Translate/ተርጉም

Tuesday, October 30, 2018

የቼሆቭ ትረካዎች ሲፈተሹ


የቼሆቭ ትረካዎች ሲፈተሹ
በዶ/ር ታደለ ገድሌ ጸጋየ
በሩሲያ ማኅበረሰብ ዘንድ በእጅጉ ከሚወደዱትና ከሚደነቁት ደራስያን ውስጥ አንቶን ፓቭሎቪች ቼሆቭ አንደኛውና ዋነኛውም ነው፡፡ ዝነኞቹ የአንቶን ፓቭሎቪች ቼሆቭ ትረካዎች ከሩሲያኛ ወደ ሌሎች የዓለም ቋንቋዎች በብዙ ቅጂ እየተተረጎሙ የዓለም ሥነ ጽሑፍ አካል ከሆኑ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቼሆቭ ጥቂት ድርሰቶች ከእንግሊዝኛ የመተርጎማቸውን ያህል በቀጥታ ከምንጩ ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ሥራዎቹ ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡
በቅርቡም ወይዘሮ ትዕግሥት ፀዳለ ኅሩይ 22 ትረካዎችን ከሩሲያኛ ተርጉመውና «ቅብጥብጧ፤ ስለፍቅርና ስለሌሎች» በሚል ርእስ አሳትመው እነሆ ብለውናል፡፡ ዘመነ ኅትመት 2009 .ም ሲሆን መካነ ኅትመት አ.. ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ ብር65 መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የገጽ ብዛት 256 ነው፡፡ በፊት ሽፋን የቅብጥብጧን እመቤት የሚያመለክት ሥዕል ይታያል፡፡
ተርጓሚዋ በውስጥ ገጾች የታላቁንና የተወዳጁን ደራሲ የቼሆቭን ሥነ ሕይወት የሚጠቁም ማለት የራሱንና የቤተሰቡን፤ ከተወዳጆቹ ከኒኮላይ ቶልስቶይና ከማክሲም ጎርኪ ጋር በሕይወት ዘመኑ የተነሣቸውን የማስታወሻ ፎቶግራፎች አካትተዋል፡፡ እንዲሁም በተወለደበት ታጋንሮጌ ከተማ፤ የተማረበት ጂምናዚየም፤ በስሙ የተሰየመው የተወለደበት ቤት ሙዚየም፤ እዲሁም በሌሎች የሩሲያ ከተሞች የተቋቋሙለት ሙዚየሞች፤ በሀገር ውስጥና በውጭው አገር ከተሞች ውስጥ ለመታሰቢያነት የቆሙለት ልዩ ልዩ ሐውልቶች፤ በሞስኮ ከተማ የሚገኘው የመካነ መቃብሩ ሐውልት እንዲካተቱ አድርገዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ተርጓሚዋ ወይዘሮ ትዕግሥት ስለዝነኛው ጸሐፌ ተውኔትና የአጫጭር ታሪኮች ደራሲ የሕይወት ታሪክ ማለፊያ የሆነ ትንታኔ ሰጥተውናል፡፡ በትርጉማቸው ውስጥም ለትረካው ግርታ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለው ለገመቷቸው ለአንዳንድ ቃላት በግርጌ ማስታወሻ የአብርሆት ሥራ ሠርተዋል፡፡ይኽም አንባቢና አናባቢ በቀላሉ እንዲግባቡ ያደርጋል፡፡ ወይዘሮ ትግሥት የደራሲውን ምርጥ አባባሎች በሥራቸው መጨረሻ ላይ አስፍረውልናል፡፡ ለምሳሌም ከምርጥ አባባሎቹ ውስጥ «ለማክሰኞ ቦታውን የማይለቅቅ ሰኞ የለም» የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ስለ ሩሲያ ስም አወጣጥ፤ የአክብሮት፤ የማዕረግ፤ ቁሳቁስና ወንዝ ስሞች--- ማብራሪያ አቅርበውልናል፡፡
ተርጓሚዋ ወይዘሮ ትዕግሥት አድካሚና አሰልቺ፤ አስቸጋሪም የሆነውን የትርጉም ሥራ ለማጠናቀቅ የቻሉት እንደ ስማቸው ትዕግሥተኛ ሆነው ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ትሑት እይታ በሀገራችን ዘመን አይሽሬና ታላላቅ ሥራዎችን ከሌላ ቋንቋ እንደ ወይዘሮ ትዕግሥት ተርጉመው ያቀረቡልን ሴቶች ቁጥር እምብዛም ነው፡፡
ተርጓሚዋ ወይዘሮ ትዕግሥት የተወለዱት በአዲስ አበባ ውስጥ በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡በልጅነታቸው አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ገብተው የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በታላቁ ሳይንቲስት ስም ከተሰየመው ሚሃኤል ሎሞኖሶቭ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኝነት ፋካልቲ በጋዜጠኝነት የማስትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡
ወይዘሮ ትዕግሥት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በመምህርነት፤ በጋዜጠኝነትና በአስተርጓሚነት፤ በዓለም አቀፍና በሕዝብ ግንኙነት ዘርፎች ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በአካዳሚው ዘርፍ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል በመምህርነት፤ በኃላፊነትና ዲን ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ዘርፍ የሴቶች ፐሮጀክት ዳይሬክተር፤ የፕሬዚዳንቱ የአስተዳደር ረዳት፤ የዩኒቨርሲቲው ልዩ አገልግሎቶች አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ይሠራሉ፡፡
የቼሆቭን ድርሰቶች ለመተርጎም ወይዘሮ ትዕግሥትን ያነሣሣቸው ገና ተማሪ ሳሉ የታላቁን ደራሲ የፓቭሎቪችን ሥራ የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ከአጎታቸው እየተዋሱ ያነብቡ ስለነበር ነው፡፡ ከጊዜ በኋላም በመቅደማቸው መግቢያ ላይ የምስጋናና የመታሰቢያ ቃል ወደ ለገሥዋት ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ለከፍተኛ ትምህርት ተልከውና ከዚያው የጥበብ ባሕር ውስጥ ገብተው የቼሆቭን ድንቅ ድርሰቶች ማንበባቸው ለዛሬው የትርጉም ሥራቸው መሠረት እንደሆናቸው ለመገመት ይቻላል፡፡
በዚህ ዓይነት ወይዘሮ ትዕግሥት ፀዳለ ኅሩይ በትርጉም ረገድ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ራሱን ችሎ የተደመረና ተጠቃሽ የሆነ ሥራ አስመዝግበዋል ማለትነው፡፡ 22ቱ የቼሆቭ ድርሰቶች ከሩሲያ ሕዝብ ሥነ ሕይወት፤ ከአዳዲስ የአተራረክ ቴክኒክና አይረሴነት ከአላቸው አዳዲስ ገጸ ባሕርያት ጋር ያስተዋውቁናል፡፡ ሩሲያውያን «ለእንግሊዞች ሸክስፒር አለላቸው፡፡ ለእኛ ደግሞ ፈጣሪ ቼሆቭን ሰጥቶናል» በማለት ይመኩበታል፡፡
እናም በወይዘሮ ትዕግሥት ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞና ታትሞ በሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል በተመረቀው መጽሐፍ ውስጥ በእውቁ ደራሲ በአንቶን ፓቭሎቢች ቼሆቭ ከተደረሱ አጫጭር ታሪኮች ጋር እንተዋወቃለን፡፡ አጫጭር ድርሰቶቹ ቅብጥብጧ፤ ለማኙ፤ የቤተሰብ አባት፤ፈንጠዝያ፤ ሰቆቃ፤ ወፍራምና ቀጭን፤ ማስረጃ፤ ያልተለመደ ሁኔታ፤ ስለፍቅር፤ የቃለ አጋንኖ ምልክት፤ ባልተቤቱ፤ (ባለቤቱ ለማለት)፤ አስቸጋሪ ሰዎች፤ ክፉ ልጅ፤ ዘማሪዋ፤ አብየ፤ አሮጌው ቤት፤ በዕረፍት ቦታ፤ መተኛኛት ፈለግሁ፤ አንጸባራቂው ሰብእና፤ ቫንካ፤ ኢኦኒች፤ ልጅ እግሯ ሴት ሲሆኑ የድርሰቶቹን የአማርኛ ትርጉም ከሩሲያኛው ጋር እስከነ ርእሳቸው እያገናዘብኩ ሳነብባቸው የወይዘሮ ትዕግሥት የአማርኛ ትርጉም ማለፊያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡


ቼሆቭ በነዚህና በሌሎች ድርሰቶቹ የሚያሳየን የድሆችንና የታናናሽ ሰዎችን ሥነ ሕይወት ነው፡፡ ድሆቹ የመንግሥት ሠራተኞች፤ አርሶ አደሮች፤ ተማሪዎች፤ ወታደሮች በሥራው ላይ ይንጸባረቃሉ፡፡ ቅብጥብጧ በሚለው ድርሰቱ የተሳሉት በኑሮዋቸው ሻል ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ቅብጥብጧ ለሚለው ርእስ ዋና ባለጉዳይ (ገጸ ባሕርይ ) ዝነኛ ሠዓሊ ለመሆን የምትፍጨረጨረው ኦልጋ ኢቫኖቭና ናት፡፡ ምንም የሌለው ተራ ሰው የሆነውንና የሕክምና ባለሙያውን ዶክተር ኦሲፕ ስቲፓኖቪች ዲሞቭን በማግባቷ ትቆጫለች፤ ታዝናለች፡፡ ለእርሱ ሙያም ክብር አትሰጥም፡፡ የኪነ ጥበብ ፍቅር ያላት ኦልጋ የሥዕል ሙያ ለመለማመድ ብላና ወደ ቮልጋ ወንዝ ዳርቻ ሄዳ ከታዋቂው ሠዓሊ ከርያቮቭኪ ጋር በፍቅር ትወድቃለች፡፡ እርሱ ግን ሙሉ ልቡን ባይሰጣትም በእርሱ ግፊት ወደ ባለቤቷ ከተመለሰች በኋላ ልቧ ይከፈልባታል፡፡ በስውር የፈጸመችውን የፍቅር ግንኙነት ተጸጽታ ለባለቤቷ ለመንገር ብታስብም ወኔ ይከዳታል፡፡ ከመኻል ባለቤቷ ዲሞቭ ታምሞ ይሞታል፡፡ ኦልጋ ኢቫኖቭናም በጸጸት ትገረፋለች፡፡
ለማኙ በሚለው ትረካ አንድ ቡትቶ ለባሽ ተማሪና አስተማሪ ነበርኩ፤ ክፍለ ሀገር ሥራ አግኝቼ መሄጃ ገንዘብ አጣሁ (እዚህ ሀገራችንም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሞልተዋል) እያለ ሲያታልል ያገኘው ስክቮርሶቭ የተባለ ደግ አሳቢ ሰው እቤቱ እየወሰደው እንጨት እንዲፈልጥ፤ እንዲረበርብ፤ በረዶ እንዲጠርግ፤ ምንጣፍ እንዲያራግፍ፤ ፍራሽ እንዲያናፍስ ያደርገዋል፡፡ ግን አቅመ ቢስ መሆኑን የቤት ሠራተኛው ስለተረዳች በብዙ ታግዘዋለች፡፡
የጽሕፈት ሥራ የሚችል መሆኑን ጠይቆም በጽሑፍ ገልባጭነት እንዲሠራ ወደሚያውቀው ሰው ይልከዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ኑሮው ሲሻሻልለት እናያለን፡፡ ፈንጠዝያ በተሰኘው ሥራ ሚትያ ኩልዳሮቭ የተባለ ወጣት በመላ ሩሲያ ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን ያለውን ምኞት ይገልጽልናል፡፡ ችግር ደርሶበት በጋዜጣ የወጣን አንድ ሰው ምሳሌ አድርጎ እንደርሱ ለመታወቅ ሚትያ ጋዜጣውን በኪሱ ይዞና በየደረሰበት እንኩ አንብቡት እያለ ስለታላቅነቱ ሲናገር እናያለን፡፡
የቃለ አጋኖ ምልክት በሚለው ትረካ ፔሬክላዲን የተባለውና ከአምስተኛ ክፍል የዘለለ ትምህርት የሌለው የቢሮ ሠራተኛና ጸሐፊ ለዐርባ ዐመት ሲሠራ የቃለ አጋኖ ምልክት እንዳላጋጠመው ይናገራል፡፡እንዲያውም ዘልቀው ከተማሩ ሰዎች በበለጠ እንደሚሠራና መማር አላስፈላጊ እንደሆነ እየተኩራራ ይናገራል፡፡ ነጠላ ሰረዝ፤ ድርብ ሰረዝ፤ ዐራት ነጥብ እነዚህ ሁሉ በሕልሙ ጭምር እየመጡ ሲጨነቅም እናያለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ያልተለመደ ሁኔታ በሚለው ድርሰት የአዋላጅዋን የማሪያ ፔትሮቭናን የሙያ ሥነ ምግባርና የኪርያኮቭን ገንዘብ ወዳድነቱንና የቤተሰብ ፍቅር አልባነቱን እናስተውላለን፡፡
ይኽ ምልከታ ለቅምሻ ያህል የቀረበ ሲሆን ጊዜ ላለመፍጀት ቀሪውን ከመጽሐፉ እናንብብ፡፡ ከአርትዖት ያመለጡና ወደፊት ሊስተካከሉ የሚችሉ አንዳንድ ጥቃቅን የቃላትና የአባባል ዓይነቶችን አስተውያለሁ፡፡ አቶ ያሬድ ገብረ ሚካኤል የተባሉ ሰው አሉ እንደሚባለው ፍየልና ፊደል ተጠብቀው አይቻልም፡፡ በቤተ ክህነቱ ትምህርት ላላለፈ ሰው ሆሄያት በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ወይዘሮ ትዕግሥትን ጠንቃቃ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌም ሥዕል፤ ፀሐይ፤ መሐላ፤ ዓይን፤ ኃጢአት፤ ዓመታት-----የመሳሰሉትን ቃላት እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ የአጻጻፍ ሥርዓት በመጻፋቸው አንድም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ፤ አንድም የቤተ ክህነት ትምህርት ቢኖራቸው ነው ብየ ገመትሁ፡፡
ነገር ግን ወደ ፊት የሚታዩ አንዳንድ ጥቃቅን ግድፈቶችን አስተውያለሁ፡፡ ፀሐፊ ተውኔት (ገጽ 12 ጸሐፌ ተውኔት ቢባል) ሙሽራው፤ (ገጽ 25 ሙሺሪት )፤ አርት፤ አርቲስት (ገጽ 25 30) የሚለው በአማርኛ ቢጻፍ፤ ኒሻን ነው ወይስ ሊሻን (ገጽ28)፤ ሩህሩህ (ገጽ 30 ርኅሩኅ)፤ ተዋቶ (32 ተዋጥቶ)፤ ስማዩ (ገጽ 44 ሰማዩ)፤ ዘማናዊው(ገጽ 47 ዘመናዊው)፤ ቀደምቱ (ቀዳሚው)፤ ቀደምት የብዙ ቁጥር ነው ቀዳማውያን እንደማለት ነው፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች፤ ደራሲዎች፤ ተርጓሚዎች በዚህ ቃል ያለአግባብ ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ) ፤ቀደምት (ገጽ 60 ቀዳሚ)፤ መስዋዕት (ገጽ 63መሥዋዕት) ማስጠሎ (ገጽ 79 አስጠሊታ)፤ ሰቆቃ (ገጽ 86 ሰቆቃው) እኒህ በምሳሌነት የቀረቡ ናቸው፡፡
ለማንኛውም ወይዘሮ ትዕግሥት በጥረታቸው በቼሆቭ ብዕር ከተቃኘው ከሩሲያ ሥነ ሕይወት፤ አዳዲስ አስተሳሰብ፤ ገጸ ባሕርያትና የአተራረክ ብልኃት ጋር ስለአስተዋወቁን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡


No comments:

Post a Comment