Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

የደብዳቤ ጩኸትና የአዳራሽ ጸጥታ


የደብዳቤ ጩኸትና የአዳራሽ ጸጥታ
ዋለልኝ አየለ
ደግነቱ እየለመድኩት ነው እንጂ ብዙ ደብዳቤዎች እያጭበረበሩኝ ነበር፡፡ ጋዜጠኝነት ብዙ ነገር ያሳያል፡፡ ለዚያውም እኮ አሁን የማነሳላችሁ ችግር በጣም ቀላሉ የሚባለው ነው፡፡ መቼም ለዘገባ ሥራ ከጋዜጣዊ መግለጫ የቀለለ አይኖርም አይደል? ታዲያ በዚህ ውስጥ የሚያጋጥም ብዙ ልብ ያልተባለ ችግር አለ፡፡ ከሰሞኑ ያጋጠመኝን ለመናገር ፈለኩ፡፡
አንድ መስሪያ ቤት መግለጫ እሰጣለሁ ብሎ ደብዳቤ ላከ፡፡ እንግዲህ ይህን ሥራ እንድዘግብ ተመደብኩ፡፡ መቼም ደብዳቤውን ብታዩት የተኩስ አቁም ስምምነት መግለጫ እንጂ የአንድ የተለመደ ጉዳይ መግለጫ አይመስልም፡፡ መገረም ከመጀመራችሁ በፊት ቆይ ልጨርሰው! የጉዳዩ ቀላልነት አይደለም የሚያስገርመው (እሱማ መቼም ታምኖበት ልሄድ ነው) የሚያስገርመው ያውም ቀላሉ ነገር ያልታሰበበት መሆኑ ነው፡፡ ሰው እንዴት ሊያዘጋጅ የነበረውን ነገር ይረሳዋል?
ደብዳቤው ላይ የተጠቀሰው ሰዓት 800 ነው፡፡ በዚህ በተዘጋጋ መንገድ ቀልቤን አጥቼ በሰዓቱ ደረስኩ፡፡ ኧረ ወዲያ እቴ! ከቦታው ስደርስ ምንም ነገር የለም፡፡ ከአንደኛ ፎቅ ጀምሬ ያገኘሁትን ሁሉ ስጠይቅ ምንም ነገር አያውቁም፡፡ ራሴን ተጠራጠርኩ፡፡ ‹‹እንዴ መስሪያ ቤቱን ተሳሳትኩ እንዴ!›› ብየ ደብዳቤውን ደግሜ አየሁት፤ ልክ ነኝ፡፡ ‹‹መቼስ በስሙ ሌላ መስሪያ ቤት ይኖራል እንዴ!›› እያልኩ ወደዋና ዳይሬክተሩ ቢሮ ወጣሁ፡፡ እዚህ ስደርስ ትንሽ ይሻላል፤ ስንት ሰዓት እንደሆነ ባያውቁም ቢያንስ አለ መባሉን ሰምተዋል፡፡ መግለጫው ይኖራል ወደተባለበት አዳራሽ ስገባ ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎችን አገኘሁ፡፡
ያው መቼም የአገራችን የሰዓት ብክነት የተለመደ ነው ብለን ቁጭ አልን፡፡ ይህኛው ግን እንደተለመደውም አልሆነም፡፡ 900 ሆነ፡፡ አሁን መጠየቅ አለብን ብለን ስንጠይቅ የተሰጠን ምላሽ ብቻ መኖሩን እንጂ ማን እንደሚሰጥ ምን አይነት መግለጫ እንደሚሰጥ አያውቁም፡፡ ጋዜጠኞች ትተውት እየሄዱ ነው፡፡ ሦስት ብቻ ቀረን፡፡ 1000 ሆነ፡፡ አሁን እኛም ትዕግስታችን አለቀ፡፡ ልንሄድ ስንል ግን ተናግረን መሄድ አለብን ብለን እየፎከርን ወደ ጸሐፊዋ ስንሄድ መግለጫ የሚሰጠው ሰው እየመጣ ነው አሉን፡፡ ቆይ አሁንም ቸኩላችሁ እንዳትገረሙ፡፡ የሰዓቱ መዘግየት መስሏችሁ ነው ችግሩ? ዋና ዳይሬክተሩ ሲነግሩን የታሰበው ነገር ምንም የሚዲያ ሽፋን የሚያስፈልገው አይደለም፤ ይሸፈን ከተባለም ደብዳቤው ላይ ያለውና የታሰበው ነገር ምንም አይገናኙም፡፡ እንዲህማ ለፍተን አንመለስም ብለን ሰውየውን ቃለመጠይቅ አድርገን መጣን እላችኋለሁ፡፡
ይሄ የአንድ ቀን አጋጣሚ ነው፡፡ ለየት ያለ ያደረኩት ደብዳቤው ላይ የተጠቀሰውና ያለው ነገር ሌላና ሌላ ስለሆነ እንጂ የሰዓቱና የደብዳቤው ጩኸት ግን የብዙ ጊዜ ገጠመኜ ነው፡፡ ደብዳቤ ላይ በሃይል ያጮሁታል፡፡ ለምሳሌ የማይገኝ ባለሥልጣን ይገኛል ማለት፤ የማይገኝ ታዋቂ ሰው ይገኛል ማለት፤ የማይከናወን ፕሮግራም ይከናወናል ማለት… የተለመደ ነው፡፡ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ላይ ግን አንድ ችግር እረዳላቸዋለሁ፡፡ ይሄውም እንመጣለን ብለው ላይመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ብዙም ላይወቀሱ ይችላሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን እንደማይመጡ እየታወቀም ደብዳቤ ላይ ይገለጻል፡፡ በተራ ነገር ሁሉ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት፣ ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት፣ ሚኒስትሩ በተገኙበት…›› እየተባለ ይገለጻል፡፡ ዝግጅቱ ላይ ግን እንኳን ባለሥልጣናቱ ራሳቸው የፕሮግራሙ አዘጋጆች ላይገኙ ይችላሉ፡፡
የባለሥልጣናቱን መቅረትም ቢሆን እኮ የሚያውቁት ቀድመው ነው፡፡ ችግሩ ግን እንደማይመጡ ነግረዋቸው እንኳን የፕሮግራም ዝርዝር ላይ ያወጡታል፡፡ እሺ የባለሥልጣናቱስ ይሆን፤ የሌላ ፕሮግራም ለምን አለ ተብሎ ይነገራል? ደብዳቤውን የሚጽፈው ሰው የዚያ መስሪያ ቤት ሰራተኛ አይደለም ማለት ነው? መስሪያ ቤቱ ምን እንዳዘጋጀ እንዴት አይናበቡም?
በነገራችን ላይ እነዚህ ደብዳቤች እኮ የተሳሳተ መረጃም እየሰጡ ነው፡፡ ለምሳሌ የብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ ከደብዳቤ ብቻ ዜና ሲሰራ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይም ጠዋት ጠዋት በዕለቱ የሚከናወኑ ነገሮችን ይጠቆማል፡፡ ምንም እንኳን ከዕለቱ ክንውኖች ለመጠቀስ የሚበቃ ባይሆንም ያ የነገርኳችሁ ያጋጠመኝ ነገር ተነግሮ ቢሆን እኮ ክስረት ነበር፡፡
እንግዲህ ዛሬ አስተውሎታችን ስለጋዜጣዊ መግለጫ አሰጣጥ ነው፡፡ አገላለጤ ግልጽ ካልሆነ ሌላም የመግለጫ ችግር ልግለጽላችሁ፡፡ ይሄኛው ደግሞ ሲያናድድ!
በመጀመሪያ የዘገባ ሽፋን እንዲሰጥላቸው ለመገናኛ ብዙኃን ደብዳቤ ይልካሉ፡፡ የዘገየውም ይዘገይና በሰዓቱ የመጣው በሰዓቱ ይመጣል፡፡ ይህን ታዲያ አንዳንዶቹ ያ የሚፈልጉት ሚዲያ ካልመጣ መግለጫውን አይሰጡም፡፡ በተለይም ጋዜጣና ሬዲዮ ብዙም ልብ አይባሉም፡፡ የእነርሱ ቀድሞ መምጣት ምንም ነው፡፡ ያ የሚፈልጉት ሚዲያ ከመጣ ግን መግለጫው ይሰጣል፡፡
አሁንም አንድ ያጋጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር(አንዳንዴማ ስም እየጠራሁ ይሁን) የጎርፍ አደጋን መከላከል በተመለከተ መግለጫ ለመስጠት ሚዲያ ጠርቷል፡፡ የተጠራው 400 ነው፡፡ እኔን ጨምሮ ከተለያየ ሚዲያ የመጡ ጋዜጠኞች በሰዓቱ ተገኝተናል፡፡ መግለጫ የሚሰጥበት አዳራሽ ስንደርስ ዝግ ነው፡፡ ገና ሆኖ ነው ብለን ውጭ ቆምን፡፡ በር ላይ ያገኘነውን ሰው ስንጠይቅ መግለጫው እያለቀ ነው፡፡ መግለጫው ለኢቢሲ እየተሰጠ ነው፡፡ ‹‹ምነው?›› ስንል ጠየቅን፡፡ ጉዳዩን ስንረዳ ኢቢሲ ለሌላ ጉዳይ ቀድሞ ሄዶ ስለነበር መግለጫውን የሚሰራው እግረ መንገዱን ነው፡፡ የተባለው ሰዓት እስከሚደርስ አይጠብቃቸውም፡፡ ስለዚህ እሱ ከሚሄድ ሌላው ሚዲያ ለፍቶ ቢቀር ይሻላል ብለው መግለጫውን ሰጡ ማለት ነው፡፡
ግዴላችሁም ይቺ የመጨረሻ ገጠመኝ ትሁን፡፡ ይሄ ደግሞ ባለፈው ዓመት የሆነ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር መግለጫ ነው፡፡ መግለጫው የተጠራው 400 ነው፡፡ ማርፈዱን ስለለመድነው ምንም ሳንል 500 ሆነ፡፡ 500 ሚኒስትሯ መጡ፡፡ መግለጫ ሊሰጡ ሲሉ ኢቢሲ የለም፡፡ ‹‹የቀረ ሚዲያ ስላለ ትንሽ እንጠብቅ›› አሉ፡፡ ይህኔ ታዲያ የተከራከረ የለም፤ ሁሉም እየተነሳ መቅረጸ ድምጹን አነሳ፡፡ ይህኔ ሚኒስትሯም ልክ እንዳልሆኑ ገባቸውና መግለጫውን ሰጡ፡፡
ይቺኛዋን ገጠመኝ ያነሳኋት ያለምክንያት አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር መለመድ አለበት፡፡ አንድ ሚዲያ ለመጠበቅ ያ ሁሉ ሰው ሥራ መፍታት የለበትም፡፡ በተለይ በብሮድካስት ሚዲያ እኮ አንድ ደቂቃም ዋጋ አላት፡፡ ያ ይሰጣል የተባለው መግለጫ እኮ ለዜና ሽፋን ሰዓት ተይዞለታል፡፡ ሌላ ሥራም እንዳይሠራ እያደረጉ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የመግለጫዎችን መንዛዛት በሌሎች የመድረክ ፕሮግራሞችም ያዙት፡፡ የሌለ ነገር ደብዳቤ ላይ ይጮሃል፤ ሲሄዱ ባዶ አዳራሽ፡፡ ታዲያ እንዴት ይሻላል እንግዲህ ጎበዝ? ቀድመው ሲሄዱ እንዲህ የሰዓት ብክነት ያጋጥማል፤ ዘግይተው ቢሄዱም ለሚፈልጉት ሚዲያ ብቻ ይሰጣሉ፡፡
ይሄንን ችግር መቅረፍ የሚችሉት ማንም ሳይሆን ራሳቸው ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው፡፡ መስሪያ ቤቶች እንዲህ የሚያደርጉት እኮ ይህን ለምደው ነው፡፡ አንድ መስሪያ ቤት መግለጫ ጠርቶ ለአንድ ሚዲያ ብቻ ከሰጠ ይሄ ራሱ ዜና ነው፤ ደብዳቤው ላይ የተጠቀሰው ነገር ከሌለ ይሄ ራሱ ዜና ነው፡፡ አለበለዚያ ለ10 ደቂቃ መግለጫ 10 ሰዓት ማባከን የዋህነት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment