የፊልም
ቅድመ ግምገማ መነሳት
-«ከድጡ
ወደ ማጡ»
እንዳይሆን
ሊድያ
ተስፋዬ
ባሳለፍነው
ሳምንት በኪነጥበቡና ሥነጥበቡ ዘርፍ መነጋገሪያ
ጉዳይ ሆኖ የነበረው የአዲስ አበባ ባህልና
ቱሪዝም ቢሮ በተለይ በፊልም እና በቴአትር
ላይ ይደረግ የነበረው ግምገማ ይነሳል ወይም
ይቀራል ማለቱ ነው። ይህን ዜና ተከትሎ «እልል»
ያሉ እንዲሁም
«አይደረግም»
በሚል ሃሳብ
የገባቸው በርካቶች ናቸው።
ዜናው
በመጀመሪያ ደረጃ «እስከዛሬም
ሳንሱር ነበር እንዴ?»
ብለን እንድንጠይቅ
ይጋብዛል። እናም «ቅድመ
ምርመራ እያለ ነው ከኢትዮጵያዊነት የተፋቱና
የማይመጥኑን ፊልሞች ለእይታ የቀረቡት?»
ብለንም ልንጠይቅ
እንችላለን። ታድያ ቅድመ ምልከታው እያለ
የተሠሩ በርካታ ፊልሞች እንደዛ ዓይነት ስሜትን
ካጋቡብን ጭራሽ ቅድመ ምልከታው ሲቀር ምን
ሊውጠን ነው? ይህም
ሌላ ጥያቄ ነው።
የቢሮው
ውሳኔ እና እርምጃ እንደ እኔ እይታ «ከድጥ
ወደ ማጥ» የሚሉት
ዓይነት ነው። እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ
ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ፊልሞችን ሲገመግም ብቻ
ሳይሆን በሳንሱር መቀስ ሲቆርጥ እንደከረመ፤
ግምገማውን አንስቻለሁ ማለቱ ይናገራል።
ጉዳዩን በሚመለከት ካናገርኳቸው ባለሙያዎች
መካከል በቢሮው የባህል አገልግሎቶች ብቃት
ማረጋገጥ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ደኑ በዚህ ላይ
አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እርሳቸው
እንዳሉት ምንም እንኳ ግምገማው ከባህል
እሴቶች፣ ከጾታ፣ ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣
ወጣቱን ሊጎዱ ከሚችሉ አላስፈላጊ ሁኔታዎች
ከመጠበቅ አንጻር የሚካሄድ ቢሆንም በመካከል
የፖለቲካ እይታዎችም ነበሩት። በዚህም እይታ
ርዕሳቸው እንዲቀየር እንዲሁም ትዕይንቶችን
እንዲቀይሩ የታዘዙ አልያም ለእይታም ሆነ
ለስርጭት ፈቃድ ያለተሰጣቸው ፊልሞች እንደነበሩ
በተለያየ ጊዜ ሰምተናል።
በቀደመው
ጊዜ አሠራሩ እንዲህ ነበር፤ ፊልሞች ወደ ቢሮው
ይቀርባሉ። ቢሮው ፊልሞቹን ከተጠቀሱት ነጥቦች
አኳያ ገምግሞ የማሰራጫና የማሳያ ፈቃድ
ይሰጣቸዋል። ፊልም ሠሪዎቹ ወደተለያዩ የግል
እና የመንግሥት ሲኒማ ቤቶች ፈቃዱን ይዘው
ይሄዳሉ። ከዚህ በኋላ ግን አዲስ አሠራርና
መመሪያ እስካልመጣ ድረስ ፊልሞች ተሠርተው
ቀጥታ ወደ ሲኒማ ቤት ይገባሉ ማለት ነው።
ፊልም
ሠሪ እና የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር
ፕሬዝዳንት ነው፤ ቢንያም ዓለማየሁ። «ሳንሱርን
አንደግፍም ግን ቀድመው መሠራት የነበረባቸው
ነገሮች ሳይሠሩ ግምገማው መነሳቱ ለሲኒማ
ኢንዱስትሪው ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም»
ሲል አስተያየቱን
ይሰጣል።
ለዚህ
ምክንያቱ የፊልም ባለሙያዎች እዛም እዚህም
ተበትነው መገኘታቸውና ወደ አንድ መምጣት
አለመቻሉ መሆኑን ነው ቢንያም የሚናገረው።
ብዙ ኃላፊነት የሚሰማቸው የፊልም ባለሙያዎች
እንዳሉ ሁሉ ምንም ስሜቱም እወቀቱም የሌላቸው
መኖራቸውንም ይጠቅሳል። «እነዛ
ሰዎች በሚያጠፉት ጥፋት በአጠቃላይ የፊልሙ
ማኅበረሰብ ነው የሚወቀሰው። ግን ከዚህ ሁሉ
ባሻገር እንደ ማኅበረሰብ የሚጠፋው ጥፋት
ከባድ ይሆናል» ይላል።
እንደቢንያም
ገለጻና እንደግል አስተያየቱ ከዚህ ውሳኔ
በፊት መደረግ የነበረበትና ሊወሰድ የሚገባው
እርምጃ አልተወሰደም። ይህም፤ ውሳኔው
አድናቆትን ወይም ጭብጨባን ለማግኘት የተደረገ
ያስመስለዋል ባይ ነው። እዚህ ላይ ቢሮው
ሲያከናውን የቆየው የግምገማ አሠራር የሳንሱር
መልክ ይዞ እንደተንጸባረቀ ገልጾ ይህንንም
ለመቃወም ማኅበራቱ ያደረጉትን ጥረት ሳያስታውስ
አላለፈም።
«ቅድመ
ምልከታ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ። የበሰለ
የፊልም ባለሙያ እስክናበዛ ድረስ እና ማኅበረሰቡ
ነገሮችን በራሱ እይታ መመዝን እስኪችል ድረስ
ሙያዊ ቅድመ ምልከታ መኖር አለበት። ግን ይህን
ነገር ማን ይሥራው?
የሚለው ነው
ጥያቄው» ይላል።
ሥራው
በእርግጥ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሆን አለበት
ማለት አይደለም። ቢንያም እንዳለውም ከውሳኔው
በፊት ቢያንስ አንድ ቡድን ተቋቁሞ ኃላፊነቱን
ለአንድ አካል መሰጠት ነበረበት። «አሁንም
እኛ በአፋጣኝ ይህን ነገር መፍትሄ ማምጣት
አለበት ብለን ስለምናስብ ከእነርሱ ጋር
በመነጋገር መፍትሄ እንዲኖር እንሠራለን
ብለን እናምናለን»
ብሏል። ዘርፉ
እንዳይባክንም ይህ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ
ሥራ መሆኑን ተቁሟል።
ከላይ
በርዕሱ እርምጃውን «ከድጥ
ወደ ማጥ» ብለነዋል።
ድጡ የቱ ነው ማጡስ?
ድጡ እንዲህ
ነበር፤ መጀመሪያውኑ ቢሮው ሲያከናውን የቆየው
ግምገማ የሳንሱር መቀስ ነበረው። የፖለቲካ
አስተሳሰቦችን የሚከትፍና ብዙዎችን ያስቀየመም
ነበር።
ቅድመ
ምርመራው በግራም ነፈሰ በቀኝ ሳነሱር እንደሆነ
ይታመናል። እዚህ ላይ የተለያዩ ነገሮችን
ግን ማገናዘብ ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ ኃላፊነት
የሚሰማቸውንና በሙያው ብቃት ከፍ ያለ ደረጃ
የደረሱትን ላይመለከት ይችላል። ነገር ግን
አንደኛ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ለሙያው
ፍላጎትና ፍቅር ኖሯቸው የሚሠሩትን በእውቀት
ለመደገፍ የሠራው ሥራ የለም። በዛም ላይ
የማኅበራት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር አልሆነም።
ሁለተኛ ነጥብ ደግሞ ምን ያህል ኃላፊነት
የሚሰማው ባለሙያ አለ?
«ተቋማቱ
ሳይደግፉኝ እንዴት ነው አገራዊ ፊልም የምሠራው?»
የሚል ስንት
የፊልም ባለሙያ አለ?
እነዚህ
ነጥቦች የፊልም ቅድመ ምርመራን መኖር ጥሩ
ያደርጉት ነበር። ቢሮው ግን ይህን ስልጣን
በአግባቡና ዘርፉን በሚጠቅም ብሎም ማኅበረሰቡን
በሚጠብቅ መልኩ ሳይጠቀምበት ቀረ። ይህ ነው
ድጡ፤ እሠራለሁ ያለውን ሥራ፣ ቢሮ ያቋቋመለትንና
ዓላማ እንዲሁም ተልዕኮ የነደፈለትን ሥራ
በአግባቡ ሲሠራ አልቆየም።
ከሁለት
ዓመታት በፊት «አስፈሪ
እየሆነ የመጣው ሳንሱር»
በሚል ርዕስ
እንደጻፈው አስታውሶ የፊልም ባለሙያው ያሬድ
ሹመቴ በማኅበራዊ ድረገጹ የሚከተለውን
አስነብሏል፤ «በኢትዮጵያ
ህገ መንግስት ፈጽሞውኑ የተከለከለው ሳንሱር
የፊልም ሥራዎች ላይ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህንን
ተግባር ህጋዊ ሽፋን አለኝ ቢልም በህገ መንግስቱ
ቀርቷል የተባለውን ቅድመ ምርመራ ተግባራዊ
ማድረጉን ቀጥሏል።
«ሀይማኖትን
ከሀይማኖት፣ ብሔርን ከብሔር የማያጋጭ እንዲሁም
ሌሎች መስፈርቶችን ምክንያት አድርጎ ፊልም
መሥራት ከጀመርንባቸው ጊዜያት አንስቶ ቅድመ
ምርመራ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በነበሩ
ቅድመ ምርመራዎች ሊያስተች የሚችል ብዙም
የሳንሱር መቀስ ባለመኖሩ ፊልም ሠሪዎች
እንደችግር ሳናነሳው ቆይተናል። በአሁኑ ጊዜ
ግን ይህ ተለሳልሶ የቆየው የሣንሱር መቀስ
አሁን አስፈሪ መሆን ጀመሯል። በቅርቡም አንድ
ፊልም ሙሉ ለሙሉ ከእይታ ውጪ አድርጎ ማገዱም
ይታወሳል።...» ይላል።
እንደ
ያሬድ ያሉና ሌሎች የፊልም ባለሙያዎች ኃላፊነት
የሚሰማቸው ናቸው፤ ይህም በተግባራቸው የተገለጠ
ነው። እናም ቅድመ ምርመራውን ያማረሩት
ምርመራው የሚቃኛቸው እሴትን የሚያስጠብቁ
መስፈርቶች ላይ ችግር ተገኝቶባቸው እንዳልሆነ
መገመት ቀላል ነው። ስለዚህ ቅድመ ምርመራው
በታሰበለት አሠራርና መንገድ ሲሄድ እንዳልነበር
ማወቅ ይቻላል።
ማጡ
ደግሞ አሁን የተከሰተው ነው። የፊልሞች ቅድመ
ምርመራ መነሳት በፊት ሊቀድሙ የሚገቡ ሥራዎች
ነበሩ። ለምሳሌ ብዙዎች የሚያነሱት የፊልሞች
የእድሜ ገደብ ወይም ሬቲንግ ጉዳይ አንዱ ነው።
ይህንን ሥራ ሊሠራ የሚችል አንድም አካል
በሌለበት ማኅበረሰቡን በተወሰነ መልኩም
ቢሆን ሊጠብቅ የሚችልን አሠራር ነቅሎ መጣል
ትክክል ሊሆን አይችልም።
ነገሩ
ሁሉ የቢሮው ውሳኔ የተጠና እንዳይደለ ያሳበቃል።
ለፊልም ያለው አስተሳሰብ ለጋ ነው፣ የፊልም
ትምህርት ቤቶች አልተቋቋሙም። የአውሮፓ
ፊልሞች እንደ አሸን ወደ አገራችን ሲገቡ ሃይ
የሚልና ዘርፉን ጠባቂ የለም፤ ሁሉም በራሱ
ጥረትና ፍላጎት ነው የሚንቀሳቀሰው። የፊልም
ፖሊሲ እንኳን ተግባራዊ እንዲሆን ገና ማስፈጸሚያ
ሰነድ እንዲዘጋጅ ባለሙያዎቹ ውይይት ከጀመሩ
ሳምንት አልሞላም።
ሳንሱር
መኖር የለበትም፤ ግልጽ ነው። ሲደረግ የቆየው
ሳንሱር ከሆነ ቢሮው ሊጠየቅ ይገባል። ነገር
ግን አሠራሩን ማስተካከል እንጂ ፈጽሞ ማስቀረቱ
ሁለተኛውና የባሰው ጥፋት ነው። ከዚህ በተቃራኒው
የሚያስብ ካለ ደግመን እንጠይቅ፤ የፊልም
ባለሙያዎቻችን ምን ያህል ኃላፊነት የሚሰማቸው
ናቸው? ስንቶች
ናቸው ለማኅበረሰቡ ተጨንቀውና ለአገራቸው
ተቆርቁረው ሥራዎችን የሚሠሩት?
ነጻነትን ምን
ያህሎቹ በአግባቡ ተረድተውታል?
ሁሉም ባለሙያ
ይህ ኃለፊነት ቢጫንበት ሊሸከም የሚችል ነው
ወይ?
የቢሮው
ኃላፊና በቅርቡ በቦታው ላይ የተሰየሙት ረዳት
ፕሮፌሰረ ነብዩ ባዬ ለባህል ዘርፍ ምክትል
ቢሮ ኃላፊው ያስገቡት ደብዳቤ ላይ አሠራሩ
እንዲቆም ከማስፈራቸው ባሻገር በደብዳቤው
ማጠናቀቂያ ላይ ያሰፈሩት ነገር አለ። ይህም
ቢሮው ዓላማና ተልዕኮውን ተግባራዊ ለማድረግ
የአቅም ግንባታ እና የክትትል ሥራው የሚቀጥል
መሆኑን ነው።
ይህስ
«ክትትል»
ምን ማለት
ነው? በምን
መልኩ ይሆን የሚካሄደው?
አቶ
ስዮም ተመስገን በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም
ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ናቸው።
ፊልም ከተቀሩት የጥበብ ሥራዎች የተለየ
ባህሪ ያለውና በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት
ተደራሽ መሆኑን አንስተዋል። በተለያየ ዜዴ
ተሠራጭቶ ከተዳረሰ በኋላ መልሶ መያዝ አይቻልም፤
በአጭር ጊዜ ውስጥ ማኅበረሰብን ቅርጽ በማስያዝ
በኩል በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መንገድ
ተጽእኖ ይፈጥራል ብለዋል።
በጉዳዩ
ላይ ለመወያየት መድረክ የመፍጠር ሃሳብ
እንዳለም ነግረውናን። እርሳቸው እንደሚሉት
በባለድርሻ አካላት የተዋቀረ አንድ አካል
ተመሥርቶ ፊልሞች ወደ ሥራ ሳይገቡ ገና በጽሑፍ
ደረጃ እንዲታዩና ሙያዊ ሂስ እንዲሰጥባቸው
ማድረግ ያስፈልጋል።
«ያ
ግን የፖለቲካ እይታዎችን የሚቆርጥና ሳንሱር
የሚያደርግ ሳይሆን በሙያዊ እይታ በየአቅጣጫው
የተሠሩትን ፊልሞች የሚያርቅ ይሆናል ብዬ
ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን ስንል ሰዎች ሃሳባቸውን
በነጻነት መግለጽ አለባቸው ከሚል ህገመንግስታዊ
መብት ጋር የሚጣረስ አይደለም»
ይላሉ።
በዚህ
ላብቃ! የአዲስ
አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደበርካታ ሌሎች
የመንግስት የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች
የሚቀረው ብዙ ሥራ አለ። በእርግጥም በቦታው
የተቀመጡት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ለፊልሙ
ዘርፍ ያላቸው ቅርበት በሌላው ወገን እንዳያዩና
መቅደም ያለበትን ከማስቀደም ገድቧቸው ይሆናል።
ከዚህ ውሳኔ በፊት ስለፊልም ካሰቡ ግን ቢያንስ
በቢሮው የሚተዳደሩ ሲኒማ ቤቶችን በመቃኘት
ሊያስተካከሉ ይገባል የሚል ጥቆመ መስጠት
አፈልጋለሁ። በጉዳዮም ላይ ባለሙያዎችን
ሰብስቦ ማወያየትና ማማከር ሊቅድም ይገባል።
በነገራችን
ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ፊልም ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጊያ ሰነድ ሊዘጋጀ
ነው ተብሏል። የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም
ሚኒስቴር ባለድርሻ ሆኖ ከፍተኛ ሚና በሚወጣበት
በዚህ ፖሊሲ፤ ክፍል ሁለት ቁጥር ሶስት ላይ
«የአገርን
ደኅንነትና ጥቅም የሚጎዱ፣ የማኅበረሰቡና
የወጣቱን ሞራል ስነምግባርና ማኅበራዊ እሴቶችን
የሚያዘቅጡ፣ ለባህል ወረራ የሚያጋልጡ ይዘቶች
ያላቸው የፊልም ምርቶች እንዳይቀርቡ ይረጋገጣል»
ይላል። ይህ
በምን መልኩ ተፈጻሚ እንደሚሆን ጊዜውን ጠብቀን
የምናየው ይሆናል። ኪዘህ በኋላ ግን ኃላፊነቱ
የፊልም ባለሙያዎች ሆኗልና አደራው ለእነርሱ
ነው። ሰላም!
No comments:
Post a Comment