጋር ተቀናጅቶ መስራት
በመጀመሩ ልዩነቱን አጥፍቶታል። ሁሉም ቻይናን
በጋዜጣ ለመስራት ብቻ ነው የሚጣደፈው። አዲሱ
ሚዲያ በቴክኖሎጂ ርቀቱ የተሻለ ስለሆነ ነባሩን
ያግዛል። ነባሩ ደግሞ አሰራሩን የለመደና
ብዙ ታሪኮችን የሚያውቅ ስለሆነ አዲሱን
በአካሂድ ያስተካክለዋል።
ስያሜውን
በቀድሞ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መሥራችና
ሊቀመንበር ማኦ እንዳገኘ የሚነገርለት ይህ
ጋዜጣ፤ ሥራዎቻቸውን በማኅበራዊ
ሚዲያ፣ አፕሊኬሽንና በኦንላይን በስፋት
ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ስለሚያደርግ 24
ሰዓት
ቻይናን በቅኝቱ ያካትታል። በየተንቀሳቀሰበት
ሁሉ ነው የሚሰራው። ከኅብረተሰቡ የሚሰጣቸውን
የአሠራርና የጥቆማ ተግባር ይበልጥ ለአገራቸውና
ለጋዜጣው እድገት እንዲያግዝ አድርጎ የመጠቀሙም
ሁኔታ የሚያስደምም ነው። ከማህበራዊ ሚዲያው
በላቀ ሁኔታ ጋዜጣውን ተወዳጅ ያደረጉበት
መንገድም እንዲሁ ያስገርማል።
የዜናና
አርቲክል ተነባቢነትን ለመጨመር የተለያዩ
ስልቶችን ይጠቀማሉ። ለአብነት የአንድ ሪፖርትር
ሥራ ጋዜጣ ላይ ከመውጣቱ በፊት ብዙ የአርትኦት
ሥራ ይሰራሉ። «ጋዜጣ
መረጃነቱ እንደ ኦላይኑ አይደለም። በማንኛውም
ጊዜ የማይጠፋና የማይፋቅ ቅርስ ነው»
የሚል
እምነት አላቸው። በዚህም ከዌብሳይት በበለጠ
ጥንቃቄ ያደርጉበታል፤ በቅርስነት እንዲቆጠር
ለማድረግም ይጥራሉ። ለዚህም የራሱ የሆነ
የአርትኦትና ሌሎች ክንውኖችን በብቸኝነት
የሚሰራ የሚዲያ ማዕከል አቋቁመውለታል።
ማዕከሉ
የወጡ መረጃዎችን የአስፈላጊነት መጠን አይቶ
እንደገና ማዳበሪያ አድርጎ በኦላይንም ሆነ
በጋዜጣው እንዲወጡ ያደርጋል። የሚለቀቀውን
መረጃ በይዘቱ፣ በጥራቱና በህዝብ ዘንድ ያለው
ተቀባይነትን በመመዘን ደረጃ ያወጣል። ከዚያ
ከጀማሪ ጋዜጠኛው ጀምሮ አርትኦቱን እስከሰራው
ጋዜጠኛ ድረስ የደረጃና የጥቅማጥቅም እድገት
ያደርጋል። ይህ ደግሞ በእኔነት መንፈስ የሚሰሩ
ጋዜጠኞችን ፈጥሯል።
ከተደራሽነቱ
አንጻርም ከማህበረሰቡ ጋር ሊያቀርበው በሚችለው
በሌሎች 7
የብሔረሰቡ
ቋንቋዎች ጋዜጣውን ያሳትማል። 9
የዓለም
አቀፍ ቋንቋዎችንም በማካተት አሳትሞ ያሰራጫል።
በዚያ ላይ 5
የቀጥታ
ማሰራጫ ጣቢያዎች እና 200
የምስል
ንግግር ስቱዲዮዎች አሉት። ስለዚህም መላውን
ቻይና በጋዜጣው ለማሳየት ይሰራል።
ሌላው
ቻይናን ሰርቷል የሚባለው ጋዜጣ ቻይና ዴይሊ
ሲሆን፤ መገኛው ሻንሃይ ነው። ስለዚህ ጋዜጣ
ለመንገር ደግሞ ከነበርኩበት መመለስ ግድ
ሊለኝ ነው። እናም ወደ ሻንሃይ በሀሳበ ተከተሉኝ።
በእርግጥ ስለጋዜጣው ስነግራችሁ ከላይ
ከጠቀስኩት ጋዜጣ የሚለይበትን ሁኔታ በማንሳት
ብቻ ነው። በቻይና አንድ አይነት የአወቃቀርና
የአሰራር ስልት ስላለ በሁለቱም ጋዜጦች ውስጥ
የሚታየው አደረጃጀትና የስራ ቦታ ምቹነት
ተመሳሳይ ነውና ለየት ያለውን ላንሳ።
ቻይና
ደይሊ በየቀኑ የሚታተምና የስርጭት አድማሱ
ግዙፍ የሆነ ጋዜጣ ነው። በብዛት በሀገሪቱና
በመላ እስያ ይሰራጫል። ራሱን የቻለ አዲሱ
ሚዲያ፣ ዌብሳይትና ኦንላይን ሚዲያ የሚባሉ
ክፍሎችም አሉት። እንደውም በእኛም አገር
እየገባ ስናነበው ቆይተናል። በቻይና በጣም
ትልቅ የፌስቡክ ተከታይ ያለው ነው። በአሁኑ
ወቅት 54
ሚሊዮን
የሚደርሱ ደምበኞች አሉት። በአፍሪካ በኬንያ
ናይሮቢ ውስጥ በየሳምንቱ እየታተመ ይቸበቸባል።
ቻይና
ዴይሊ «አፍሪካ
ዊክሊ»
እየተባለ
አፍሪካን ያዳርሳል። ይህንን ሁሉ ሲያደርግ
ዋና ጉዳዩ ግን የአገሩን ገፅታ መገንባትና
ማስተዋወቅ ነው። የቻይና የኢኮኖሚ መረብም
መሆን ነው። በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ
ገጽታ ቻይናን ማበልጸግ ነው።
በቻይና
ደይሊ ጋዜጠኛው ሥራዎቹን ሲሰራ የሚወደውን
ነገር ከስሩ አስቀምጦ ነው። መስራት የሚፈልገውን
ተግባር ተኮር ለማድረግ የሚጥርበት ሁኔታም
በእጅጉ የረቀቀ ነው። ሰራተኞቹ ቤት ውስጥ
ያሉ እንጂ የሥራ ቦታቸው ያሉ ሳይመስላቸው
ይጽፋሉ፣ ያወራሉ፣ ይወያያሉ። ይህ በመሆኑም
የአገራቸው ነጋዴ ያለምንም እንግልት እንዲሰራ
ጥቆማ ይሰጡታል፤ ሸማቹ የማኅበረሰብ ክፍልም
የት የሚመጥነውን እቃ ማግኘት እንደሚችል
ይነግሩታል። በዚህም ማኅበረሰቡንና ጋዜጣውን
እንዳይለያይ አድርገውታል።
ቻይና
ደይሊ ከፍተኛ የሚባለውን ደሞዝ ለጋዜጠኞቹ
ይከፍላል። በእኛ አገር ካለው የጋዜጠኞች
ደሞዝ አከፋፈል ጋር እንዳያነፃፅሩት።
ቻይናውያን ቋንቋቸውን በይበልጥ ያከብሩታል።
በቋንቋቸው መኖርንና ማደግንም ይፈልጋሉ።
እናም ከእንግሊዝኛ ይልቅ ቻይንኛን መናገርን
ስለሚመርጡ ተግባቦታችን ሁሉ በአስተርጓሚ
ነው። ይህም ቢሆን ጥሩ የማዳመጥ ልምድን
ይጠይቃል።
ውዱ
አፋችን ያልነው ባልደረባችን የሚመጣው እዚህ
ላይ ነው። ከነበርነው 4ኢትዮጵያን
«ውዱ
አፋችን»
ብለን
ስያሜ የሰጠነው አንድ ባልደረባችን የሚሰባበሩ
የእንግሊዝኛ ቃላት እየተጠቀመ ይሰማና መልስ
ይሰጣል። አንዳንዱን መስማታችን አይቀርምና
ድንገት በድህነታችን የተሳቀቅንበትን ነገር
ሰማን። «ለመሆኑ
በእናንተ አገር ለአንድ ጋዜጠኛ በአማካይ
ስንት ይከፈላል»
የሚል
ጥያቄ ከቻይናዊያን ተሰነዘረ። ያው የፈረደበት
ውድ አፋችን ቀልጠፍ ብሎ «እንደ
ድርጅቱ ሁኔታ ቢለያይም በአማካኝ በእኛ ተቋም
በአዘጋጅ ደረጃ ላይ ያሉ ጋዜጠኞች 10ሺህ
1መቶ
ብር ይከፈላቸዋል»
አለ።
ጥያቄ አንሽውም ሆነ ሌሎቹ በተደናገጠ አይን
አዩን። ሁላችንም ግራ ተጋባን።
ወዲያው
«በእኛ
ለጀማሪው በሚከፈለው ላይ ዜሮ ጨምርበት»
ሲሉ
ደሞዛቸው ከእኛ ምን ያህል ርቀት እንዳለው
ነገሩን። 100ሺ
ዩዋን መሆኑ ነው። ውዱ አፋችን ግን አልተሸነፈላቸውም
«የኢኮኖሚ
ደረጃችሁ ነው፤ እኛም አንድ ቀን የእናንተን
ያህል እናገኝ ይሆናል»
ሲል
መለሰላቸው። ደስ አለኝ፤ የተሸማቀኩትን
ያህል ፈታ አልኩ። ግን እውነት ነው ምን
ያሸማቅቀኛል ብዬ ራሴን አረጋጋሁ። መቼም
ሃያል ከተባለች ሀገር እኩል መሆን አይቻልም።
ግን ልዩነቱ ሲሰፋ ማስቆጨቱ አይቀርም። ልዩነቱ
በመስራትና ባለመስራት መካከል የመጣ መሆኑንም
አስባለሁ።
እና
ምን ይሁን ካላችሁኝ ጋዜጦቻችን አገራችንን
ይስሯት፤ የሚያነቡ የማህበረሰብ ክፍሎችን
ይፈጠሩ፤ አስተያየት ሰጪ እንጂ ትርጉም አልባ
ትችቶችን እንቀንስ ነው ምላሹ። እንደቻይና
ለመሆንና ከቁጭት ለመውጣት በጋዜጦቻችን
ኢትዮጵያን እንስራት። በተለይ የማኅበረሰቡ
አስተያየትና ጥንካሬ ለለውጡ መሰረት ነውና
እናስብበት። ሰላም!
No comments:
Post a Comment