Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

ቅድሚያ ለእሴቶች!


ቅድሚያ ለእሴቶች!
ሊድያ ተስፋዬ
«እንዴ እንኳንም ዘንቦብሽ...አለ የሀገሬ ሰው...»«ስነ ምግባር ደኅና ሰንብች...» «እንግዲህ ሀገሬ ሰለጠንን ባዮች ባህልሽን ሊያጨመላልቁልሽ ነው...» እነዚህና ሌሎች ከዘጠና አንድ በላይ አስተያየቶች ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በማኅበራዊ ድረ ገጽ /face book/ ይፋ ካደረገው መረጃ ስር ሰፍረዋል። እለተ አርብ መስከረም 25 ቀን 2011.ም ነው። መረጃው ደግሞ «ቅድመ-ምርመራ /ሳንሱር/ ተነስቷል» በሚል ርዕስ የተጻፈ ነው።
ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኃላፊነት በመጡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው ይህን ውሳኔ ያስተላለፉት። ይህ ውሳኔው በአግባቡ የታየና የተጤነ ነው ወይ? የሚለው በጥያቄነት የሚቆይ ሆኖ፤ በዚህ ዜና የተደሰቱ እንዳሉ ሁሉ ግን እጅግ በርካቶችም ስጋት ገብቷቸዋል። በመሃልም በቀደመው ጊዜ የነበረው የፊልም «ግምገማ» ነበር ወይ? የሚሉም አልጠፉ።
«ከዚህ በፊት በሙያዊ እይታ የአእምሮ ህሙማንን በትክክል አልገለጸም ብለን ያየነው ፊልም ወጥቶ ነበር። ያኔ ግን ፊልሙ ከእይታ መነሳት አለበት በሚል ሳይሆን ሰው ፊልሙን ሲመለከት ችግሮቹንም አብሮ እንዲያይ ማድረግና ፊልም ጥናት ተደርጎ መሠራት አለበት የሚል ሃሳብ ነው የሰተጠው» ይላሉ ዶክተር ዳዊት አሰፋ።
ዶክተር ዳዊት ሳይካትሪስት እና የኢትዮጵያ አእምሮ ህክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው። በእርሳቸው እይታ ፊልሞች ለብዙኅኑ እይታ ከመቅረባቸው በፊት በቅድመ ግምገማ ማለፋቸው «ሳንሱር» ነው ወይስ አይደለም የሚለው እንደአተያዩ ይለያያል። አክለውም ክልከላ እና ቁጥጥር መኖሩ ብቻ በዘርፉ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣትና ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ መፍትሄ አይሆንም።
«ቅድመ ምልከታው በመነሳቱ ምክንያት እስከአሁን ከነበረው የበለጠ ጎጂ ነገር ይመጣል ብዬ አላስብም። በዛም ያመጣነው ለውጥና ያዳበርነው ነገር የለም» ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ አንድ ማኅበረሰብ ሃሳቡን መግለጥ እስከቻለ ድረስ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ሃሳቦች ይኖራሉ። እነዛ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ ሲሄዱ በፊልሙ ዘርፍ እድገት ማየት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
ይህ ግን የየዘርፉን ባለሙያ አስተያየት መጠየቁ አይቀሬ ነው። የፊልም አዘጋጆች እንደፊልሞቻቸው ጭብጥና ታሪኮች የህግ፣ የጤና፣ የስነልቦና ባለሙያዎችንና በቂ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ አካላትን ሃሳብ መካፈል ይኖርባቸዋል። ከዛ ባሻገር ግን የባህል እሴቶችና ማንነቶችም አሉ። ለማንነት የሚጨነቅና ለአገራዊ እሴት የሚሳሳ ደግሞ የፊልም ባለሙያዎች ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው ወይ? የሚለው ያሳስበዋል። የአገራችን ፊልሞች በብዛት ከባህርማዶ የተቀዱ መሆናቸው ማንነትን ሊሸረሽርና እሴቶችንም ሊያደበዝዝ ይችላልና።
አቶ ሰለሞን ደኑ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቀድሞ የፊልም እና የቴአትር አሁን ደግሞ የባህል አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥ ባለሙያ ናቸው። በክፍሉ ሥራ ከጀመሩባቸው ጥቂት ዓመታት ወዲህ በርካታ ፊልሞችን በቅድመ እይታ ተመልክተዋል፤ ገምግመዋል።
እርሳቸው እንደባለሙያ የብዙዎችን ስጋት ይጋራሉ። «ዚህ የነበረውና ፊልም የሚገመግም ባለሙያ የነበረውን ነገር ስለሚያውቀው ስጋት አለ። ነገር ግን እነሱም የሚታዩበትን አሠራረ በቀጣይ በከፍተኛ አመራሮች ታይቶ ውሳኔ የሚያገኝ ይመስለኛል» ይላሉ።
ከምንጩ ቅድመ ግምገማ በሳንሱር ስም እየታየ መሆኑንም ያነሳሉ። ግምገማ መቅረቱን ይፋ ያደረገው ደብዳቤ ከበላይ አመራር እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ፊልሞች ከይዘት አንጻር ቅድመ ምልከታ ይደረግባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህም ከእጽ ተጠቃሚነት፣ ከሴቶች፣ ግልጽ ወሲብ የሚያሳዩ ትዕይንቶችንና ወደዛ ገፋፊ ንግግሮች ከማስወጣት፣ እንዲሁም ከሃይማኖትና ከብሔር አንጻር ለማኅበረሰቡ የሚልከው መልዕክት አግባበ አይደለም የተባለ ትዕይንት በምልከታው ስር ይወድቃል።
«ይህን የምናደርገው ኅብረተሰቡን ለመጠበቅና ማኅበረሰቡ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ነው» ይላሉ አቶ ሰለሞን፤ የሳንሱር ባህሪ ያላቸው አሠራሮች የታዩበት ጊዜ መኖሩንም ሳይገልጹ አላለፉም። «ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ንክኪ ያለው ሆኖ የታገደ ፊልም አለ። በአብዛኛው ግን በቢሮው ባህልና እሴቶች እንዲጠበቁ የማድረግ ሥራ ነው የሚሠራው» ሲሉ አክለዋል።
ምንአልባትም ፊልሞች ላይ ከዚህ ቀደም ቅድመ ምልከታ ሊያደርግ የተቀመጠ ቡድን ሥራውን በአግባብ ሊያከናውን አለመቻሉ፤ ከባህል አንጻር ማየት ሲኖርበት የፖለቲካ እይታ ውስጥ መግባቱ ለዛሬ አድርሶናል ማለት ይቻላል። የሆነው ሆኖ ግን ውሳኔው ስጋት ለገባቸው መፍትሄ ያስቀመጠ አይደለም። አቶ ሰለሞን እንዳሉት ግን ይህ ቅድመ ግምገማ መነሳቱ ጥፋት ያጠፋ ሰው ወይም ባለሙያ በህግ አይጠየቅም ማለት አይደለም።
«ፊልም ሠሪዎች ከሌላው ይልቅ አሁን ጫናው እነርሱ ላይ ነው፤ ኃላፊነቱ የእነርሱ ሆኗል። መልካም ነገር ከሠሩ የሚመሰገኑበት ካልሆነ ደግሞ ተጠያቂም የሚሆኑበት ነው» ብለዋል። ይህ ማለት ተመልካቹና ፊልም አፍቃሪው ተስፋውንና ጠባቆቱን በፊልም ባለሙያዎች ላይ ብቻ አኑሯል ማለት ነው። ፊልሞችም ከዚህ በኋላ ለቅድመ እይታም ሆነ የእይታና የስርጭት ፈቃድ ለመውሰድ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አያቀኑም።
በባህልና ቱሪዝም ቢሮው የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ስዩም ተመስገን በበኩላቸው ቅድመ ምልከታው ቢነሳም ማኅበረሰቡ ጥበቃ ማግኘት አለበት ብለዋል። «ሁሉም ፊልሞች አስተማሪ ላይሆኑ ይችላሉ። የማኅበረሰብን የተለያዩ እሴቶች ሊሸረሽሩ የሚችሉ በገንዘብ ላይ ብቻ የተመሰረቱ ገንዘብ ላይ መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ሊሰራጩ ይችላሉ። ከተሰራጨ በኋላ መቆም ከባድ ነው» አያየዘው የተናገሩት ነው።
ሉላዊነት በሰለጠነበት በዚህ ጊዜ አገራዊ እሴቶችን የሚሸረሽሩ የባሀርማዶ ሥራዎችን ተጽእኖ መቋቋም እንዳልተቻለ ያስታወሱት አቶ ስዩም፤ ፊልሞችን የሚሄስ እንጂ የባለሙያውን መብትም ሆነ ስሜት የማይነካ አሠራር ሊበጅ ይገባል ብለዋል።
ጥያቄው ይህን ማን ያደርገዋል የሚለው ነው። ባለድርሻ አካላት የሚያቋቁሙትና ሙያዊ አስተያየት የሚሰጥ ቡድን፤ ከባህል እሴቶች አንጻር በኃላፊነት እንዲሠራ የሚያሳስብ ማኅበር ወይም ሌላ። ለፊልም ዘርፍ እድገት፣ ቅድሚያ ለአገር እሴት ስለመስጠት ውሳኔውን ያስተላለፈው የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አመራር ከዚህ በኋላ ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ እንደሚወስኑ ስጋት የገባቸው ብዙዎች በተስፋ እየጠበቁ ነው።

No comments:

Post a Comment