Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

‹‹ባዶ እግር›› በሙሉ ጭንቅላት


‹‹ባዶ እግር›› በሙሉ ጭንቅላት
ዋለልኝ አየለ
ይህ የሶቅራጥስ ታሪክ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ፈላስፋ ነው፡፡ ፈላስፋ ነው ማለት ጭንቅላቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ፍልስፍና ማለት ሁሌም መጠየቅና መመራመር መሆኑን ደግሞ የፍልስፍና ምሁራን ነግረውናል፡፡
ሶቅራጥስ በግሪክ የኖረ ፈላስፋ ነው፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት የነበረው ሶቅራጥስ በአቴና ከተማ ስሙ የገነነ ሲሆን የመጨረሻዎቹ ሕይወቱ ግን በችግር የተሞሉ ሆኑ፡፡ በባዶ እግሩ በአቴንስ ጎዳና መኳተን ጀመረ፡፡ ይህም ለባለቤቱ ዛንቲኘ እና ለልጆቹ ሀፍረትና መሸማቀቅን ፈጠረ፡፡ እሱ ግን ፍልስፍናውን ቀጥሏል፡፡
ሶቅራጥስ ይህን ያህል ምን አደከመው ነበር? ‹‹እውነት ምንድነው?›› ብሎ ስለጠየቀ የደረሰበት መከራ ነዋ! የአቴንስን ፈላጭ ቆራጭ መንግስት መጋፈጥ ጀመረ፡፡ የአካባቢው ገዥዎች ከባድ ስጋት ተደቀነባቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ይሁን?›› ብለው ሲያስቡ መፍትሔው ሶቅራጥስን ማስወገድ ብቻ መስሎ ታያቸው፡፡ እነዚህን ሁለት አማራጮች ብቻ ሰጡት፡፡ አቴንስን ለቆ መሰደድ ወይም ሞት! የሚወደውን የአቴንስ ህዝብ ለቆ ከመሄድ የሞት ፍርድን መቀበል ለሶቅራጥስ ተመራጭ ነበር፡፡
ይህኔ ታዲያ የወዳጅ ዘመድ ምክር አልጠፋም፡፡ ‹‹ኧረ ባክህ ተሰደድና ሕይወትህን አትርፍ›› ተባለ፡፡ እሱ ግን አላደረገውም፡፡
እንዲህም አለ፡፡ ‹‹እኔ ለአቴናውያን ከአማልዕክቱ የተላኩ ተናዳፊ ዝንብ ነኝ፤ መንግስት ከስልጣኑ ብዛት የተነሳ ኃላፊነቱን ዘንግቶ እንደሚሰባ በሬ እየወፈረ እንዳይተኛ እኔ እየነደፍኩ አነቃዋለሁ፡፡ እኔን ከገደላችሁኝ ግን መንግስትን የሚያነቃና የሚቆነጥጥ ሌላ ሰው አታገኙም፡፡ ያን ጊዜ መንግስት በእናንተ ላይ አንባገነን ይሆናል››
‹‹ባዶ እግር›› ቴአትር ነው፡፡ በታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ሶቅራጠስ ህይወትና አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ቴአትር፡፡ ተውኔቱን ማክስዌል አንደርሰን የተባለ አሜሪካዊ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1951 Barefoot in Athens በሚል ርዕስ ጻፈው፡፡ በዚሁ አቆጣጠር በ1966 ደግሞ ወደ ፊልም ተቀይሯል፡፡

አሁን ‹‹ባዶ እግር›› ቴአትርን በአገራችን እንየው፡፡ ድርሰቱን ‹‹ባዶ እግር›› ሲል የአማርኛ ትርጉም የሰጠልን አስቻለው ፈቀደ ነው፡፡ ቴአትሩ ዘወትር እሁድ በ800 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲታይ ቆይቷል፤ ወደፊትም እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡
«ባዶ እግር» ቴአትርን ያዘጋጀችው ራሄል ተሾመ መሀመድ ስትሆን የአርትዖት ሥራውን የሰሩት ደበበ እሸቱና ራሷ ራሄል ናቸው፡፡ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡
‹‹ባዶ እግር›› ቴአትር በታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ አገር ግሪክ ሄዶ ታይቶ መጥቷል፡፡ ወደ ግሪክ የሄደው የልዑካን ቡድንም ባሳለፍነው ሳምንት በብሔራዊ ቴአትር አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ለመሆኑ ይህ በኢትዮጵያውያን የተሰራውና በእንቁ ፈላስፋቸው ሶቅራጠስ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ቴአትር ሲቀርብላቸው ምን ብለው ይሆን? ተደምመው ተደንቀው ‹‹ለካ ቴአትርም እንዲህ ይሰራል እንዴ!›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡
እንግዲህ አርቲሰት ደበበ እሸቱ ነው በተዋዛ አነጋገሩ ታዳሚውን ሲያስቀው የነበረው፡፡ ‹‹አስተማርናቸው እንጂ አላስተማሩንም›› ያለው ጋሽ ደበበ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር ይሰራል እንዴ!›› ብለው ይጠይቁ የነበሩ አገራት መልሱን አግኝተውታል፡፡ አፍሪካ ውስጥ የነበሩ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ አገሮች ራሳቸውን ‹‹ፍራንኮ ፎን›› ነን ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ የነበሩት ደግሞ ‹‹አንገሎ ፎን›› ነን ብለው ያምናሉ፡፡ ለማሳየት ወደ ውጭ አገራትም ሲሄዱ የሚያሳዩት በውጭ ቋንቋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ቅኝ ለመገዛቷን በራሷ ቋንቋ በመጠቀም አስመሰከረች፡፡
ባዶ እግር ቴአትር በአቴንስ ከተማ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው የታየው፡፡ የራሳቸው ቋንቋ በ‹‹ሰብታይትል›› ነው የታየው፡፡ በአማርኛ ተጻፈ፤ በአማርኛ ተተወነ፡፡ ቴአትሩን በአቴንስ 5 ሺህ ሰው ተመልክቶታል፡፡ የግሪክ ጋዜጦች የፊት ለፊት ገጻቸው ላይ ይዘውት ወጥተዋል፡፡
ግሪኮች በዚህ ቴአትር ይዘት ላይ ብቻ አልነበረም የተገረሙት፡፡ በኢትዮጵያውያን እምነትና ባህልም እጅግ ተደንቀዋል፡፡ ይህን አጋጣሚ መናገር የግድ ነው፡፡ አጋጣሚውን የተናገሩት የልዑካን ቡድኑ መሪና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ አስረስ ናቸው፡፡
ቴአትሩ የታየው በአውሮፓውያን አቆጣጠር ኦክቶበር 1 ነው፡፡ ይህ ወቅት በግሪኮች ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ የሚታይበት ነፋስና የመሬት መንሸራተት የሚከሰትበት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የእምነት ሰዎች ናቸውና በዚህ ዕለት ምንም ነገር እንዳይከሰት ‹‹ጸልዩልን›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ የፈረንጆቹ ኦክቶበር 1 ማለት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መስከረም 21 ማለት ነው፡፡ መስከረም 21 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የቅድስት ድንግል ማርያም ንግስ ነው፡፡
ቴአትሩ እንደ ነገ ሊታይ ከማታ ጀምሮ ነው ጸልዩልን የተባለው፡፡ ሁሉም በየእምነቱ ‹‹እባክህ ደህና ቀን አድርገው!›› እያለ ፈጣሪውን ይማጸን ጀመር፡፡ አመሻሽ አካባቢ ነፋስ ይነስፍ ጀመር፡፡ ሥጋት ፈጠረ፡፡ እንደተለመደው ቢሆን ኖሮ እያደር ይብስበትና ኦክቶበር ወር ሲገባ ከባድ ነውጥ ይፈጠር ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ግን በተቃራኒው ሆነ፡፡ ነፋሱ እየባሰው ሳይሆን እየቀነሰ ሄደ፤ ጠዋት ጭራሹንም ድራሹ ጠፋ፡፡ በዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ ግርምት ተፈጥሮባቸዋል፡፡
ከዚህ አንድ ነገር እንረዳለን፡፡ ኢትዮጵያ በእምነት፣ በባህል በቋንቋ ያልተበረዘችና ድንቅ መሆኗን ማወቃቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች አገርን ያስተዋውቃሉና የጥበብ ሰዎችን በርቱልን እንበላቸው!


No comments:

Post a Comment