Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

በመጻሕፍት የተገነባ ማንነት


ሕይወት እንዲህ ናት
በመጻሕፍት የተገነባ ማንነት
ሊድያ ተስፋዬ
ሁሉም ነገር በምክንያት የሆነና የሚሆን ነው። የሰው ልጅ በሕይወቱ ያላሰበው ሁነት ባላሰበው መንገድ ሊከሰት ይችላል። ለምን ወደቅሁ? ለምን ተዘነጋሁ? ለምን ታመምኩ? ለምን ተሰደድኩ? ለምን እኔ ላይ? የሚሉ ጥያቄዎችም እንቆቅልሽ ይሆናሉ። ግን ነገሩ የሆነው ለአስደናቂ ውጤት ቢሆንስ? ካለፈ በኋላ ሳይሆን እየሆነ እያለ የነገ ምክንያት የሆኑ ብዙ ክስተቶችን በሕይወታችን እናያለን። በቃ! ሕይወት እንዲህ ናት።
«ኢትዮጵያዊ ከአገሩ ተለይቶ በሰው አገር ቢገኝ እንኳ ኢትዮጵያን በልቡ ይዟት ይዞራል» ይህን ብሂል በእውነት መስታወት ቁልጭ አድርገው ካሳዩን መካከል አንዱ ነው፤ የዛሬው እንግዳችን አቶ ኤልያስ ወንድሙ። በወጣትነት እድሜ ወደተለያት አገሩ የተመለሰው ከ24ዓመታት በኋላ ነው። በአገሩ ከኖረበት ዓመታት በላይ በቆባት አሜሪካ የአገሩን ፍቅር ተሸክሞ፤ ሌሎችም የአገራቸውን ታሪክ እንዲሰሙ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በአሜሪካና በአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ብቸኛውን በጥቁር ሰው ባለቤትነት የሚንቀሳቀስ የዩኒቨርሲቲ ፕሬስ መሥርቶም ያስተዳድራል።
እንግዳችን ሊሆን ስለፈቀደና እንደሥራው ብዛት ሳይሆን በትህትና እና በአክብሮት አንተ እያልን እንድናወራው ስለፈቀደ እያመሰገንን፤ በሕይወት እርምጃው ካካፈለን እንስጣችሁ፤ መልካም ንባብ።
የሚመነዘር ልጅነት
የኤልያስ ልጅነት በእውቀት፣ በንባብ ብሎም በታሪክ የታጀበ ነበር። ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ አካባቢ ነው። እናቱ ወይዘሮ ፀሐይ ደግ፣ ቤታቸው እንግዳ የማይጠፋ ደርባባ የቤት እመቤት፤ አባቱ አቶ ወንድሙ ደግሞ የጎንደርና የጎጃም አውራጃ አስተዳደር እንዲሁም የቀበሌ 54 ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል። ስድስት ልጆችን ያፈሩት አቶ ወንድሙ በአካባቢው ነዋሪ ፍቅርና አክብሮት የተቸራቸው ነበሩ። በዛም ምክንያት ልጆቻቸው ከአካባቢው ነዋሪ ዓይን ማምለጥ አይችሉም። «እኔ የቤቴ ልጅ ብቻ ሳልሆን የአካባቢያችን ነዋሪ ሁሉ ልጅ ነበርኩ፤ አካባቢው ነው ያሳደገኝ» ይላል ኤለያስ።
«ቤታችን የመጽሐፍ መደርደሪያ ነበር። አባታችን ለምሳ ቤት ገብቶ ቡና እየተፈላ እርሱ መጽሐፍ ያነባል። ሲወጣ መጽሐፉን ባቆመበት ገጽ ላይ ደፍቶት ይወጣል፤ እኔም መጽሐፉን ካቆመበት ቦታ እጀምርና አነባለሁ» በማለት ስለንባብ ጅማሮው ያስታውሰዋል። አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በፍሬሕይወት ቁጥር ሁለት እና ነፋስ ስልክ ተምሯል። የንባብ ልምዱ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍ እንዲሁም በስዕል ውድድሮች በማሸነፍ ከእኩዮቹ ልቆ እንዲገኝ ምክንያት ሆኖታል።
መሠረት የህንጻን ጥንካሬ እንደሚወስን ሁሉ ልጅነትም በጥንቃቄ ከተያዘ እድሜ ልክ የሚመነዘር መልካም ማንነት ይገኝበታል። ኤልያስም ለአገሩ ያለውን መልካም እይታ ያገኘው ከዚህ ከልጅነት ጊዜ ነው። «ኢትዮጵያን ለየት አድርጌ እንድወዳት አድርጎኛል...» የሚለው አቶ ኤልያስ፤ ይህም በአባቱ ሥራ ምክንያት በልጅነቱ ስለአገሩ ለመስማት ቀጥሎም ለማወቅ ቅርብ ነበርና ነው።
ትውስታውንም እንዲህ ሲል በቃላት ያስቀምጣል፤ «ልጅ ሆኜ የማስታውሰው አባቴ ከወዳጆቹ ጋር ሰብሰብ ብለው ሲጫወቱ 'ስለእናንተ የነገ እጣ ነው የምናወራው፤ ና ስማ' ይለኝ ነበር። በልጅነቴ እንደአዋቂ አዛውንቶች ስለአገር ሲያወሩ እሰማ ነበር»
የጋሽ ከበደ ውለታ
አቶ ከበደ ተክለየስ፤ «አብዬ» ይሏቸዋል እነኤልያስ። ስታዲየም ፊት ለፊት የእውቀት በር መጻሕፍት ቤት የሚባልና ከነኩራዝ ማተሚያ ቤት ቀጥሎ የአንጋፋ ደራስያንን መጻሕፍት አሳታሚና አከፋፋይ ባለቤት ነበሩ። «ጋሽ ከበደ የአባቴ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ። ቤት ከሌለሁና እግር ኳስ ልጫወት ሜዳ ካልሄድኩ እርሳቸው ጋር ነው የምገኘው። አዳዲስ መጻሕፍት ሲመጡ ለልጆች ያከፋፍላሉ እናም አንዱ ተቀባይ እኔ ነኝ»
ጋሽ ከበደ ደግ፣ ጨዋ፣ ለልጆች አሳቢም ነበሩ። ትንሹን ኤልያስ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደአዋቂ የሚያወሩና የሚመክሩ። «ከጓደኞቼ ጋር ሊኖረኝ ስለሚገባ ግንኙነትና ጊዜዬን እንዴት መጠቀም እንደለብኝ ይመክሩኝም ነበር። በልጅነት ያሳደጉኝ ትልቅ ሰው ናቸው፤ ያም በስብእናዬ ተጽእኖ ነበረው»
አገር፣ ፖለቲካ፣ ወጣትነትና ጋዜጠኝነት
የልጅነት አልፎም የወጣትነት መጀመሪያ ጊዜው የቀይ ሽብርና የአብዮት ወሬ የበዛበት ነው። «ዙሪያውን ጦርነት የነበረበት ጊዜ ነው። ይህ ማለት ከትምህርት ቤት ስንወጣ መኪና ቆሞ ወጣቶችን ጭኖ ሲሄድ እናያለን። ልጆች እየታፈሱ ብሔራዊ ውትድርና ይሄዳሉ፤ የሚያሳዝን ጊዜ ነበር» ይላል መለስ ብሎ እያስታወሰ።
በኋላ ኢህአዴግ ገባ፤ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ ደርግ የወሰደውን እንመልሳለን ያጠፋውን እናርማለን ብሎ ብዙ ነገር ቃል ገባ። ትኩስ የወጣትነት እድሜ ላይ የነበሩ ሁሉ ደግሞ የተገባው ቃል ሁሉ የሚሆን መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን የተባለው ሁሉ ሳይሆን ቀረና ብዙዎችን አስከፋ።
«በሰዓቱ ያኮረፈና የተቆጣ ሁሉ ጫካ ይገባል ብለን እንድናስብ ሆነን ነው የተሠራነው» የሚለው አቶ ኤልያስ፤ በታሪካችን ያለውና የሚባለውም ይህ ነበር ምርጫ የሌለው ወጣት ያመነበትን ከማድረግ ወደኋላ አይልም፤ ድንጋይ መወርወር ከሆነ ይወረውራል፤ መንገድ መዝጋት ከሆነ ይዘጋል...ወዘተ። ይህ የሆነው ደግሞ ቀድሞ መዘጋጀት ያለበት ስላልተዘጋጀና ስላልተሠራበት መሆኑን ይናገራል።
ይህን መተንፈሻ ፍለጋ ላይ ያለው ወጣት ኤልያስ ጋዜጠኝነትን ተቀላቀለ። በዋናነት «ሞገድ ጋዜጣ» ላይ የሠራ ሲሆን፤ ከዛ ቀደም ብሎ ሶስት ጋዜጦችን አገልግሏል። በኋላ የሞገድ ጋዜጣ እንቅስቃሴ ባሰጋቸው ሰዎች ምክንያት ጋዜጣው ተዘጋ። የመዘጋቱን ነገር ሲያነሳ በጋዜጣው የነበረውንም ስህተት አያይዞ ይጠቅሳል። «ብዙ ስህተት ለመሥራት ቅርብ ነበርን። ያለውን ስህተት ለማስተካከል ግን የሚረዱ የመንግስት አካላት አልነበሩም»
ወጣትነቱን በአግባቡና በልክ የተጠቀመው አቶ ኤልያስ፤ ያጠፋው ምንም ዓይነት ጊዜ አልነበረም። ከአሁን ዘመን ወጣት ጋር ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር በዛ ልክ ጎልተው ውጤታማ መሆን የቻሉ ብዙ ወጣቶች አልነበሩም። ከሥራው አንጻር እድሜውን የሚገምቱ ሰዎች በጣም ትልቅ ሰው ነው ብለው ያስቡ እንጂ ኤልያስ በአርባዎቹ የሚገኝ ጎልማሳ ነው።
«ለአገር እኛ ካልሠራን ማን ያስተካክላታል? ማን ይረከባታል? የሚል የትውልድ ቁጭት ነበረን። በአጋጣሚ ሆኖ እኔ እድለኛ ሆኜ የከበቡኝ ሰዎች ትላልቅ ነበሩ። ጓደኞቼ ትላልቅ ሰዎች ናቸው። ይህም የአስተዳደግ ውጤት ይመስለኛል» ይላል።
«እመለሳለሁ» ስንብት
1986.ም ሃያዎቹን በቅጡ ያልደፈነው ወጣት ኤልያስ በአዲስ አበባ በተካሄደ አንድ የጥናት አውድ ላይ ንግግር ሊያደርግ ወጣ። ንግግሩን በአዳራሹ የነበሩት ትላልቅ ሰዎች ወድውት ነበር። በተለይም ተናጋሪው በእድሜ ከሁሉም ታናሽ መሆኑ ትኩረታቸውን ሳበው። የንግግሩ መልዕክት፤ «ታሪካችን እየጠፋ ነው፤ በዚህ ከቀጠልን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አንችልም። እንበርታና እየፈረሱ ያሉትን እናቆያቸው» የሚል ነበር።
በመቀጠልም በወቅቱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስለነበረው ግንኙነት በሚነሱ ሃሳቦችና በሚወጡ ካርቱኖች መሰረት ያደረገ ጥናታዊ ወረቀት አዘጋጀ። ወረቀቱንም በአሜሪካ በሚካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አውደ ጥናት ላይ ለማቅረብ ጠየቀ፤ ተፈቀደለት። ወረቀቱንም 12ኛው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አውደ ጥናት ላይ ለማቅረብ ተመረጠ። በዛውም የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ መሥራች አባል ነበረና ድርብ ኃላፊነትን ይዟል። አውደጥናቱ ደግሞ በአሜሪካ ሚችጋን ዩኒቨርስቱ ለሶስት ሳምንታት የሚቆይ ነበር። አንደሄደ ግን ሀገር ቤት የስራ ባልደረቦቹ ጋዜጠኞች መታሰራቸወን ተከትሎ መመለስ አንደማይችል ተረዳ።
አስቀድሞ ግን ተመልሶ አገሩ እንደሚገባ እርግጠኛ ነበር፤ ለዛም ነው አየር መንገድ ሄደው የሸኙትን እናቱን በቅጡ ያልተሰናበተውና «እመለሳለሁ» ብሎ የተለየው። አስቀድሞ ከአገር የመውጣት ሃሳብ አልነበረውም፤ «ልሄድ ተነስቼ አውቃለሁ፤ ግን ትቼው እዚሁ ኑሮ ጀምሬ ነበር። ሁለት ሃሳብ ይዞ ሥራ መሥራት አይቻልምና። እዚህ ቆርጬ ልሠራና ትልቅ ሰው ሆኜ አገሬን አገለግላለሁ ብዬ ነበር» ይላል።
አሜሪካን ገብቶ አገሩ እንደማይመለስ ካወቀ ሦስት ዓመታት እንዳለፉ የእናቱን ዜና እረፍት በዛው በአሜሪካ ሰማ። «ወላጆቼ እኔን ወልደው አሳድገው ለዚህ አድረሳዋል፤ እኔ እንዴት ነው ውለታቸውን የምከፍለው እል ነበር። ልጅ ሆኜ የምሞት አይመስለኝም ነበር። ከሚፈለገው በላይ ደፋር ሆኜም አውቃለሁ። እናቴ ስትሞት ግን ሞት ምን እንደሆነ በቅርብ ለማየት ቻልኩ»
ለአንዱ የከፈሉት ዘጠና ዘጠኝ
የአሜሪካ ኑሮ ቀጠለ፤ በሎስአንጀለስ የኢትዮጵያን ሪቪው ጋዜጣ ለስድስት ዓመታት እንዲሁም ለአንድ ዓመት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ አርታኢ ሆኖ አገለገለ። በካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ እየሠራ ሳለ ነበር ፀሐይ አሳታሚ ድርጅትን የመውለድ ሃሳቡ ጸንቶ ሥራውን የለቀቀው። እንዲህ ሆነ፤ የኢትዮጵያ ባለውለታና ወዳጅ ከሆኑት ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ቅርብ ወዳጅነት ነበራቸው። አንድ ጊዜም የህትመት ድርጅት ስለመክፈት ያለውን ሃሳብ አካፈላቸው።
ሪቻርድ ነገሩ ከባድ መሆኑን አንስተው፤ «ምንም ትርፍ ላታገኝ ትችላለህ፤ ጭራሽም መጎዳት አለ። ድካሙንና ኪሳራውን እያወቅህ ነው ልትገባበት የወሰንከውሲሉም ጠየቁ። አቶ ኤልያስ በበኩሉ እርግጠኛ ነበር። የሪቻርድ ቀጣይ ምክር እንዲህ የሚል ሆነ፤ «መቶ መጽሐፍ አሳትመህ ምንአልባት እድለኛ ከሆንክ አንዱ ነው ትርፋማ የሚሆነው፤ ከዛም የዘጠና ዘጠኙን አንዱ ነው የሚከፍልልህ» ነገሩን ከልብ ያደመጠው ኤልያስ እስከዛሬም የሪቻርድን ምክር አልዘነጋም። «እውነት እስኪሆን ድረስ እውነት አልመሰለኝም ነበር» ይላል ዛሬ ላይ ሆኖ።
የመጨረሻዎቹ አንድ ሳንቲሞች
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ብዙ ተደክሞበታል። በአገረ አሜሪካ የኢትዮጵያውያን መጻሕፍት ሊታተሙባቸው የሚችሉባቸው ድርጅቶች በበቂ አማራጭ አልነበሩምና ፀሐይ ትልቅ ቀዳዳ ሊሸፍን የሚችል ድርጅት የመሆን ተስፋው ትልቅ ነበር። በወቅቱም የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሐፍትን በማሳተም ላይ ያሉት አንዳንድ ቦታዎች ጥሩ መጻሐፍትን ቢያሳትሙም መጥፎ የሚናገሩትም ይወጡ ነበር።
«አማራጭ መፍጠር አለብን» በሚል መነሻ የተጀመረው ሥራ ቀላል አልሆነም። «በገንዘብ ደረጃ ፈታኝ ጊዜ ነበር። ክሬዲት ካርድ እስከጥግ ድረስ ወስጄ፤ ከጡረታ ገንዘብ ላይ አውጥቼ፤ ከዛም አልፎ በጥቂቱ ከጓደኞቼ ተበድሬ ነበር» ይላል መነሻወን ሲያስታውስ።
የመጨረሻዎቹ አንድ ሳንቲሞች ታሪክ ደግሞ እንዲህ ነው። ከእቃ ግዢ መልስ የሆነና የተራረፈ ዝርዝር ሳንቲም ማጠራቀሚያ እቃ አለ። ኤልያስም ከኪሱ የሚተራርፉ ሳምቲሞች በዕቃው ውስጥ ሲያስቀምጥ ኖሯል። ገንዘቡ ባስፈለገው ጊዜ ታድያ ሳንቲሙን እየለቀመ መጠቀም ጀመረ። እያለ እያለ የቀሩት አንድ አንድ ዶላር ሳንቲሞች ብቻ ሆኑ።
«በእቃው የነበረውን ሳንቲም ለቅሜ ጨርሼ አንድ ሳንቲሞች ነበሩ የቀሩት። በመጨረሻ ነዳጅ ለመሙላት ፈልጌ አንድ ሳንቲሞቹን ሰብስቤ በላስቲክ አድርጌ ነዳጅ ልከፍል ሄድኩ። ነዳጅ ቀድቼ እንደጨረስኩ  ለማደያ ጣብያው ሰራተኛ ሳንቲሙን ሰጥቼ በፍጥነት ከቦታው ራቅሁ። ላስቲክ ሙሉ አንድ ሳንቲም ነበርና ሰውየው ያንን መቁጠር ነበረበት።»
የኤልያስ እያንዳንዱ እርምጃ ለጓደኞቹ ግልጽ አልነበረም፤ በጣም ጥሩ ከሚባል ሥራ ለቅቀው ያለተዋጠላቸውም ብዙ ናቸው። እርሱ ግን አለ፤ «ብዙ ሰው አውቃለሁ፤ አገሬ ብዙ ታሪክ አላት፤ እነዚህን ሰዎች ረድቼ ታሪኩ ካልወጣ እነዚህ ሰዎች ከታሪኩ ጋር ይሞታሉ። ያኔ ለኢትዮጵያ የሞት ሞት ነው።»
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት
«ሁሌም ታሪክ አልተነገረልንም እንላለን፤ ያንን እንዲነግሩልን የምንፈልገው ሌሎች ሰዎችን ነው። እነርሱ ምንም ዕዳ የለባቸውም። እናም ችግሩ ያለው ከእኛ ግምትና ጥበቃ ላይ ነው» ባይ ነው ባለታሪካችን። በዚህ ምክንያትና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ታሪክ ለመናገር አቅም አላቸው በሚል መነሻ ሃሳብ ፀሐይ ማተሚያ ድርጅት ተጸነሰ። በዛም ላይ የውጪ አገር ዜግነት ኖሯቸው ስለኢትዮጵያ በፍቅር የሚሠሩ ሰዎች ሥራዎቻቸው እየጠፉ ነበርና ለእነርሱም ፀሐይ ብርሃን ሆናቸው።
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት አምስት የተለያዩ የሀትመት ኢምፕርንቶች ያሉትና ከኢትዮጵያ በተጓዳኝ አፍሪካን አና የጥቁር አሜሪካውያንን ታሪክ እና ስነጽሁፍ የማሳተም ኃላፊነት የተሸከመ ማተሚያ ድርጅት ነው። እዚህ ላይ አቶ ኤልያስ በ6ኛው የዓደዋ ጉዞ መክፈቻ ስነስርዓት ጥቅምት 02 ቀን 2011.ም በጣይቱ ሆቴል ባደረገው ንግግር እንዳለው፤ «የአፍሪካውያን የጽሑፍ ሥራዎችን እናሳትም ነበር። በዚህ መካከል ሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ዘጋ፤ ይህም ብቸኛው አፍሪካዊ አሳታሚ ድርጅት ነበር። እነርሱ ገንዘብ እያላቸው ግን ባለራዕዮቹ ስለሞቱ ገንዘብ የለንም ብለው ነው ያቆሙት፤ እኔ ከእነርሱ የበለጠ የነበረኝ የአገሬ ታሪክ ነው»
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ፈተናዎችን አልፎ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያለ ብቸኛው የጥቁር አሳታሚ ድርጅት ነው። የተለያዩ የህትመት ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን፤ አፍሪካን አካዳሚ ፕሬስ፣ ሜሪማውንት ፕሬስ እንዲሁም የልጆች መጻሐፍትን ከሚያሳትመው የጨረቃ መጻሕፍት ጋር በጋራ ሲሠራ ዓመታት ተቆጥረዋል። በነገራችን ላይ አሳታሚ ድርጅቱ ከሚያሳትማቸው ሥራዎች ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የታሪክ መጻሕፍት ይገኙበታል።
«ወደአገራችን ልንገባ ነው»
አቶ ኤልያስ ሪቻርድ ፓንክረስትን ሲያስታውስ «በልጅነት ስሰማው ከነበረው ታሪክ አብሮኝ ላደገው ጥያቄ መልስ የሰጡኝ አንዱ ሰው ናቸው» ይላል። አንድ ጊዜ የሆነውን አስታውሶ የነገረኝን በእኔ ቃል ልንገራችሁ፤ ሪቻርድ ፓንክረስት ከባለቤታቸው ጋር የጻፉትን መጽሐፍ ያሳተመው ኤልያስ አገር ቤት መምጣት ስለማይችል ሪቻርድ ለህክምና ለንደን በሄዱ ጊዜ አጋጣሚውን ለመጠቀም ወደዛ አቀና። ሃሳቡ ሪቻርድን በአገራቸው ሰዎች ፊት የሚያመሰግንና የሚያከብር ክዋኔ ለማካሄድ ነበር።
ፕሮግራሙ እንደ ነገ ሊሆን ዛሬ ላይ ወደ ሪቻርድ ቤት አቀና። ቤቱ ሪቻርድ ለንደን ሲሆኑ የሚገኙበትና እዛ ባልሆኑ ጊዜ ደግሞ የሚያከራዩት ነው። ታድያ ኤልያስ ወደቤታቸው ዘልቆ ሲያይ ሪቻርድና ባለቤታቸው እቃዎቻቸውን እየሸከፉ ለጉዞ ዝግጅት ላይ ነበሩ። ነገሩ ምን እንደሆነ ኤልያስ ጠየቀ፤ «ቤቱን ሸጠን ለንደንን ለቅቀን ወደአገራችን ልንሄድ ነው» ብለው መለሱለት ፓንክረስት።
«የነበርነው ለንደን ያለው ቤታቸው ውስጥ ነው፤ ኢንግሊዛዊ መስለውኝ ነበር፤ ከለንደን ሊወጡ ነው? እቃቸውን ሸክፈው ወደሌላ አገር ሊሄዱ ነውባለማመን ውስጥ ሆኖ ኤልያስ በውስጡ የሚመላልሰው ሃሳብ ነበር። ሪቻርድ እያሉ የነበረው ግን ለንደን መኖራችንን አቁመን ኢትዮጵያ ልንኖር ነው ነበር።
«እንባዬ ግጥም ነው ያለው፤ ኢትዮጵያን ወደው አቅፈው ይኖራሉ፤ እኔ እንኳ በእርሳቸው ልክ ይህን ማለት አልችልም። እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ያለኝ ፍቅር የባሰ እንዲግል አድርገዋል» ይላል።
ለሥራ ያነሳሳ ምላሽ
ይህን ነገር ሳልገልጽ መቅረት አይቻለኝምና ኤልያስ ከነገረኝ መካከልና ለሥራ ብርቱ ካደረገው ሀሳብ ውስጥ ሌላውን ላካፍላችሁ። አሁንም ጉዳዩ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር የሚገናኝ ነው። ኤልያስ፤ ገበያ ላይ የጠፋ አንድ መጽሐፍ ፈልጎ በእጃቸው የሚገኝ ከሆነ ይጠይቃቸዋል።
እርሳቸውም «ማን ነው የጻፈውሲሉ ጠየቁት። ነገሩ አስደነገጠው። መጽሐፉ ራሳቸው የጻፉት መሆኑን ባለቤታቸው ሪታ አስታወሷቸውና መለስ ብለው መጽሐፉ ገበያ ላይ የማይገኝ መሆኑን ለኤልያስ ነገሩት። እርሱ ግን ከተፈጠረው ነገር የራሱን ትምህርት እየቀሰመና እያብላላ ነበር።
እንዲህም ጠየቀ፤ «ሰው እንዲህ መሆን ይችላልን? ብዙ ከመሥራቱ የተነሳ ቀድሞ የሠራውን እስኪረሳ ድረስ ይሆናልከዚህም በኋላ መለስ ብሎ እስኪረሳው ድረስ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለበት አመነ። «ብዙ መሥራት እንዳለብኝ ያሳሰቡኝና ገደቡን አንስተው መንገድ የከፈቱልኝ ሰው ናቸው። እርሳቸው በዛ ንግግር ሕይወቴን ቀይረዋል» ይላል።
«እንዴት ነሽ አገሬአመጣጥ
24ዓመታት በኋላ አገሩ የተመለሰው ኤልያስ ወደ አገሩ የመመለስ ተስፋውን ፍጹም ቆርጦ ነበር፤ «የነገሮችን አካሄድ ስመለከት ይህ ቀን ሊመጣ አይደለም ኢትዮጵያ ትቆያለች ብዬ አስቤ አላውቅም» ይላል። ከአገሩ ርቆ ለአገሩ ብዙ ሥራን ሲሠራ ይቆይ እንጂ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ያጣው ብዙ ነው።
«ኢትዮጵያ ውስጥ አስቀያሚዋ እንኳ ቆንጆ ናት። የመልክ ቁንጅና ሳይሆን ከውስጥ የሚበራ ውበት አለ። ሕዝቡ ደግ ነው። ውስጥ ለውስጥ የተወሳሰበ ነገር ቢኖርም የሚራራ ሕዝብ አለ። ለመስተካከልና ጥሩ ለመሆን በጣም ቅርብ ነው። መጥፎ ለመሆንም እንደዛው።...በታሪካችን መጥፎ የሚባለውን ነገር አይተናል። ከዚህ በኋላ ግን የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን ብዬ አስባለሁ» ሲል ተስፋውን ይገልጻል።
ነገን በፀሐይ እይታ
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ልክ እንደ ኤልያስ ሁሉ ስደቱ አብቅቶ አገሩ ገብቷል። መጻሕፍትን ለማስገባት የነበረው ችግር አልፎ አሁን ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቶ ለመሥራትም እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ነው ኤልያስ የነገረን። «ትልቅነት መጻሐፍትን ማሳተሙ አይደለም፤ ትውልድ መፍጠሩ ነው። የሚያነብ፣ የሚጽፍና አርትኦት የሚሠራ ትውልድ መፈጠር አለበት» ያለው ኤልያስ ይህን ግብ ለማሳካት ይንቀሳቀሳል። የፀሐይ ቢሮ አዲስ አበባ እስኪከፈት ድረስ ታድያ ፀሐይተለያዩ ዪኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ በመሥራት ይሳተፋል፤ ለዛም በአሁኑ ሰዓት ከጎንደርና ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
መልዕክተ ኤልያስ
መልዕክቱ እንዲህ ነው፤ አረአያነት ወሳኝ ነው፤ ንባብን ለማስፋፋት የወላጅ በምሳሌነት መምራት ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት ያመለጡንን እድሎች ላለመርሳት ማንበብ አስፈላጊ መሆኑንም አያይዞ በማንሳት በአገራዊ ለውጦች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ያሳስባል። «ካለፉ በኋላ 'ወይ የእንትና ጊዜ' የምንላቸው ጊዜያት አሉ። በዛ ጊዜ የነበሩ ሳይጠቀሙበት አልፈዋል። ይህ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ነው። አይሆንም የሚባሉ ነገሮች የሆኑበት እና ይሆናሉ ብለን የምንፈራቸው ያልሆኑበት ጊዜ ነው»
ቀጠለ፤ «ሁላችን ፖለቲከኛ መሆን የለብንም፤ ባለንበት ቦታ የምንሠራውን ሥራ በስርዓትና በሀቅ ካደረግን፤ መሥራት የሚቻለው ላይ አተኩረን በጥራት ከሠራን ኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባት አይኖርም» ባለአገር ሆኖ ለእያንዳንዱ አገራዊ ነገር በመጨነቅና ያገባኛል በማለት፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለውን ማስረከብ ተገቢ መሆኑንም በመልዕክቱ ጨምሯል።
«የኢትዮጵያ ትልቅነት መጽሐፍ ውስጥ ተደብቆ ነው ያለው» ምክንያት ሆኖ ታሪክን የሚናገረው የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መሥራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ። እኛም መልካም የሥራ ዘመንና ዕድል እየተመኘን በዚህ እናብቃ! ሰላም።

1 comment: