የደጋ
ዳሞት የእረኛ ግጥሞች
ጌትነት
ተስፋማርያም
የቃል
ግጥም ወይም ስነቃል ሰው በአዕምሮው የሚያመላልሰውን
ሀሳብ የሚያመጣበት መንገድ ነው፡፡ በቃል
ግጥም ሀሳብን ለማስተላለፍ የተማረ፣ ያልተማረ፣
ልጅ አዋቂ የሚል ውሳኔ የለም፡፡ የሰው ልጅ
ሀሳቡን ለሌሎች በቃል ማስተላለፍ የዕለት
ተዕለት ኑሮ ማለት ስለሆነ ዘወትር ከሰው ልጅ
የማይነጠል ሂደት ነው፡፡ በአጠቃላይ የቃል
ግጥም በአፍ ከሚነገሩ መካከል ሲመደብ ትዝታን፣
ፍቅርን፣ ኀዘንን፣ ትዝብትን፣ልመናን፣
ክፋትን ደግነትና ሌሎችንም ሁኔታዎች በሽለላ፣
በዘፈን፣ በእንጉርጉሮ ወዘተ በማቅረብ
መልዕክትን ማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡
የቃል
ግጥም ምንነት ቃላዊ ግጥም ከትውልድ ወደ
ትውልድ የሚተላለፍ በቃል የሚባል፣ የሚዜም፣
የሚገጠም ነው፡፡ ህብረተሰቡ በተለይ የገጠሩ
ነዋሪ በነጋ በጠባ አሰራሩንና አመለካከቱን
የሚገልጽበት ስነቃሎች እንዳሉት እሙን ነው፡፡
ስነ ቃል ከህዝብ ባህል አንዱ ዘርፍ መሆኑንና
ከተፃፉ ነገሮች የሚለዩበት ባህርያት፣ ክዋኔ፣
ተደራሲና አጋጣሚ አላቸው፡፡ የቃል ግጥም
በስነቃልነት መንገድ አንድ ህዝብ ባህሉን፣
ወጉንና ሥርዓቱን፣ ውስጣዊ ስሜቱን በቃል
ለማስተላለፍ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ
ነው፡፡ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ግጥምን
በደቦ ሥራ፣ በእረኞች፣ በለቅሶ፣ በሰርግ፣
በእርሻ፣ በየዓመት በዓሉ ውበትና ለዛ ባለሙ
መልኩ በማዜም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
አፋዊ
ኪነተቃል በአደራረሱ፣ አከዋውኑ፣ ተስተላልፎውና
አቀራረቡ ብዙ ጊዜ በመዜም የሚቀርብ፣ በዘፈን፣
በሙሾ፣ በእንጉርጉሮ እና በሌሎችም ተመሳሳይ
የዜማዊ ቅርፆች ውስጥ የሚገኝ ህዝባዊ ግጥም
ነው፡፡ የሥራ ግጥሞች ከሥራው ጋር ያላቸውን
ተራክቦ ሲገልጹ፣ የእርሻ ዘፈኖች ግጥም
በውቂያ፣ በማበራየት እና በሌሎችም የእርሻ
ክንውኖች ላይ ያተኩራሉ። እንዲሁም የእረኞች
ግጥም የሚባልም አለ። እረኞች በብዛት አብረው
ሲውሉ አንዱ ከአንዱ እየሰማ እና የእራሱንም
እየጨመረ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ
ስነቃል ይዘት ያላቸው ግጥሞችን ያሰማሉ።
በዚህ
ረገድ በተለያዩ አካባቢዎች የእረኞች ግጥሞች
መሰረት ያደረጉ ጥናቶች ተከናውነዋል አሁንም
በመከናወን ላይ ናቸው። በደጋ ዳሞት አካባቢ
ስላለው የእረኞች ግጥም ይዘት ትንተና ምንነት
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና
ሥነ ጽሑፍ ክፍል የተጠና ጥናት አለ። ጥናቱን
አቶ ሙሉቀን ጌትነት ያቀረቡ ሲሆን በ2001
ዓ.ም
የተሰናዳ ነው።
ደጋ
ዳሞት
ደጋዳሞት
በምዕራብ ጐጃም ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ
ነው፡፡ ወረዳው ከአዲስ አበባ 391
ኪሎ
ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። አካባቢው ደጋማ
የአየር ንብረት ስላለው ስያሜውን ከአየር
ንብረቱ እንዳገኘ የሚናገሩት ደግሞ ጥናቱን
ያካፈሉኝ የአካባቢው ነዋሪ አቶ በላይ ድረስ
ናቸው። ለሦስት ዓመታት የቤተሰቦቻቸውን
ከብቶች አግደዋል። እርሳቸው እንደሚሉት
የደጋዳሞት ሰዎች ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ በግ
እና ፍየል ፣ የቀንድ ከብት እንዲሁም የጋማ
ከብቶችን ያረባሉ።
እረኞች
ከብቶችን ግጦሽ ወዳለበት ቦታ በሚያሰማሩበት
በአንድ ቦታ ወይንም ትልቅ ዛፍ ስር ተሰባስበው
በጋራ ይጫወታሉ። ከእረኞች መካከል አንዳንዶቹ
ከተለያየ አጎራባች አካባቢዎች በችግር ምክንያት
ወይንም ለትምህርት ብለው ተቀጥረው በሰው
ቤት የሚሰሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የቤተሰቦቻቸውን
ከብቶች የሚያግዱ ናቸው። የእረኛ ሥራ በዋነኛነት
ከብቶችን መንከባከብና ማገድ ቢሆንም ለቤት
ውስጥ ክንውኖችም ትዕዛዝ ሊሰጣቸው ይችላል።
በሰብል ጥበቃ፣ በአጨዳ፣ በውቂያ፣ እና
በሌሎችም የእርሻ ወቅት ሥራዎች ላይ ይሰማራሉ።
ወረዳው
በአንዳንድ ወቅት ከተለመደው በላይ ቅዝቃዜ
ይታይበታል፡፡ ምንም እንኳን አሁን የአየር
ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቢያሳድርበትም ከጥቅምት
ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ ድረስ ያለው ወቅት ከፍተኛ
ቅዝቃዜ ይታይበታል። አካባቢውም በውርጭ እና
በቁር ይሸፈናል፡፡ ነዋሪው በአብዛኛው
ቅዝቃዜውን የተላመደው ቢሆንም በእነዚህ
ወራት ከጥጥ የተሰሩ ሙቀት ሰጪ ልብሶችን
ያዘወትራል። እረኞችም ከበግ ለምድ የተሰራ
ልብስ አዘጋጅተው ይለብሳሉ። በክረምት ወቅት
አካባቢው ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ እረኞች
የሚለብሱት ማቅ፣ ድሪቶ፣ ከበግ ቆዳ የሚሰራ
በአካባቢው አጠራር ደበሎና ጐጃም አዘነ
የመሳሰሉትን ቅዝቃዜውን ለመከላከል ይለብሳሉ፡፡
የደጋ
ዳሞት እረኞች
እረኞች
ውሏቸው በውጭ በመሆኑ ኃይለኛ ዝናብ በመጣ
ጊዜ ዛፍ ስር የሚቆሙ ቢሆንም በይበልጥ ሊያድናቸው
የሚችል ከቄጤማ የተሰራ «ገሳ»
እንዲሁም
አሮጌ ጃንጥላ ያዘጋጃሉ፡፡ እያንዳንዱ እረኛ
ከብቶችን ሲያግድ ከለስላሳ የባህር ዛፍ
ቅርፊት የተገመደ ጅራፍ ይኖረዋል፡፡ የጅራፉ
ጫፍ ደግሞ ድምጽ እንዲኖረው በፈረስ ጭራ
ይገመዳል አሁን አሁን ግን በማዳበሪያ ቃጫ
እየተተካ ይገኛል፡፡በክረምት ጊዜ እረኝነት
ከበጋው የበለጠ ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡
በክረምት
ወቅት እያንዳንዱ የማሳ
በሰብል የሚሸፈን በመሆኑ
ከብቶች በማሳ ውስጥ አልፈው እንዳይሄዱ ጠንክሮ
መጠበቅ ያስፈልጋል። አካባቢው በጉም ስለሚሸፈንም
ከብቶች በሌባ እንዳይሰረቁ እና ከዓይን
እንዳይሰወሩ እረኞች በንቃት ክትትል ያደርጋሉ።
ስለዚህ እረኞች በክረምት ወቅት ለምሳ ወደ
ቤት አይሄዱም፡፡ ወደሚያሰማሩበት ሜዳ
እንስሶቻቸውን ከፊት አድርገው እንጀራ፣ ዳቦ
ወይም ቆሎ ይዘው ይሄዳሉ፡፡
አሳዳሪዎቻቸው
ቤቶች ቅርበት ያላቸው እና በጉርብትና የተቀራረቡ
እረኞች ህብረታቸውን ይጠናከራል። ከዕለት
ወደ ዕለት የሚገናኙ ከሆነ ደግሞ ከብቶቻቸውን
በጋራ ሊያሰማሩ ይችላሉ። እነዚህ እረኞች
በህብረት ሆነው በሚውሉበት ጊዜ ከጨዋታ አልፈው
አንዳንድ ሥራዎችን ይሰራሉ፡፡ ከብቶቻቸው
አረፍ ሲሉ ገመድ መግመድ፣ ቅርጫት መስራት
እና የመሳሰሉትን ሥራዎች በተጨማሪነት
ያከናውናሉ፡፡ በክረምት ወቅት ደግሞ የጅራፍ
ማጮህ ፉክክር እረኞች መካከል ይካሄዳል፡፡
አለፍ ሲልም በመተራረብና በዘፈን መልክ
ኀዘናቸውን እንዲሁም ደስታቸውን በስነቃል
ይገላለጻሉ። በደጋ ዳሞት የሚገኝ አንድ እረኛ
የዕለት ተዕለት ህይወቱ በስነቃል ላይ የተመሰረተ
ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእረኛ ግጥም ውስጥ
ደግሞ ሊዳሰስ የሚችል ሰፊ የማህበራዊ ጉዳይ
እንዳለ እሙን ነው።
በአቶ
ሙሉቀን የደጋ ዳሞት የእረኛ ግጥሞች ጥናት
መሰረት ስነቃሉ አንድም በማህበረሰቡ ውስጥ
ያለን ክፍተት ለማሳየት እንዲሁም የእኔ ይበልጥ
የእኔ ስሜቶችን
የሚቀርቡ ናቸው። በጥናቱ መሰረት በአካባቢው
ከሚገኙ ፈረስ ቤት ሚካኤል፣ ዝቋላ፣ አረፋ
ደብተራ፣ አበግራ፣ ሸምብርማ፣ ሻንጊ ደረቄ፣
ቋቁቻ፣ ወገም፣ ድኩልካና፣ጠሊምና ፍላጢት
በተባሉ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ እረኞች
የሚጠቀሟቸው ስነቃላት ተወስደዋል።
እረኞቹ
ከብቶችን በኃላፊነት ከመጠበቅ አልፈው የራሳቸው
የሆነ እንዲሁም ከማህበረሰቡ የሰሙትንና
ያዩትን ጉዳይ በሜዳ ላይ ይጫወቱታል፡፡
ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ተረብ፣ ዘፈን፣
ቀልድ የተካተቱባቸው ናቸው።፡ በመሆኑም
በጨዋታው ላይም ሆነ ያለጨዋታ በእረኞች
የሚደረደሩና የሚዘፈኑ ስነቃላት ሰፊ ማህበራዊ
ጉዳዮችን ይዳስሱበታል።
የእረኛ
ግጥም
እረኞች
ከሚጠቀሙባቸው ስነቃሎች አንዱ የጅራፍ ግጥም
ነው። ጅራፍ ማጮህ በእረኞች ዘንድ የሚዘወተር
የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ጅራፍ በቡሄ ወቅት
ይበልጥ ቢዘወተርም የአካባቢው እረኞች በብዛት
ከብቶቻቸውን ለማገድ ጅራፋቸውን ይዘው ይወጣሉ።
ከብቶችን ሜዳ ላይ በማሰማራት ጅራፍ ይዘው
በማጮህ ይወዳደራሉ፡፡ አንደኛው ወገን
የሌላኛውን ወገን «ከአንተ
ጅራፍ የእኔ ጅራፍ ጩኸት ይልቃል»
በማለት
እያንዳንዱ የራሱን ከፍ የሌላውን ዝቅ በማድረግ
ይፎካከሩበታል። ሆኖም እረኞች በጅራፍ ጩኸት
ውድድር ጊዜ ያሸነፈው ቡድን ይዘፍናል፡፡ተሸናፊውም
ቢሆን ራሱን ለማጠናከርና ለማበረታታት የራሱን
የመልስ ዘፈን ይዘፍናል፡፡ ይህን የጅራፍ
ውድድር ሁለትና ከዚያ በላይ ሊጫወቱት ይችላሉ፡፡
«የአንተ
ጅራፍ ለከስካሳ፣
የኔ
ጅራፍ አንበሳ፣
ስማው
ስማው ሲያገሳ፡፡
የአንተ
ጅራፍ ስትቆረጥ ፣
በኔ
ለመድረስ ወገብህ አይቆረጥ »
እየተባባሉ
በልጦ መገኘትን ይለማመዳሉ።
በሌላ
በኩል አንድ በሰው ቤት ተቀጥሮ ሰርቶ የሚበላ
እረኛ እና ሌላው በወላጆቹ ቤት እንደልቡ
የሚኖር እረኛ በአንድ ሜዳ ከብት ሲያግዱ
በሚገናኙበት ወቅት የሚጫወቱት ጨዋታ አለ፡፡
በሰው ቤት ተቀጥሮ ቢሰራም ስንፍናው ያስቸገረ፤
ሁሌም ከአሰሪዎች ቤት የማይለምድ በየጊዜው
በተለያየ ሰዎች ቤት እየዞረ የሚቀጠርን እረኛ
ይተረባል። እንዲሁም በእናት እና በአባቱ
ቤት እያለ ከብቶቹን የማይቆጣጠር እና አብዛኛውን
ጊዜ ቤት ውስጥ የሚውል እረኛ ብዙ ጊዜ ተረቡ
ከሚያርፍባቸው መካከል ናቸው። በጧት የማይነሳ
ሰነፍ፣ እንቅልፋምን ደግሞ በአካባቢው ያሉ
የጓደኞቹ ከብቶች በጠዋት ሲወጡ «የእርሱማ
ከብቶች ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ከቤት አይወጡም»
እየተባለ
ይዜምበታል።
እነዚህ
እረኞች የሚጫወቱት ምሽት አካባቢ ከብቶችን
ወደ መንደር ካስጠጉ በኋላ ነው። ጓደኞች
ስንፍናውን ለመግለጽና ከአንዱ ቤት ሌላ ቤት
የሚቀያይር መሆኑን በጅራፍ ውድድር ጨዋታቸው
ላይ እንዲህ እያሉ ይገልፁለታል፡፡ ከብቶቻቸውን
ወደ በረት ሳያስገቡ ተራርቀው ኮረብታ ላይ
በመቆም ጅራፍ እያጮሁ ምልልስ ያደርጋሉ።
«ንሳ
ተቀበል የጅራፌን መልዕክት፣
መስከረም
ጠባ ስትዞርለከት፣
ብታስታውሰው
አበቧ ልሙጀ፣
እንግዲህ
ይብቃህ ያለው ምድጃ»
ሲል
አንደኛው ሌላኛው እረኛ ደግሞ መልስ ለመስጠት
«ንሳ
ተቀበል የጅራፌን ጩኸት፣
ቡሃቃውን
አምጣ ከትንሿ ማጀት፣
ታች
ምድጃ ስጣት ለናትህ፣
ስታነኳኩር
እንድታጐርስህ»
እያለ
ይተርበዋል ሰነፉን እረኛ።
የ«አህያ
መጣች»
የእረኛ
ግጥም
የ«አህያ
መጣች»
ግጥሞች
መቼ እንደተጀመሩ ባይታወቅም በደጋዳሞት
አካባቢ ያሉ እረኞች በብዛትም ባይሆን ሲጠቀሙበት
እንደሚስተዋል በጥናቱ ሰፍሯል። እረኞቹ
ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ «አው
...አው»
ብለው
ጉሮሮአቸውን ከጠራረጉ በኋላ ግጥሙን ያሰማሉ፡፡
እነዚህ ግጥሞች የተለያዩ አሉታዊ ድርጊቶችን
የሚነቅፉ፣ የሚያወግዙ፣ አንዳንዴም ለማስጠንቀቅ
የሚሞክሩ ናቸው፡፡
ለአብነት
ክፉ ወረርሽኝ በገባ ጊዜ የአንዱ አካባቢ
ለሌላው
«አህያ
መጣች ተጭና ወንበር፤
እጣን
አሮጌው ይቀጠፍ ጀመር»
እያለ
ስለደረሰው በሽታ በስነቃል ሃሳቡን ይገልጻል።
እዚህ
ላይ «እጣን»
የሚለው
አገላለጽ «ህጻን»
የሚለውን
ትርጉም ይይዛል። ይህ ግጥም የሚያሳየን በሽታ
በአካባቢው ውስጥ መኖሩን ነው፡፡ በሽታ በአንድ
አካባቢ ከተከሰተ በኋላ ሁሉም አካባቢ በተለያየ
መንገድ መድረሱ አይቀርም፡፡ እረኞች የመጣውን
በሽታ ከሰሙ በአህያ መጣ ግጥማቸው እንደ
ማስጠንቀቂያ በመቁጠር መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
አህያ መጣች በተባለው ግጥም አያሌ የሆኑ
ማህበራዊ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ በተለይም
የአካባቢው ህብረተሰብ ፍላጐትና ምኞት በእረኞች
ስነቃል ላይ ይንፀባረቅበታል፡፡ በብዛት
የቤተሰብ እንስሳትን የሚያግዱ እረኞች
የወላጆቻቸው የግል ይዞታ የነበረ መሬት ወደ
ሌላሰው መዞሩን አስመልክተው የተቃውሞ ድምጽ
በግጥማቸው ያሰማሉ፡፡ እረኞች ይህን ድርጊት
የፈፀመውን ዳኛ ወይም የአካባቢው ሊቀመንበር
እረኛ ባለበት ቦታ ተሰባስበው በሚጫወቱበት
ወቅት እንዲህ እያሉ ይተቹታል፡፡
«አህያ
መጣች ተጭና ገብስ፣
ምን
የሚሉት ነው መሬት ማውረስ፣
ተትቶ
መሬት ወዴት ሊደረስ»
እረኞች
ከብት ሲያግዱ ከመንደር ከማህበረሰቡ ውስጥ
ለውስጥ የሚሰሙትን ምስጢር በሜዳ ያውሉታል፡፡
እረኞች ድንገት በቤት ሲወራ የሰሙትን ጉዳይ
በዜማቸው እየተቀባበሉ ይደረድሩታል፡፡
በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከባሏ ውጪ ሌላ
ወንድ ጋር ግንኙነት ያላት ሴት የተጠላች
ናት፡፡ይች ሴት ብዙ ጊዜ የባሏን ቤት ትታ
ውሽማዋን ወደምታገኝበት ቦታ ስትሄድ ከታየች
ወይም ወሬ ከተሰማባት በእረኞች ትሰደባለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሚስቱ ከሌላ ወንድ ጋር ግንኙነት
እንዳላት የሚጠረጥር ባል በማህበረሰቡ ዘንድ
ዝቅተኛ ግምት ይሰጠዋል። ምክንያቱም ሚስቱን
መቆጣጠር አይችልም ተብሎ ስለሚታሰብ ክብር
አይሰጠውም፡፡ ነገር ግን አጥፊዎቹን ለማረም
ደግሞ እረኞች ከመንደር የቃረሙትን ወይም
ያዩት ጉዳይ ላይ ተመስርተው ይገጥማሉ።
«አህያ
መጣች ተጭና ዳባ
እገሊት
ሄደች ጉድባ ለጉድባ፡፡
አንተ
አያ እገሌ የእንትና ባል
ምሽትህን
ጠብቅ አትበል ቸል፡፡
እንዲህ
ተሆነ የባልስራቱ
ቶሎ
ቶሎ በል ይቅረብ እራቱ፡፡
እግሯንም
አጥበህ አደስ ቀብተህ
ላክለት
እንጅ ላያ ውሽሜ
ለሜዳ
አህያ ለያሸምሽሜ»
እያሉ
ምክር አዘል ትችታቸውን በዜማ ያንቆረቁሩታል።
በሌላ
በኩል የአካባቢው እረኞች ሌብነት የተጠላ
ሥነ ምግባር መሆኑን ያውቃሉ፡፡ በአካባቢው
እንስሳትን እና የቤት ዕቃዎችን ጨለማን ተገን
በማድረግ የሚሰርቅ ሌባን ፊትለፊት በግጥም
ይሰድቡታል። ቤተሰቦቻቸው በሌቦች ሲማረሩ
ያደመጡ እና በሬ ሊሰርቅ በጨለማ የመጣው ሌባ
በድንጋይ መመታቱን እንዲሁም ጉድጓዶች ውስጥ
መግባቱን የተረዱ እረኞች በአንድ ወቅት ሌባውን
ሲያዩ እንደሚከተለው ተናግረውታል፡፡
«አህያ
መጣች ተጭና ሙሬ
አያ
እገሌ ገባ በጉድጓድ ሲሰርቅ በሬ»
በሰው
ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ እረኞች ደግሞ የኑሮአቸውን
ሁኔታ በሰው ቤት የሚንከራተቱት፣ በተጐሳቆለ
ኑሮ ያሉ፣ የሚራቡ፣ የሚገፋ ሆነው ግን የተለያየ
ባህር ያላቸው ይሆናሉ፡፡ አንደኛው ሰነፍ፣
ሌላኛው ሌባ፣ አንዱ በሆዱ የሚታማ እንዲሁም
የራሱንና የከብቶችን ደህንነት የማይጠብቅ
ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ እረኞች በአህያ መጣች
ግጥም እየተቀባበሉ እንደሚከተለው ይተራረባሉ፡፡
«አህያ
መጣች ተጭና ኮርቻ
ያ
ጓደኛየ መተኛት ብቻ፡፡
አህያ
መጣች ተጭና ለምድ
ያ
ጓደኛየ ማዞርያ ሆድ፡፡
አህያ
መጣች ተጭና ድስት
የእግሩ
ቅርጭጭት ያለው ብዛት»
እረኞች
በጓደኛቸው ያጋጠማቸውን ያለመታመን ችግር
በቀልድ መልክ በላሜ ቦራ ግጥም ይገልፁታል፡፡
«ላሜ
ቦራ እንች እንጀራ የዳጉሣ፤
ቢያንቀኝሳ፤
እግዜርሳ፤
እግዜርማ
ቆላ ወርዶ ተወራርዶ
ላሚቷ
ጥቁር ወተቷ ነጭ
የዘንድሮ
ሰው ተገላባጭ»
ይህን
የቀልድ ግጥም ሲዘፍኑ እርስ በርስ እየተቀባበሉ
ነው፡፡ እረኞች በመካከላቸው እንደዚህ አይነት
ባህሪ ያለበትን ልጅ በግጥም መልክ ይነግሩታል፡፡
የእረኛ
ብሶት ግጥሞች
በጥናቱ
መሰረት እረኞች ብሶታቸውን የሚያቀርቡበት
ስነቃል አላቸው። ችግሮቻቸውን በተለያየ ጊዜ
ከሚገኝበት የኑሮ ደረጃ ጋር በማዛመድ
በእንጉርጉሮ፣ በዘፈን፣ በፉከራና በቅረርቶ
ብሶታቸውን ያሰማሉ፡፡ በውስጡ የታመቀውን
ብሶትና ወደፊት ይሆናል ብሎ የሚገምተውን
ችግር ከአዕምሮው አውጥቶ በመናገሩ ከችግሩ
የተላቀቀ እየመሰለው ይረካል፡፡ እረኞች
ብዙጊዜ ተቀጥረው በሚሰሩበት ቤት የሚደርስባቸውን
በደል በእንጉርጉሮ ይገልፃሉ፡፡ እረኞች
ከብቶችን ሩቅ ቦታ ይዘው የሚሄዱ ከሆነ በጠዋት
ተነስቶ ለእነሱ ምግብ አይሰራላቸውም፡፡
በጠዋት ሳይበሉ ከብቶችን ይዘው ይሄዳሉ፡፡
ምሳ የሚላክላቸው ከራባቸውና ከደከማቸው
በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃብ አንጀቱ
ቢጠበስ
«የሰው
ቤት እንጀራ ምን ቢጋገር ብዙ
ሳይርብ
አይገኝም ሳይቅበዘበዙ»
እያለ
ብሶቱን ይገልጻል።
እረኛ
በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ዝቅ ያለ ቦታ የሚሰጠው
በመሆኑ ለእረኛ ተብሎ ምግብ አይሰራም፡፡
እረኛ ቤት ያፈራውንና የተገኘውን በልቶ
ይውላል፡፡ ወጥ ከቤት ውስጥ አልቆ ከሆነ
በአዋዜ ወይም በድልህ ተደርጐ በደረቅ እንጀራ
ይሰጠዋል፡፡ ይህ አዋዜ መደጋገሙ ያሰለቸው
እረኛ የውስጡን እንደሚከተለው በእንጉርጉሮ
ቅሬታና ብሶቱን ይገልፃል፡፡
«ማታ
በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ፣
ምሳ
በጨው በላሁ እንዲያው በደረቁ
የሰው
ቤት እንጀራ ይሄ ነበር ጠንቁ፡፡
ራቡና
ጥሙ በዛብኝ ሁልጊዜ
የሚቀርበው
ምግብ ወጥ የለው አዋዜ»
እረኞች
በተቀጠሩበት ቤት ውስጥ እንደልጆች እኩል
ምግብ አይሰጣቸውም፡፡ ለእረኞች ትንሽ ሆኖ
የልጆች ትርፍራፊ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ
የከፋው እረኛ ብሶቱን ይገልፃል፡፡
«እህቴ
ትፍጭና እናቴ ትጋግረው፣
ይህን
በልቷል ብላ የማትናገረው።
አንች
የሰው እናት ይብላሽ አረመኔ፣
ትኩሱን
ለልጅሽ ያደረውን ለኔ።
አንች
የሰው እናት ጠባይሽ ወለላ፣
አይቡን
ለልጅሽ አጓቱን ለእረኛ»
እያለ
ያንጎራጉራል።
ከሰው
ቤት ተቀጥሮ በችግር ምክንያት የሰው አገልጋይ
በመሆኑ ያዝናል፡፡ እረኛው ቀኑን ሙሉ ከብት
ሲያግድ ይውላል፡፡ በተጨማሪም
ይጎጉላል፣ያርማል፣
ያጭዳል፣ ያበራያል እንዲሁም ሌሎች የቤት
ውስጥ
ሥራዎችን ይሰራል፡፡ በመሆኑም ሰዎቹ የሰራ
ስለማይመስላቸው ልፋቱን በሙሉ ገደል ይከቱበታል።
በዚህ ጊዜ
«ውሃ
ወርዶ ወርዶ መቆሚያው አባይ
እናት
ወልዳ ወልዳ ለሰው አገልጋይ
እውሃ
ቢዶሉት አይሟሟም ኩበት
አይመሰገንም
የድሃ ጉልበት»
በማለት
ስነቃሉን ያሰማል።
በተጨማሪ
በአካባቢው ብዙ መሬት ያለው ነገር ግን ጉልበቱ
ከመድከሙ የተነሳ መሬቱን ማረስ ያልቻለ ሰው
መሬቱን ማረስ ለሚችል ሰው በመስጠት አዝመራውን
እኩል ይካፈላል፡፡ እነዚህን ሰዎች የተመለከተ
እረኛ ቢከፋው ጊዜ ጉልበት ካለኝ የእኩል
እየሰራሁ፣ እየተዘዋወርኩ እኖራለሁ ለማለት
በግጥም መልዕክት እረኞች በከብት ጥበቃ ወቅት
እንደሚከተለው በዜማ ይዘፍኑታል፡፡
«ሚስትም
አላገባ ላሳብም አልቸኩል
የደከመ
እያየሁ እገባለሁ የኩል»
እያለ
ከዚህ ሁሉ ችግር ዕድሜው ለእርሻ ሲደርስ
የእኩል እየሰራ መኖር እንደሚችል ይገልጻል።
ግጥሙን በብዛት የሚጠቀሙት በችግር ምክንያት
ኑሮ የከበዳቸው፣ ትዳር መያዝ ያልቻሉ ሰዎች
ናቸው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች
የሚገኙ የእረኛ ግጥሞች መልዕክት የማስተላለፍ
ዘዴያቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከስነ ቃልነት ባለፈ
በህትመት ተዘጋጅተው ቢሰነዱ መልካም ነው።
ደሥሚይል ነው
ReplyDelete