Translate/ተርጉም

Tuesday, October 30, 2018

አርሲ ያፈራት የዲፕሎማሲ ሻምፒዮን



አርሲ ያፈራት የዲፕሎማሲ ሻምፒዮን
ጽጌረዳ ጫንያለው
ካናዳንና ኢትዮጵያን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በባህልና በፖለቲካው መስክ እንዲተሳሰሩ ካደረጉ አምባሳደሮች መካከል አንዷ ናቸው። የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል፤ የዓለም አቀፍ ሴት አምባሳደሮች ማህበር ጸፊና የአፍሪካ ሴት አምባሳደሮች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛም ነበሩ። በመምህርነትም እውቀትን ዘርተዋል። የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አምባሳደር ብርቱካን አያኖ። ከይወታቸው ብዙ የምንቀስማቸው ቁም ነገሮች አሉና እንካችሁ ብለናል።
ልጅነት

ትውልዳቸው ኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ አሰላ ዞን ጦሳ ወረዳ ነው። አባታቸው አበራ ኤልቦ ይባላሉ። ከእርሳቸው ጋር ባለመኖራቸው በአያታቸው ስም ነው የሚጠሩት። ብርቱካን አያኖ ዳዲ በመባል። እስከ ስድስት ዓመታቸው በእናት አባታቸው ቤት የቆዩ ሲሆን፤ ስድስት ዓመታቸው ሊጠናቀቅ አቅራቢያ አያታቸው ጋር እንዲያድጉ ወደ ጥዬ ወረዳ ሄዱ። በዚያም እንደማንኛውም የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ልጅ በቤተሰብ የታዘዙትን እየሠሩ አደጉ።

አካባቢው ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩበት፤ የሃይማኖት ልዩነት የሌለበት በመሆኑ ሁሉም በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ይኖራሉ። እርሳቸውም ያንን ባህልና ወግ ይዘው በማደጋቸው ከማንም ጋር ልዩነት ሳይኖራቸው ጊዜውን እንዲያሳልፉ ሆነዋል። እንደውም ጎረቤቶች ሲቆጧቸው በእሽታ ያልፋሉ፤ ቁጣቸውንም ያከብሩታል። «ለዛሬ ማንነቴ መሰረቱ የጎረቤቶቻችን ቁንጥጫና ፍቅር አሰጣጥ ነው» ይላሉ። የእርስ በርስ ኑሯቸውን እንዳጠናከረው፤ ማህበረሰቡን እንዳይዘነጉት እንዳደረጋቸው ለማውሳት። በተለይ በዓላት ሲሆኑ ከዚያ አካባቢ መለየት ችግር እንደሚሆንባቸው ያስታውሳሉ።
«የአያት ልጅ ቅምጥል» የሚለው ነገር በአምባሳደር ብርቱካን ቤተሰቦች ዘንድ አይሠራም። ያው የሚፈልጉት ነገር ይሟላላቸዋል እንጂ እንደፈለጉ ከቤት መውጣት በፍጹም አይፈቀድላቸውም። በተለይም ከሴትነታቸው ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች ይገደቡባቸዋል። በዚህም አያታቸው ጋር ሳሉ እንደእድሜ እኩዮቻቸው ሳይጫወቱ ያሳለፉት ጊዜ ይበዛል። በዚህም «የልጅነት ጊዜዬን በሚገባ ተጫውቼ ያደኩት እናት አባቴ ጋር ሆኜ ነው» ይላሉ።
አምባሳደር ብርቱካን በልጅነታቸው አርቲስት ወይም ጋዜጠኛ መሆንን ይፈልጉ ነበር። ይወት በሌላው መንገድ መራቻቸውና በሌላ ሙያ ላይ ተገኙ እንጂ። ሆኖም ግጥሞችንና ሌሎች መጣጥፎችን እየጻፉ ለኦሮምኛ ሬዲዮ ጣቢያ እየሰጡ የጋዜጠኝነትና የኪነጥበብ ጥማታቸውን አስታግሰዋል። በቅርብ የሚያገኟቸውን መምህራንን መሆንንም ይሹ ነበር። እናም እንደቀደመው ሳይሆንባቸው ሙያው ላይ መቆየት ችለው ነበር።
ሯጭ መሆን ከመፈለጋቸው አንጻር ደግሞ በኦሮምኛ «ሲንቢሮ» በአማርኛ «ወፌ» የሚል ቅጽል ስም እስኪወጣላቸው ድረስ በሩጫ ጉብዝናቸውን አስመስክረው ነበር። የአርሲ ልጆች ብዙዎቹ በሩጫቸው እንደሚታወቁ ለማንም የተሰወረ አይደለም። የእርሳቸው ግን በቤተሰብ እገዛ ያልተደገፈ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። በብዙ ጫና ውስጥ ሆነው እየተደበቁ ነበር ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጥሩት። በዚህም በሩጫው አካባቢያቸውን ሲያስጠሩ እስከ ስምንተኛ ክፍል ቆይተዋል።
አገርን ከማስጠራትም በላይ ራሳቸውን የሚያሳውቁበት እድል ተፈጥሮላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ተፈላጊነታቸው ቢያይልም፤ እርሳቸው ግን የማይጋፉት ነገር አስቆማቸው። ቤተሰብ «ትምህርትሽን ይጋፋዋልና መሮጥ የለብሽም» የሚል ውሳኔ አስተላለፈባቸው። «ይህ በክፋት የተደረገ አልነበረም። ትኩረቴ ትምህርቴ ላይ እንዲሆን በመፈለግ የመጣ ነው» የሚሉት ባለታሪኳ፤ በወቅቱ የቤተሰብን ሃሳብ መቃወም አይቻልምና ፍላጎታቸውን ተቋቁመው ከሩጫው ዓለም ለመራቅ ተገደዱ። በዚህም የሩው ህልም ዳር ሳይደርስ ተጨናገፈ።
ሩጫውን ሲያቆሙ ለወረዳ ተመርጠው ትልቅ ደረጃ የሚደርሱበት መስመር ላይ ነበሩ። አሁን ላይ ሆነው ሲያስታውሱት በጣሙን ይቆጩበታል። አቅማቸውን የሚያውቁ መምህራንም በወቅቱ ቅሬታ ተሰምቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። «ቤተሰብን ማን ይሟገታል፤ የእኔ እጣ እንዳይገጥማቸው አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁም» ይላሉ። ቤተሰብ የልጆቹን ፍላጎት መግታት የለበትም፤ ፍላጎታቸውን ለይቶ ሊያበረታቸው ይገባል። ከዚህ በኋላ ነው ውለታ አለባችሁ ሊሏቸው የሚያስፈልገው።
የእንግዳችን የአምባሳደር ብርቱካን ሌላው ልዩ ተሰጥኦ የቅርጫት ኳስ የመጫወት ብቃታቸው ነው። ይህም ቢሆን በቤተሰብ ፍላጎት የተጨናገፈ ነበር። ልምምዱና ጨዋታው ከትምህርት በኋላ ይመጣል ይባላሉ። እንደውም መሸት አድርገው ሲመጡ «የት አመሸሽ?፤ ሴት ይህንን ማድረግ የለባትም፤ ከማን ጋር ነው እስካሁን የቆየሽው? ወዘተ» የሚሉ ጥያቄዎች ይነጉዱባቸዋል። ስለዚህ አማራጫቸው ፍላጎታቸውን መግታት ብቻ ሆኖ ቀረ።
አያት ያበጀው ...
አያታቸው አያኖ ዳዲ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ባይሆኑም ለልጆቻቸውም ሆነ ለልጅ ልጆቻቸው ትምህርት ግን አይቦዝኑም። በጥሩ ሁኔታ መማር እንደሚገባቸው ያምናሉ። በዚህም ከክፍል ክፍል የሚዘዋወሩበትን ውጤት ለማየት ሳይቀር ተራራ እየወጡ ይጠባበቃሉ። በተለይ ሰኔ 30 ሲደርስ የልጅ ልጃቸውን ውጤት ለማየት ቀድመው እንደሚጠብቁ ባለታሪኳ ያስታውሳሉ።
አንደኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት መሰረተ ትምህርት ሲማሩ በክፍል ውስጥ መድረክ ላይ ወጥተው «የኢሠማኮ ተልኮ ይሳካል» ማለታቸውን ከመምህሮቻቸው ሰምተው የመከሯቸው መቼም እንደማይረሳቸው የሚናገሩት አምባሳደር ብርቱካን፤ «ትርጉሙን ሳታውቂ ለምን ተናገርሽሲሉ እንደገሰጿቸውና እርሳቸውም ከዚያ በኋላ እርግጠኛ ያልሆኑበትን ነገር እንዳይናገሩ እንደሆኑ አጫውተውናል። እስካሁን የማያውቁትን ነገር ለመናገር እንደማይደፍሩ ሲያወሱም «በማውቀው ነገር እስከጥግ ድረስ እከራከራለሁ፤ የማላውቀውንም ለማወቅ እጥራለሁ፤ ሆኖም የማላውቀውን ለመናገር ግን አልደፍርም። ይህ ደግሞ አዋቂነቴን ጨምሮልኛል» ይላሉ።
የአምባሳደር ብርቱካን አያት ከማረፋቸው በፊት ለልጃቸው (ለአምባሳደር ብርቱካን አጎት) አደራ የሰጡት የትምህርታቸውን ጉዳይ ነው። «ተምራ ለወግ ማረግ እንድታበቃት፤ ምንም ችግር በትምህርቷ እንዳይገጥማት አደራ» ብለውላቸዋል። በዚህም የእርሳቸውን ቃል ማክበር ለውጤት አብቅቷቸዋል። 
 
አንከራታቹ ትምህርት
አምባሳደር ብርቱካን፤ የመጀመሪያ ትምህርታቸውን አርሲ ውስጥ ጦሳ ወረዳ ጎንዴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት። በዚህም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይይዙ ነበር። ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ወደ አሰላ ከተማ በመሄድ አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነበር ውጤታቸው መቀነስ የታየበት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቤት ተከራይተው በእግራቸው ረጅም ርቀት ተመላልሰው መማራቸው ነበር። በተለይም የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ የመጨረሻ ፈተና ወስደው በእግራቸው በመጓዝ ላይ እያሉ ያጋጠማቸው የጠለፋ ሙከራ ትምህርት ቤቱን ለቀው ወደሌላ አካባቢ እስከመዘዋወር አድርሷቸው ነበር።
አምባሳደር ብርቱካን ከአስር እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት አጎታቸው በሚኖርበት ባሌ ሮቢ ከተማ ነው። ምክንያቱም ከዘጠነኛ ክፍሉ የጠለፋ ሙከራ በኋላ የአምባሳደር ብርቱካን አያት በዚያ እንዲቆዩ አልፈለጉም። በዚህም «ከትምህርትሽ የሚበልጥ የለም። ስለዚህ ተምረሽ አኩሪኝ» ሲሉ አደራ ሰጥተው ባሌ ላኳቸው። ስለዚህ እርሳቸውም አደራ በላ ላለመሆን ሮቤ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ከአስረኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሩ። ጥሩ ውጤት በማምጣትም በዚያው በሮቤ መምህራን ማልጠኛ ተቋም ገብተው በመምህርነት ሙያ ተመረቁ። ከቦታ ቦታ ሲያንከራትታቸው የነበረው የትምህርት ጥማትም በመምህርነት ተቋጨ።
አምባሳደር ብርቱካን ጥቂት ዓመታትን እንዳስተማሩ ሌላኛውን የልጅነት ፍላጎት ለማሟላት ወደ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ። «ምን ትፈልጊያለሽ፤ ምርጫሽ ምን ይሁን» ሲባሉም አርቲስት ወይም ጋዜጠኛ መሆንን እንደሚፈልጉ ገለጹ። ሆኖም ይህ የትምህርት መስክ የለም በመባላቸው ምርጫቸውን የህግ ትምህርት ላይ አድርገው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አጠናቀቁ። ከዚያም በሌላ ጊዜ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዛው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲ ኤንድ ኢንተርሽናል ሪሌሽን ተመረቁ፤ ወደ ቤልጅም ብራስልስ በማምራትም ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በገቨርናንስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፖሊሲ ተማሩ። ከዚያ በኋላም የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችን ቢወስዱም የሥራ ሁኔታቸው ለመማር እድል ስላልሰጣቸው ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አልቀጠሉበትም። ይሁን እንጂ የመማር ፍላጎቱ እንዳላቸው አልሸሸጉም።
ሴትነት እና የአካባቢ ፈተና
በአካባቢው ሴት መሆን ፈተና ውስጥ የወደቀበት ወቅት ነበር እርሳቸው ሲማሩ። ከቤተሰብ ጫና በላይ በአካባቢው ያለው ባህላዊ አኗኗር ሴት ልጅን በእጅጉ ይፈትናታል። በተለይ አደግ ብላ ትምህርቷን መከታተል የጀመረች ሴት ነገሮችን በቀላሉ መቋቋም አትችልም። በየመንገዱ የጠለፋ ሙከራ ይደረግባታል። ከተሸነፈች ደግሞ ያለፈቃዷ ተድራ የቤት እመቤት ሆና ትቀራለች። በዚህ አካባቢያዊ ተፅእኖ ውስጥ ካለፉት መካከል ደግሞ የአምባሳደር ብርቱካን ሦስት እህቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እርሳቸውም ቢሆኑ የጠለፋ ሙከራ ከተደረገባቸው መካከል አንዷ ነበሩ። ይሁንና ስፖርተኛ መሆናቸው ጠቅሟቸው እየተጎተቱ ከተወሰዱበት ለማምለጥ ችለዋል። የአካባቢው ማህበረሰብና ጓደኞቻቸው ደግሞ በስፖርተኝነት ጥንካሬያቸው ላይ ተጨምሮበት ችግሩን በጊዜው እንዲያልፉት አድርጓቸዋል። ነገር ግን የሴቶች ጠለፋ በዚህ ብቻ የሚገታ አይደለምና ቀጣዩ ታሪክ በእንግዳችን ላይ ተከስቷል። ይኸውም በአካባቢው ልማድ አንድ ወንድ የጠለፋ ሙከራ አድርጎ ካልተሳካለት ተበለጠ ወይም ተሸነፈ ተብሎ ይታመናልና በሽማግሌ መጠየቅና ልጅቷን መውሰድ ይኖርበታል። ያለዚያ ግን ሚስት እንደማያገኝ ይታመናል። ስለዚህም ጠላፊው በተደጋጋሚ ሽማግሌዎችን መላኩን ተያያዘው። ቤተሰብ አይሆንም ማለት ባህሉ አይፈቅድለትም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ አንድም አካባቢውን እንዲለቁ ማድረግ አለያም መዳር ነው። በዚህ ግራ የተጋቡት አያትም አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ለልጃቸው አደራ ሰጥተው ሳይወዱ በግድ ከይናቸው እንድትርቅ አደረጉ።
ሌላው በዚህ አካባቢ የሚኖሩ እንስቶች ፈተና «ይህ አይደረግም፤ ይህ መሆን አለበት» የሚሉ ማህበረሰባዊ ህጎች መብዛታቸው ነው። እናም አምባሳደር ብርቱካንም በዚህ ህግ የመተዳደር ግዴታ አለባቸውና ከጥምቀት በዓል በስተቀር የትም መሄድና መጫወት በቤተሰቡ ዘንድ ክልክል ከሆነባቸው መካከል አንዷ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለአዲስ ዓመት አበባየሆሽ እንዲጫወቱ አይፈቀድላቸውም። ይህ ደግሞ በጣሙን ያበሳጫቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። «የአያት ልጅ ቅምጥል» የሚለው ነገር በአምባሳደር ብርቱካን ቤተሰቦች ዘንድ እንዳይሠራ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነበር።
ብዙኃኑ ሴቶች ሴትነት ማለፍ ያለበት በዚህ አይነት ባህል እንደሆነ አምነው ተቀብለው ስለሚኖሩ አምባሳደር ብርቱካንም ላይ ከአክስቶቻቸው ሳይቀር ብዙ ቁጥጥር ይደርጉባቸው ነበር። እናም አያታቸው ጋር ሳሉ እንደእድሜ እኩዮቻቸው ሳይጫወቱ ያሳለፉት ጊዜ ብዙ ነው። ከተማ ባሌ ሮቤ ከገቡ በኋላም ቢሆን ወንድማቸው ስለሚያስተዳድራቸው ብዙ የመጫወቱ እድል አልነበራቸውም።
በእቅድ መወፈር
አምባሳደር ብርቱካን ዳኝነት እየሠሩ ሳለ ነበር መወፈር እንዳለባቸው የወሰኑት። ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች ሲያዩዋቸው «ክቡር ፍርድ ቤት» ማለታቸውን ትተው «ልጄ» እያሉ ያወሯቸዋል። በተለይ አንድ ቀን የገጠማቸው ነገር ይህንን እንዲያስቡት አስገድዷቸዋል። ሁነቱ እንዲህ ነው፤ እርሳቸውና ሌላ ዳኛ አብረው ተቀምጠው ክስ በመስማት ላይ ናቸው። አንዲት አዛውንት ገብተው ከሥራቸው የነበረችውን ዳኛ በአካል ስትታይ ግዙፍ በመሆኗ «ክቡር ፍርድ ቤት» እያሉ ሲያወሩ እርሳቸውን ግን «ልጄ» ይሏቸዋል።
በዚህ የተናደዱት አምባሳደር ብርቱካንም «ለምን እንዲህ ይላሉ፤ ያሉት ፍርድ ቤት መሆኑን ዘነጉበማለት ተቆጡ። አዛውንቷም «ልጅ ስለሆንሽ ነዋ እንዲህ ያልኩት» ብለው መለሱላቸው። ምላሻቸው ያልተዋጠላቸው አምባሳደር ብርቱካንም ግርማ ሞገስን ፍለጋ አቅደው መወፈር ጀመሩና ተሳካላቸው።
ኑሮ በካናዳ
ካናዳ ለአምባሳደር ብርቱካን የመጀመሪያ የው አገር ጉዟቸው ማረፊያ ነበረች። በተለይ ደግሞ የሰበሰቧቸው መረጃዎች እዚያ ሄደው ካገኟቸው መረጃዎች ጋር የሚለያዩ ስለሆኑባቸው ተቸግረው እንደነበር አይረሱትም። በአገር ውስጥ የተሰጣቸው ሥልጠናና በካናዳ የተሰጣቸው ሥልጠና የተራራቀ መሆኑ ሌላው ፈተና ነበር። በተለይ የአገር ውስጡ ሥልጠና ለአገር ገጽታ ሲባል ሁሉ ነገር ጠንከር ተደርጎ ነበር የተሰጣቸው። በሙሉ መረጃ የተደገፈም አልነበረም። ይህ ደግሞ ከአገር ወጥተው ለማያውቁት አምባሳደር ብርቱካን እንዴት እንደሚኖሩና እንዴት ስኬታማ ሥራ እንደሚሠሩ አሳስቧቸው ነበር።
መጀመሪያ ሲላኩ ዲፕሎማት ሆነው እንዲያገለግሉ ነበር። በዚያ ላይ የኢትዮጵያንና የካናዳ ባህልም ሆነ አኗኗር በእጅጉ ይራራቃል። ስለዚህ ለአገራቸው ሲሉ ከብዙ ችግሮች ጋር መጋፈጥ እንዳለባቸው አምነዋል። የመጀመሪያ ጊዜ ሲገቡ ቅዝቃዜውና ምግቡ በእጅጉ አስቸግቸው ነበር።። በኢትዮጵያ በዚያ ደረጃ በረዶ አይጥልም፤ ቅዝቃዜውም አጥንት ሰርስሮ የሚገባ አይደለም። እናም ቢሮ ሲገቡ ወቅቱ ግንቦት ቢሆንም ኮፍያ ያለው ካፖርትና ጓንት አጥልቀዋል። በነዋሪው ዘንድ ግን ይህ አይነት አለባበስ በሞቃታማ ጊዜ አይደረግም ነበር። ወደ መሥሪያ ቤት መጓዝ ሲጀምሩ ያገኟቸው ኢትዮጵያዊያን የሥራ ባልደረቦቻቸው «አታሰድቢን ቢያንስ ኮፍያሽን አውልቂ» ያሏቸውን አይረሱትም።
በምግቡም ቢሆን ለመልመድ በእጅጉ እንደተቸገሩ ያስታውሳሉ። የሆነው ሆኖ በጥቂት ቀናት ውስጥ ካናዳን መልመድ ጀምረዋል። አራት ዓመታትን በዲፕሎማትነት፤ አራት ዓመታትን በአምባሳደርነትም አገልግለውበታል። በእርግጥ በመሃል አገራቸው ተመልሰው የው ጉዳይ ዓለም አቀፍ ዲፓርትመንት ውስጥ በመግባት በሙያቸው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ሠርተዋል። ግን መልሰው ካናዳ እንዲሠሩ ተልከው ነበርና የለመዱትን እንዲተገብሩት መሆን ችለዋል። ቆንስላው ተዘግቶ እንደአዲስ ኤምባሲው ሲከፈት እንዴት ታደርገው ይሆን? ቢባልም እርሳቸው ግን በጥሩ ሁኔታ ከፍተው የተሻለ ውጤት አስመዝግበውበት ነበር።
በእርግጥ በእርሳቸው የእድሜ ክልል ውስጥ ሆነው አምባሳደር የሆኑ ጥቂቶች ናቸውና አንዳንድ ችግሮች አይገጥሟቸውም ማለት አይቻልም። በመሆኑም ሪሴፕሽን ሲሄዱ እንኳን ከእርሳቸው ይልቅ ባለቤታቸውን ቀድመው ሰላም ይሏቸዋል። በግዝፈትም ሆነ በእድሜ ብዙዎቹ የአፍሪካ አምባሳደር ሴቶች ይበልጧቸዋል። እናም እርሳቸውን ብዙዎች አምባሳደር ናቸው ለማለት ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም ጠንካራ ስለነበሩ በውጤታማነት አልፈውታል።
ገጠመኝ
ወደ ካናዳ ለመጓዝ ከተሰጣቸው ሥልጠና ጋር ተያይዞ ነው ገጠመኙ የተፈጠረው። ሥልጠናው የአገር ገጽታ እንዳይጠፋ በሚል «በምንም መልኩ ፖሊስ ሊያስመጣ የሚችል ተገቢ ያልሆነ ተግባር መፈጸም የለባችሁም» የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በዚህም ምንም አይነት ችግር ላለመፍጠር ይጠነቀቃሉ። የካናዳ ሥልጠና ደግሞ የእሳት አደጋም ሆነ በቤቱ ላይ ችግር የሚስተዋል ከሆነ በቤቱ ውስጥ አላርም ስላለ ፖሊስ ፈጥኖ ይደርስላችኋል የሚል ነበር። ሁለቱን ማስታረቅ ያልቻሉት እነአምባሳደር ብርቱካን አንድ ቀን እንዲህ አጋጠማቸው።
በውው ዓለም ሴትም ሆነ ወንድ በእኩል ደረጃ ምግብ ያዘጋጃልና ባል ምግብ ለመሥራት ማዕድ ቤት ይገባል። ከዚያም አንዷ የስጋ ቁራጭ እሳቱ ውስጥ ገባች። ጭሱም ተንቦለቦለ። አላርሟም ጭሱን ተከትላ ጮኸች። በዚህ የተደናገጡ ባልና ሚስትም ግራ በመጋባት ፖሊስ ሳይመጣ በሚል የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰዱን ተያያዙት። በተለይ አምባሳደር ብርቱካን ከመደንገጣቸው የተነሳ መጥበሻውን አንስተው ፍሪጅ ውስጥ አስገቡት። ባል ደግሞ መስኮቱን ከፍቶ ማናፈሱን ቀጠለ። ጭሱም የተከፋፈተለትን መስኮት በመከተል በመውጣቱ አላርሟ ጸጥ አለች።
በዚህ ሁሉ ጭንቀት ውስጥ ሆነውም የፖሊሱን መምጣትና ምን ማለት እንዳለባቸው ማሰባቸውን አላቆሙም። ቢጠብቁ ቢጠብቁ የሚመጣ ፖሊስ አልነበረም። ከዚያ አምባሳደር ብርቱካንም ሥልጠና የወሰዱበት ቦታ ደውለው «አላርም ስትጮህ ፖሊስ ይመጣል ብለው አልነበር ለምን አልመጣም» ሲሉ ጠየቁ። ምላሹ ግን በጣም ትልቅ አደጋ ሲደርስና ከአደጋና ዝግጁነት ፖሊሶች ጋር የሚገናኘው ኮሪደር ላይ ያለው አላርም ሲሰበር እንጂ የቤቱ አላም ሲጮህ አይደለም ፖሊስ የሚመጣው የሚል ነበር። የቤቷ አላርም ጥቅም መቀስቀሻ ወይም ሰዎችን ማንቂያ ብቻ ሆና ተገኘች።
ከዚያ በኋላ ላለመሸወድ ብዙ መረጃዎችን በትክክል እስኪረዱት መጠየቅና እርሳቸውም በማንኛውም ጉዞና ሁኔታ ውስጥ መረጃ ሲሰጡ ሙሉ ማድረግ እንዳለባቸው እንደተማሩበት አጫውተውናል።
የሥራ ስኬት
በባሌ ጋሰራ ወረዳ ደንበል ሚስራ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር የመጀመሪያ ሥራቸውን በመምህርነት ሙያ የጀመሩት። አምስት ዓመታትም በዚህ ሙያ በተለያየ ቦታ እያስተማሩ ቆይተዋል። ከዚያ የህግ ትምህርት ተመርቀው በአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት አገለገሉ። ሆኖም በሙያው የመቆየቱ ፍላጎት ቢኖራቸውም ዲፕሎማት መሆን እንዳለባቸው ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተነገራቸው።
«ፍትህን በሴቶች ላይ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። የእኔ እህቶችን ጨምሮ ያለው የፍትህ ጫፍ መስተካከል አለበት። ስለዚህም መቀጠል የምፈልገው ዳኝነቱ ላይ ነው» ቢሉም ክልላቸው ትልቅ ኃላፊነት ጥሎባቸዋልና ዳኝነቱን ለመተው ተገደዱ። ለዲፕሎማትነት ከተመረጡ ሠራተኞች መካከል በመሆንም ከሦስት ወር ሥልጠና በኋላ ወደ ካናዳ አቀኑ። እየተመላለሱም ቢሆን ስምንት ዓመታትን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ሠሩ።
በካናዳ እንደሄዱ በዳያስፖራ ዘርፍ የመጀመሪያ ደረጃ ጸሀፊ ሆነው ሠርተዋል። ከዚያ አማካሪ ሆነው ሥራቸውን ቀጠሉ። ወደ አገር ውስጥ በመመለስ የዓለም አቀፍ ህግ ስምምነቶች ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው የሠሩ ሲሆን፤ የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ሆነውም አገልግለዋል። ዳግመኛ ካናዳ ሲላኩ ደግሞ አምባሳደር ሆኑ። ከአምባሳደርነቱ ጎን ለጎን ሌሎች ሀገራዊ ሥራዎችንም ያከናውኑ ነበር። ለአብነት የምስራቅ አፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን ምክትል ዲን፤ የሴት አምባሳደሮች ማህበር ጸፊ፣ የአፍሪካ ሴት አምባሳደሮች ፕሬዚዳንት፣ የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ ማህበር አመራር ሆነው አገልግለዋል። አሁን ደግሞ በው ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ሽልማት
በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል። ይሁንና የማይረሱትና የሚደሰቱበት ሽልማታቸው በተለያየ መድረክ ከሚያቀርቧቸው ሀሳቦችና ንግግሮች በመነሳት «ሴንሸ ሞን» ከሚባል ካናዳ ከሚገኝ ድርጅት «ፒስ ድሪመርስ» የተሰኘ ሽልማት መቀበላቸውን ነው።
የሚያተጋው ባል
ባለቤታቸው ዮሐንስ አድማሱ ይባላሉ። በትዳር የተገናኙትም በባሌ ጋሰራ ወረዳ በመምህርነት በመሥራት ላይ ሳሉ ነው። በሥራ ትጋታቸው በጣም ያደንቋቸውና ያከብሯቸው ነበር። የቅርብ መካሪያቸውም እርሳቸው ነበሩ። እናም ይህ ቅርርባቸው በፍቅር ተቀየረና ለጋብቻ አደረሳቸው። አምባሳደር ብርቱካን ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት «እንኳንም አገባሁት» ይላሉ። ምክንያቱም «ያለ እርሱ እዚህ ደረጃ መድረስ በፍጹም አልችልም፤ ሁልጊዜ በሥራዬ እንድበረታና ከሥራ ሰዓት ውጪ እንድሠራም ይገፋፋ ነበር፤ ሥራ ይቀይራል እንጂ አያደክምም የሚል እምነት ስላለው በሥራ እንድተጋ ይፈልጋል» በማለት የባለቤታቸውን አጋዥነት ይመሰክራሉ።
ከፍቷቸው እንኳን ሲመጡ ቀለል አድርገው በማጽናናትና «ይህ በዚህ መታረቅ ይችላል» በሚል መፍትሄ በመጠቆም እንደሚደግፏቸውም ይገልጻሉ። በተለይ ለሥራቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጡና ከሁሉም በላቀ መልኩ ሥራቸውን እንዲያከብሩ ከሚያግዟቸው መካከል ባለቤታቸው የመጀመሪያ መሆናቸውን ይመሰክራሉ። ሁለት የሚያሳድጓቸው ልጆቻቸውም የአባታቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ይመክራሉ።

No comments:

Post a Comment