Translate/ተርጉም

Tuesday, October 30, 2018

ጓደኛማቾቹ


ጓደኛማቾቹ
ሊድያ ተስፋዬ
«እኔ እንደ እናንተ ዓይነት የጓደኝነት ሕይወት ባሳልፍ ደስ ይለኝ ነበር...ማለቴ ጓደኛ ብትኖረኝና እንዲህ ብዙ ዘመን አብረን ብንኖር» አልኳቸው፤ ከልቤ ነበር። በእትዬ የሻሽወርቅና እትዬ አደላሽ እቀናለሁ፤ ያው የምቀኛ ቅናት ሳይሆን መንፈሳዊ ቅናት ነው። ከአርባ ዓመታት በላይ በጠበቀ ጓደኝነት አሳልፈዋል'ኮ፤ እንዴት አልቀናባቸው?
በእኔ ዘመንና ጊዜ ዘላቂ ጓደኛ መሆንም ማግኘትም ከባድ ነው፤ ይባላል። ደግሞ አንዳንዴ ነገሩ ሁሉ ግራ ይሆንና ጥሩ ጓደኛ ስትሆኑ በምላሹ እንደዛ ያለ አታገኙም፤ ወይ ታገኙና እናንተ የልብ ጓደኛ መሆን ሳትችሉ ትቀራላችሁ። ይህ እንዲህ ባለበት ሁኔታ በእነ እትዬ ያልቀናሁ በማን ልቀና ነው? ከልብ የሚዋደዱ፣ ሳይተያዩ የማይውሉ፣ የማይተማመኑ፣ ደስታውንም ሃዘኑንም ህመሙንም የሚጋሩ...እስከ እርጅና ጓደኝነታቸውን ያዘለቁ ሰዎች።
«ቆይ አንቺ አንድም የልብ ጓደኛ የለኝም ነው የምትይውመላኩ ጠየቀኝ፤ ከሁለት ሳምንታት በላይ በሥራ ምክንያት ከቤት ርቄ ያላየሁትን የመላኩን ገጽ ለአፍታ ልብ ብዬ አየሁት፤ ጥያቄውን ሰምቻለሁ...ጓደኛ አለኝ እንዴ? ማለቴ ብዙ የሥራ ባልደረቦች፣ አብሮ አደጎች፣ ትምህርት ቤት በአንድ ክፍል የተማርን የትምህርት ቤት ልጆች ወይም በጉዞ ምክንያት ወዳጅነታችን የጠነከረ...ብዙ ሰዎች አሉ። ግን ጓደኞቼ ናቸው? ጓደኛቸው ነኝ?
«እነ እትዬ ፊት ስሆን ጓደኛ አለኝ አልልም። ማለት በዛ ልክ የምሆንላት ወይም የምሆንለት ጓደኛ የለኝም» አልኩኝ። መላኩ በግርምት እይታ አይቶኝ ሳቀ። «ምን ያስቅሃልመታ አደረግኩት፤ «ጓደኞች ቢኖሩሽማ እዚህ ከእናቶቻችን ጋር ቡና አትጠጪም ነበር» አለኝና ጮክ ብሎ ሳቀ። እነእትዬም ተቀብለውት ሳቁ እንጂ የቀለደው በእነርሱ እንደሆነ እንኳ አልተሰማቸው፤ ወይስ እኔ ነኝ የመሰለኝ?
«ሳይታወቅሽ ቀርቶ ነው እንጂ አንድ ጓደኛማ ሳትኖርሽ ቀርታ አይደለም...አንዳንዴ አጠገብሽ እያሉ የሚያደርጉልሽንና የሚሆኑልሽን ልብ ሳትይ ቀርተሽ...ምንም ምላሽ ሳትሰጪ የምታጫቸው ብዙ ጓደኞች ይኖራሉ። እንደዛ ይሆናል ልጄ...እንጂማ ያውም በአንቺ ሥራ መች ጓደኛ ይታጣል» እትዬ አደላሽ ሊያጽናኑኝ ፈልገው መሰለኝ፤ እንጂ የልብ ጓደኛ ማግኘት መታደል መሆኑን እንደማውቅ አልገባቸውም።
የልብ ጓደኛ ውድ ነው። ለምሳሌ እንዳልኳችሁ እኔን ውሰዱ፤ ከዚህ ቀደም በሠራሁባቸው ጥቂት መሥሪያ ቤቶች የልብ ጓደኛ ያገኘሁ መስሎኝ ነበር። ግን መሥሪያ ቤቱን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም፤ አንጠያየቅም። እድሜ 'ለፌስቡክ' ቢያንስ በሕይወት መኖራችንን ግን እናውቃለን። እነ እትዬ ግን ስልክ የለ፣ ፌስቡክ የለ፣ ቴሌግራም የለ ሜሴንጀር...እንደውም ጓደኝነታቸውን ያበረታው ምንም ለጓደኝነት የሚረዳ ነገር አለመኖሩ መሰለኝ። ብልሃት ያለው ከተቸገረ ሰው ዘንድ አይደለምን?
«የዚህችን ወዳጅ አልባ ታሪክ ከምንሰማ የእናንተን ንገሩን እማዬ...አይሻልምየተናገረው መላኩ ነው። ለዘብ ባለ ቁጣ መላኩን አየሁት፤ ሳቀብኝ። እንዲህ እናቱ ፊት ስንቀላለድ እናቱ ምን ያስቡ ይሆን? ወይም ምንአልባት ልክ እንደ እርሳቸውና እንደ እትዬ አደላሽ አርባ ዓመት ሙሉ የአንድ ሰፈር ልጆችና ጓደኛማቾች ሆነን የምንኖር ይመስላቸው ይሆን?
«የመጀመሪያ ቀን ያደረኩትን አልረሳም።...ሆሆይ! ይሄ ኃይለኛነቴ ያኔም ነበር ከባሌ ጋር አየኋት ብዬ አንዷን ሴት የስድብ መዓት አዥጎደጉድባታለሁ። ምን ያለችው ሴት እንደሆነች አላውቅም ከቤቷም አልወጣች። እናቴ ተይ ብላ ብትቆጣኝ...ባለቤቴ የቅርብ ወዳጄ ናት ቢለኝ ልሰማ ነው...ታድያ የዛች ሴት ትዕግስት፣ ዝምታዋ ሊያናድደኝ ሲገባ እንደውም ጭራሹን አስገረመችኝ...» እትዬ የሻሽወርቅ ለብቻቸው እየሳቁ አደላሽን ተመለከቱ።
«አንቺ ጉደኛ መቼም ረሳሁት ትይኝ ይሆናልኮሳቃቸውን ገታ ለማድረግ እየሞከሩ፤ «አሃ!ለምን ብዬ? ቂም መያዜን ዘነጋሽው እንዴ? የምሰድብበት አጋጣሚ አጥቼ ነው እንጂ አዘጋጅቼልሻለሁ...» እትዬ አደላሽ ደስ የሚለው ሳቃቸውን ሳቁ። አሳሳቃቸው እድሜያቸውን ያስመኛል፤ እንደእርሳቸው ትልቅ ሰው ሆኜ ስስቅ እንደእርሳቸው ደስ የሚል በሆንኩ ያስብላል። ወይም እንደ ህጻን ልጅ ፈገግታ ሳቃቸው ያሳሳል፤ ፈገግታቸውን ለማየት ቀኑን ሙሉ ስቀልድ ብውልስ ያሰኛል።
«እንዴ እማዬ? እትዬን ነው እንዴ የሰደብሽውመላኩ በግርምት ጠየቀ፤ «እርሷ መሆኗን መች አውቄ፤ ብቻ ተራግሜ ተሳድቤ ሳበቃ ንዴት ፊቷን ያቀላው አንዲት ሴት እንባ በዓይኗ ሞልቶ ከቤቱ ወጣች። ቅዱስ ገብርኤልን ነው የምላችሁ ልጆቼ! እንደዛን ቀን በድንጋጤ ከሁለት ተከፍዬ አላውቅም። እንደው ያሰብኩትን ክፉ ክፉ ሃሳብ ሁሉ እርግፍ አድርጌ ረሳሁና ጭራሹን አዘንኩላት...»
እትዬ አደላሽ ቀበል ብለው ቀጠሉ፤ «አይ! እንደው ስታጋንን እንጂ የዚህን ያህል ጭቁንና ምስኪን ሆኜ ነው? ተይ እንጂ የሻሽ...በስንቱ ሆድ ብሶኝ ስለነበር ነው...» ከአርባ ዓመት በፊት የሆነውን ዛሬ የተከሰተ ያህል ምስል ፈጥረው ይጨዋወቱት ጀመር።
«ብቻ ሆዴ ስስት አለላትና ስድቤን ወደ ባሌ አዞርኩታ! አትናገርም ወይ? ለምንድን ነው ሴቶቹን የምታጣላን? የምታባላንብዬ አቅጣጫ ቀይሬ የሷ ወዳጅ ሆኜ ቁጭ። ከዛን ቀን በኋላ ነገሩም በረደ፤ ነፍሱን ይማረው ባለቤቴም ይኸው የለም፤ እኔ ግን ወዳጅ አተረፍኩ። መሰንበት ደግ ነው...አሁን ብቻዬን ብሆን እንዴት ነበር የምኖረውአሉ እትዬ የሻሽ አደላሽን እያዩ፤ ሁለቱ እርጅና የተጫጫናቸው እናቶች በፈገግታ ተግባቡ።
«ደስ ትላላችሁ...መቼም መጽሐፉ መሃሉ አይነገርም እንዲል ብዙ እንዳሳለፋችሁ አልጠራጠርም። እንደ እናንተ ዓይነት ጓደኝነት ማግኘት መታደል ነው። ስለማውቃችሁ እድለኛ ነኝ፤ አንድ ቀን ታሪካችሁን በዝርዝር አውጥቼ ለሰው መናገሬ አይቀርም» አልኳቸው፤ ርዕሰ ጉዳዩ ነው መሰለኝ ምላስ አብዝቻለሁ። ቢሆንም ከወሬኛነት የተቆጠረ ሳይሆን ከቁምነገር የተሰለፈ በመሆኑ ማንም ልብ አላለውም።
«እና ምን ትመክሩናላችሁአለ መላኩ፤ እኔን እያየ። «ማለቴ ለምሳሌ እኔና ሜሪ በጓደኝነት አብረን እንድንቆይና አርባ ዓመታትን አብረን እንድናሳልፍ ምን ትመክሩናላችሁይህን ነገር ልጠይቅ እፈልግ ነበር? ሲጀመር እኔ ጓደኛው እንድሆን ነው እንዴ የሚፈልገው? በእርግጥ እሱም ቢሆን ክብር ነው፤ ያቺ አንድ ሰሞን ከስር ከስሩ የምትለዋ ልጅ ማን እንደሆነች አላውቅም። ጓደኛው ሆኖ መቆየቱን መጥላት የለብኝም መሰለኝ።
«የሻሽን አውቃታለሁ...ጓደኝነትን ለማጽናት ዋናው ቁምነገር መተዋወቅ ነው። የግድ አመሌ እንዲህ ነው...ፀባዬ እንዲያ ነው መባባል አይደለም፤ በሁኔታዎች በየእለቱ የሚገለጥ በመሆኑ ጸባይን መተዋወቅ ያስፈልጋል። ከዛ መቀራረቡ...ከዛ መከባበሩ...ከዛ የጠበቀ ወዳጅነቱ ይከታተሉና ይመጣሉ።
ጓደኛዬ ካልከው ሰው ጋር በአንዲት ጠባብ ማለፊያ መካከል ብትገናኙስ? ቅድሚያ ይሰጥሃል? ቅድሚያ ትሰጠዋለህ? ወይስ አብራችሁ መላ ትፈልጋላችሁ? ልጆቼ እኔና የሻሽ መጀመሪያ ተዋውቀናል። ኃይለኝነቷን ሳውቅ ዝምታዬን ተረድታለች። የእርሷ ኃይል ለእኔ ጥበቃ፤ የእኔ ዝምታ ለእርሷ ሞገስ ሆኖናል...አይይ! ዝምተኛ መሰልኩ እንጂ ነገር አረዝማለሁ።...ዝም በይ አትሉኝም እንዴእትዬ አደላሽ ለራሳቸው ሳቁ።
«የሰፈሩ ሰው ዝምተኛ እየመሰልሽው እንጂ ይህንንማ እኔ አውቃለሁ...» በድጋሚ ቤቱ በሳቅ ተሞላ። በጓደኝነታቸው የበለጠ ቀናሁ። ጓደኛ የሚመርጡት ቤተሰብ ነው፤ ስንት ሰው እንዲህ ቤተሰቤ የሚለውን ጓደኛ አግኝቷል? ስንት ሰው ለሌላው የልብ ጓደኛ ለመሆን ራሱን አዘጋጅቷል። እንዲህ «እኔነት» የበዛ በመሰለበት ዘመን የልብ ጓደኝነት ይገኝ ይሆን? ከአርባ ዓመት በኋላ መላኩንና እኔን ለመሳል ሞከርኩ። ጥያቄ ፈጠረብኝ፤ እኔስ የሌላ ሰው የልብ ጓደኛ ለመሆን እብቃ ይሆን? የሚል። «ለመሆኑ ዛሬ ስለጓደኝነት ጥያቄ ያነሳሽው...ምን አስበሽ ነውእትዬ የሻሽ ተነሳባቸው መሰለኝ፤ የቀዱትን ቡና ፉት እያሉ ጠየቁኝ። እንዴ? እኔ ነኝ እንዴ ጥያቄውን ያነሳሁት? ሰላም!

No comments:

Post a Comment