Translate/ተርጉም

Tuesday, October 30, 2018

ያልተጠቀምንበት የሥነ ጥበብ ሕክምና (አርት ቴራፒ)


 ያልተጠቀምንበት የሥነ ጥበብ ሕክምና  (አርት ቴራፒ)

ጌትነት ተስፋማርያም
በአንድ ወቅት በአማኑኤል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ተገኝቼ ነበር፡፡ መርሃግብሩ የተዘጋጀው «ጥበብን ለአዕምሮ ህክምና አጋዥ ማድረግ ይቻላል» የሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡ ዝግጅቱ የመስክ ጥበብ ዝግጅት (ኮንሰርት) አይነት ነው፡፡ የአዘጋጁት የአማኑኤል ሆስፒታል እና የብሬማን ፊልም ፕሮዳክሽን ናቸው፡፡ ከድምፃውያን እነ ማሀሙድ አህመድ፣ ፀሐዬ ዮንስ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ሔለን በርሄ … ሌሎችም አሉ፡፡ ከኮሜዲያን እነፍልፍሉ፣ ከገጣሚያን ተፈሪ ዓለሙ፣ ምሥራቅ ተረፈ አሉ፡፡ ገጣሚ አበባው መላኩና ተዋናይ ግሩም ዘነበ መድረክ መሪዎች ነበሩ፡፡ ሁሉም የጥበብ ሰዎች ሲሆኑ፤ ታዳሚዎች ደግሞ የአማኑኤል ሆስፒታል ታካሚዎች ናቸው፡፡
ይሄ በአማኑኤል ሆስፒታል ያየሁት ኮንሰርት በሀገራችን የመጀመሪው ይመስለኛል፡፡ የኮሜዲ ራዎች፣ ዘፈኖች፣ ግጥሞች ለህሙማኑ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከአማኑኤል ሆስፒታል ህሙማን መካከልም የሚደንቅ ግጥም ያቀረቡም ነበሩ፡፡ ይህን ሃሳብ እያሰላሰልኩ ነበር የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና ወደሚሰጥበት «ክሁል ሁለንተናዊ የዕድገት ማዕከል» ያመራሁት። 
 
ኢማና ኢብራሒም የ25 ዓመት ወጣት እና የህክምና ትምህርት ተማሪ ነች። ክሁል ሁለንተናዊ የዕድገት ማዕከል በተሰጠው የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ተሳታፊ ነች። እርሷ እንደምትለው፤ መጀመሪያ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ምንድን ነው? የሚለውን የማወቅ ፍላጎት ስለነበራት እንድትሳተፍ አስችሏታል። ከልምምዱ በኋላ ግን በህይወቷ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደምትችል ምልክት አይታበታለች። በልምምዱ ወቅት በመጀመሪያ አዕምሮዋን እና ሰውነቷን ዘና አድረጋ እንድትቆይ አድርጓታል። ከዚያም በተሰጣት ወረቀት ላይ የተለያዩ መስመሮችን እየሳለች የውስጧን ፍላጎት እንድታወጣ አስችሏታል። በአሰመረቻቸው መስመሮች ውስጥ ግን አንድ ነገር ፈልጋ እንድታገኝ ሲደረግ ከህይወቷ ውስጥ የረሳችው የመሰላት ነገር አብሯት እንዳለ ተረዳች። አንድ ክስተት እንደሚያስታውሳትም አወቀች። የምትወስናቸው ውሳኔዎች፣ አስተሳሰቧ ላይ እና ንግግሯ ላይ ያለፈ ክስተት ተጽእኖ እያደረገባት እደሆነ እና እንዳልሆነ ሳታውቅ ነበር እስከአሁን ህይወቷን ስትመራ የነበረው። ይሁንና የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ባለሙያዋ በሰጠቻት ህክምና ይህንን በሚገባ እንድትረዳው እንዳደረጋት ትናገራለች።
በአስተሳሰቧም ሆነ በውሳኔዎቿ መሃል ይህ ክስተት ተጽእኖ እንደማያሳድርባት እርግጠኛ መሆን ችላለች። በመሆኑም የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) በእያንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ መለመድ ያለበት ጥበብ መሆኑን ወጣት ኢማና ታስረዳለች።
አርት ቴራፒ (የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና መስጠት) በተቀረው ዓለም ቢለመድም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ተሠርቶበታል ማለት የሚያስደፍር ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ በርካታ የማገገሚያ ህክምና ዘዴዎች(ቴራፒ) አሉ። ፊዚዮ ቴራፒ በመባል የሚጠራው የህክምና ዘዴ የአካል እንቅስቃሴን ለማሻሻል የሚሰጥ ሲሆን፤ ሳይኮቴራፒ የሚባለው ደግሞ የሥነ አዕምሮ ጤንነትን ለማሻሻል የሚሠራበት ነው። ወደ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ሲመጣ ደግሞ በጥሬ ትርጉሙ ሥነጥበብን ለህክምና ማዋል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ህክምናው ጥበብን ለህክምና የማዋል ዘዴን ተጠቅሞ የሰዎችን የአዕምሮ ጭንቀት እና ድብርት እንዲሁም ያለፈ የህይወት ታሪክ ክስተት መጥፎ ተጽእኖን ለመቀነስ ይረዳል። 
የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) በተለይ በአደጉት አገራት በርካታ ሙያተኞችን ያፈራ የህክምና አይነት ነው። ከህጻናት እስከ አዋቂዎች ድረስ የሃሳባቸውአውጥተው በወረቀት እንዲያሰፍሩ እና በባለቀለም ሥዕልን እንዲስሉ በማድረግ ከአዕምሮ ጤንነት ጋር የተያያዘ ህክምና ይሰጥበታል። ሆኖም በፍርድ ቤቶች ውስጥ እና በተለያዩ የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታሎች ውስጥ ጭንቀትን እና የአዕምሮ ውጥረትን ለመቀነስ እደመፍትሄ  ይውላል።  
የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ የተማሩት ወይዘሮ ዘሃራ ለገሰ ህክምናውን በኢትዮጵያ በመስጠት ተጠቃሽ ሙያተኛ ናቸው። በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው እና የሥነጥበብ ሥራዎችን በሚደግፈው «ኩሁል አካዳሚ» ባለፈው ወር ለበጎ ፈቃደኞች የአርት ቴራፒ ልምምድ ሰጥተዋል። በተለያዩ ወቅቶች ላይ በኢትዮጵያ በነጻ በፍርድ ቤቶች እና በተለያዩ ማዕከላት በተለይ ጥቃት የደረሰባቸው ህጻናት ላይ የፍርድ ቤት ማቆያን በመጠቀም ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።
 ወይዘሮ ዘሃራ እንደሚናገሩት፣ አርት ቴራፒን የሚማር ሰው በአብዛኛው የሳይኮሎጂ ትምህርት ላይ የሚሰጡ እወቀቶችን የሚጠቀም ነው። ነገር ግን የሥነአዕምሮ ችግር መፍትሄዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ እንዲሆን ያስፈልጋል። የቀለም ቅንብሮች ከአዕምሮ ጋር ያላቸውን ዝምድና እና አስፈላጊነት ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆን ይገባዋል። የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ህክምና (አርት ቴራፒ) ለማንኛውም ሰው የሚሰጥ ህክምና በመሆኑ ማንኛውም ሰው በባለሙያ ታግዞ በተዘጋጀለት ወረቀት ላይ አዕምሮው ውስጥ ያለውን ሃሳብ በሥዕል እንዲያወጣው ይደረጋል። በተለይ ከሥራ በኋላ የተጨናነቀ አዕምሮን ዘና ለማድረግ ህክምናውን በእጅጉ ይጠቅማል። ህክምናው ሲሰጥ ሥዕል የሚችልም ሆነ የማይችል ሰው መሳተፍ እንደሚችል ማመን እንደሚገባ ያስረዳሉ።
 የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ከመሰጠቱ በፊት ለተጠቃሚው ቃለመጠይቅ ይደረጋል የሚሉት ወይዘሮ ዘሃራ፤ በሰውዬው ላይ አጠቃላይ ምልከታ እንደሚደረግ እና ህክምናው የሚጠቀም ሰው በቡድን መምጣት እና አጠቃላይ ቤተሰቡን ይዞ ልምምድ ማድረግ እንደሚችልም ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚጨናነቁ ተማሪዎች፣ ለህጻናትና እርጅና ለተጫጫናቸው ሰዎች እንዲሁም  ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ተመራጭ መሆኑን ያስረዳሉ።
የኩሁል አካዳሚ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አርክቴክት ነጻነት አስመላሽ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ ውስጥ «ኩሁል አስኳላ»«ሸጋ ቶክ» እና «ሰልፊ ኢንጂነሪንግ» የተባሉ የግለሰቦችን የህይወት ብቃት ለማሻሻል የሚሰራባቸው መርሃግብሮች አሉ። በርካታ ወጣቶችም ማዕከሉ ውስጥ በነጻ የመነጋገር እና ስለተለያዩ ጉዳዮች የመወያያት ልምድ እንዲያዳብሩ ይደረጋል። የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ልምምድ ቢሰጥ ይበልጥ ወጣቶችን ማገዝ እንደሚቻል ያመኑት ወይዘሮ ዘሃራም ፍላጎት በማሳየታቸው ለ70  ሰዎች በማዕከሉ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሕክምና (አርት ቴራፒ) ልምምድ በነጻ እንዲሰጡ ሆኗል። በወቅቱ ስለአርት ቴራፒ አብዛኛው ሰው ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ስለነበር ምን እንደሆነ እንኳን የማያውቁ እና የሥዕል ጥበብ መማር እንደሚችሉ ያስቡ ነበር። 
 «ህክምናው የሥዕል ችሎታ ጋር የማይገናኝ እና የአዕምሮ ሃሳብን በማውጣት ውስጣቸው ያለውን ስሜት ብቻ መግለጽ የሚቻልበት፤ የሥዕል ችሎታን የሚጠይቅ እንዳልሆነ መረጃ ተሰጥቿዋል። ስለዚህም በልምምዱ ወቅት ሁሉም የእየራሳቸውን ሥዕል እንዲሰሠሩ የከለር እርሳሶች ቀርበውላቸው ነበር። ከልምምዱ በኋላ ደግሞ አብዛኛው ተሳታፊ ነጻ አዕምሮ በመያዛቸው በአርት ቴራፒ ህክምናው ደስተኛ ሆነዋል» በማለት አርክቴክት ነጻነት በህክምናው እየተገኘ ያለውን ጠቀሜታ ይገልጻሉ።
 

No comments:

Post a Comment