Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

ከቻይና ባህል ምን እንማራለን?


ከቻይና ባህል ምን እንማራለን?
ጽጌረዳ ጫንያለው
ቻይናውያን ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን የደገሱትን ሲበሉላቸው ያስደስታቸዋል። የሚያቀርቡበትም መንገድ እንደ ድሮው የኢትዮጵያን ባህል በገፍ ስለሆነ የወደዱትን እያነሱ ሲመገቡላቸው ይደሰታሉ። የእርስዎ ባህል የማይፈቅዳቸው በርካታ የምግብ ዓይነቶችን በገበታው ላይ ይመለከታሉ። ስለዚህም የመብላት ስሜትዎ ሊቀሰቀስ የሚችለው ቻይናዊ ከሆኑ ብቻ ነው።
በሥራ አጋጣሚ ወደቻይና ባቀናሁበት ወቅት መታዘብ እንደቻልኩት ጠረጴዛውን የሚሞላው የተመጣጠነ ምግብ ነው። የባህር ላይ ምግቦች ይበዛሉ። አትክልትና ፍራፍሬም እንዲሁ ይቀርባል። ከባህር ምግብ ውጪ እንደ የበሬና የበግ ስጋዎች በተለያየ መልኩ ተሠርተው እንዲመገቡ ይጋበዛሉ።
ቻይናውያን በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ብዙ ይበላሉ። ግን ያው እንደ እኛ ቁጭ ብለው ስለማያሳልፉ ምግቡ አይከብዳቸውም። የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን ስለሚሠሩ በቀላሉ እንዲፈጭና ወደሰውነታቸው እንዲዋሃድ ያደርጉታል።
ጸያፍና የማይፈቀድ የሚባል ምግብ በእነርሱ ዘንድ ያለ አይመስለኝም። አንበጣ፣ ቅንቡርስና ዳክዬ እንዲሁም እንቁራሪት ተወዳጅ ምግቦቻቸው ናቸው። ፈረስና አህያም እንዲሁ ለትልልቅ እንግዶች የሚቀርቡ ምግብ እንደሆነ ይነገራል።
ቻይናውያንን ከዚህ ለየት የሚያደርጋቸው የየአገሩን ባህል የሚያከብሩ መሆናቸው ነው። እንደ አገራቸው ባህል ሁሉ የሌላውንም ያከብራሉ። ስለዚህም ምንም እንኳን ባህላዊ ምግባቸውን ቢያቀርቡም ያልተመቸዎት ከሆነ አያስገድዱም፤ የሚመርጡትን በቻ እንዲመገቡ ይጋበዛሉ ። በተለይ የሚያስገርመው ከተለመደው ወጣ ያለ አመጋገብን ይበልጥ ይወዳሉ ለመሞከርና ለመመገብም ጥረት ያደርጋሉ።
ከምግባቸው ወጣ ስንል የምናገኘው የሥራ ባህላቸውን ነው። አዛውንት፣ ወጣት፣ ሴት ወንድ ብሎ ነገር በሥራ ላይ ልዩነት የለውም። ሁሉም የቻለውን መሥራት እንዳለበት ያምናሉ። ለዚህም ይመስላል በቻይና ባህል ገና የ15 ዓመት ልጅ እንዳሉ ወንዱም ሆነ ሴቷ ትዳር እንዲመሠርቱ የሚደረገው። የእኛ የጎበኝበት ወቅት የሰርግ ሳይሆን አይቀርም አመሻሽ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተጠቀሱት የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ታዳጊዎች ሰርጋቸውን ሲያደርጉ ይታያሉ።
የፎቶ መነሳት ፕሮግራማቸው በእጅጉ ፈገግ ያሰኛል። ምክንያቱም እንዴት መተቃቀፍና ፎቶ መነሳት እንዳለባቸው እንኳን በቅጡ አያውቁም፤ ፎቶ አንሽው እንዲህ ሁኑ እያለ ሲመራቸው ይስተካከላሉ እንጂ። እድሜያቸው ለጋ ሆኖ ሳለ ጋብቻ የመፈጸማቸው ነገር ሁላችንንም ያስገረመን ነበር። እናም አስጎብኛችንን «ለመሆኑ ገና በዚህ እድሜ ለምን ይጋባሉስንል ጥያቄ አነሳን።
እርሷም ሥራን መልመድ ያለባቸውና ኃላፊነትን መሸከም የሚገባቸው ገና በወጣትነታቸው ነው ተብሎ እንደሚታመን ነገረችን። ከወጣቱ ሻገር ስንል ደግሞ ቻይናውያን አዛውንቶችን እናገኛለን። ቁጭ ብሎ መዋልና መስራት የህይወት ልምዳቸው እንደሆነ በአንድ ድርጅት ውስጥ በገባንበት ወቅት አረጋግጫለሁ። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ።
ይበልጡ ሴት አዛውንቶች ሲሆኑ፤ የወር ደሞዝተኛ ናቸው። ጥልፍ ይጠልፋሉ፤ ቦርሳ ይሰፋሉ፣ የተለያዩ ዲዛይን ያላቸው አበቦችን ይሠራሉ፤ የሚሠሯቸውን አበቦች ጎብኚዎች ሲመጡ በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ። ስለዚህ የቻይና የሥራ ባህል ለአንድ ወገን ብቻ የተተወ አይደለም። አዛውንቱ ደከመ ተብሎ እንዲቀመጥ አይፈቀድም፤ ልጆችም በሚችሉት መጠን እየሠሩ ነው ትምህርታቸውን የሚማሩት።
ንግድንና ሌሎች ጉዳዮችን ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር አስተሳስሮ የመሥራት ባህላቸውም የጠነከረ መሆኑም ሊወሰድ የሚገባው ጠቃሚ ባህላቸው ነው። የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው ሁኔታ ገና ላላያቸውና ድንገት ዐይኑ ላይ ላረፉ ተመልካች ሥራ ፈት ያስመስላቸዋል። እነርሱ ግን ዘወትር በሥራ ላይ ናቸው። ሥራዎችም የሚሠሩትና ማንኛውም ግዢ የሚፈጸመው በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ነው። በጥቅሉ የኑሮ ባህላቸው ከማህበራዊ ሚዲያው ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያ በእነርሱ ባህል የሥራ እንጂ የነቀፌታና ሥራ ለመፍታት የሚውል አይደለም። የውሸት መልዕክት ማስተላለፊያም አይፈቀድም። ቁም ነገር የታከለባቸውና የህይወት መስመራቸውን የሚያስተካክሉበት መንገዳቸው ነው።
ሌላው ስለ ቻይና ባህል ሳላነሳና ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ላመኑበት ወደኋላ አለማለታቸውን ነው። ይህንንም በሁለተኛው ቀን ጉብኝታችን አረጋግጫለሁ። የማይፈቀድ (forbidden) የሚል ስያሜ የተሰጠውን የቻይና ብሔራዊ ቤተመንግስት በጎበኘንበት ወቅት። ይህ ቤተመንግሥት ታላቁ የቻይና መሪ ማኦ የመሰረቱት ሲሆን፤ ማኦ ለቻይና ህዝብ ህይወትና መሰረት መሆናቸውን የሚመሰክሩበት ነው። በቻይና ታሪክ ከባድና ወሳኝ ውሳኔዎችን ካስተላለፉ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፤ ማኦ።
ማኦ ብዙ ሰዎችን በሙስና ምክንያት ገለዋል፤ በዝሙት ምክንያት የተከሰሱ ሰዎችን ብልት አስቆርጠዋል። ቤተመንግስታቸውም በአገሪቱ ሙስና የፈጸሙ፣ የአገር ህልውናን ለማጥፋት የተጣጣሩ፣ የሰረቁ፣ ሰዎችን የበደሉና አጸያፊ ተግባር የፈጸሙትን ሳይቀር አንገት ቆርጠዋል። ግን ቻይናዊያን ይህንን ያደረጉት በምክንያት ነው ይላሉ። ለዛሬ ቻይና ማደግ ይህ መሰረት ባይጣል ኖሮ ስኬት እንደማይመጣ ይናገራሉ። ስለዚህ ማኦን ትክክለኛው መሪያችንና የህዝባችን ህልውና ባለቤት ናቸው ይሏቸዋል።
ይህ ተግባራቸውን ማንም እንዲዘልፍባቸው አይፈቅዱም፤ ይልቁንም ቤተመንግሥታቸውን ባማረ ጥበባቸው አሸብርቀው ሰርተውላቸዋል። የእርሳቸውን መርህ እንዲከተልና ሙስናና አገር መክዳትን የሚጸየፍ ማህበረሰብ እንዲኖራቸውም እርሳቸውን አብነት እያደረጉ ማህበረሰባቸውን ያስተምራሉ። «የማኦን እምነት የሚከተል ወጣት መኖር አለበት፤ ነገር ግን በአዕምሮ መበልጸግ እንጂ መግደል ላይ መመስረት የለበትም» የሚል አቋም አላቸው። በዚህ ባህልም ከሙስና ይልቅ ሰርቶ ማግኘትን ምርጫቸው አድርገዋል።
ቻይናውያን ራሳቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙበት ጥበብም ሌላው ሊያስተምር የሚችል ባህላቸው ነው። የጫጉላ ቤቶች፣ የተጋቡበት ንብረቶችና መገልገያ ቁሶች በእጅጉ ተጠብቀው እንዲቆዩ፤ ያለአስተርጓሚ ጎብኝተው እንዲወጡ የተደረገበት መንገድ እጅጉን ያስገርማል። ለአብነት ገና ቤተመንግሥቱን ለመጎብኘት ሲገቡ ሁለመናውን በቀላሉ ሊረዱበት የሚችል ካርታ መግቢያው ላይ ተለጥፎ ይመለከታሉ። አንብበው ከጨረሱ በኋላ ወደ ክፍያ ጣቢያው ለደቂቃ ይጓዙና ልክ ገንዘቡን እንደከፈሉ ያለምንም ተንታኝና አስተርጓሚ የሚፈልጉትን መረጃ ለማግኘት የሚያስችል መረጃ ይደርስዎታል።
የሚፈልጉትን ቋንቋ ይመርጣሉ። እጅዎ ላይም ቀደም ሲል ያዩት ካርታ ድምጽ በሚሠራ መሣሪያ ታግዞና የጆሮ ማድመጫ ተጨምሮበት ይደርስዎታል። ከዚያማ ማንንም ሳይጠብቁ በድምጽ ብቻ ጉብኝትዎን ይቀጥላሉ። ማቆምና መረጃው መያዝ ከፈለጉም «ፖዝ» የሚለውን መጫን ነው የሚጠበቅብዎ፤ በዚህ ቦታ ሌላም አስደናቂ ነገር አለ። ጎብኚው የውጪ ዜጋ ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ መሆኑ ነው። እንደውም ከተለያዩ የቻይና ግዛቶች የሚመጡ ሰዎች እንደሚበዙ በሚያውለበልቡት ባንዲራ ይለያል።
ባህሌን ሌላ እንዲያውቀው ምን ላክልበት የሚለው ዜጋ በርካታ ነው። ለቻይናውያን ባህል ማለት ማንነት ነው። ስለዚህም በአካባቢ ተከፍሎ የአካባቢውን ባህል ለመሸጥና ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ለመልካም ነገር መፎካከርን ያሳያል። በባህላቸው ዓሳ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋልና በቻይና ዙሪያ ያሉ የከተማ ነዋሪዎች ባንዲራ አስመስለው እያውለበለቡ ከየት ግዛት እንደመጡ ያስተዋውቁበታል።
የአገር ውስጥ ጎብኚውም ቢሆን ከየት አካባቢ እንደመጣ ስለሚረዳ በትክክል ታሪኩን ለማወቅ ምርጫውን ፈልጎ ይጠጋል። በጉብኝት የእድሜ ገደብ የለም፤ አካል ጉዳትም አይወስንም። እንደውም ከጎብኝዎች መካከል ብዙዎቹ አዛውንቶች ናቸው።
ልጆቻቸውን ይዘው በሚገባ ታሪኩን የሚነግሩ ቻይናውያን ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። አካል ጉዳተኞች የሚስተናገዱበት አግባብም በእጅጉ ይለያል። ፍላጎታቸውን ማዕከል አድርጎ ከመንገድ ጀምሮ የተስተካከሉ መስመሮች አሏቸው። በዚያ መስመርም ተጠቅመው ጉብኝታቸውን እንዲያደርጉ ይደገፋሉ።
በራስ ቋንቋ ማደግ እንዴት እንደሚቻል ካስተማሩ አገራት መካከል ቻይናውያን ይጠቀሳሉ። በየትኛውም አገር ቢሄዱ ቻይናውያን የራሳቸውን ቋንቋ አይተውም። ይልቁንም ሌሎች እንዲያውቁትና በእነርሱ ቋንቋ እንዲግባቡ ያግዛሉ። ከፕሬዚዳንታቸው ጀምሮ ንግግራቸውም ሆነ ሥራቸው በቻይንኛ ብቻ ነው።
በመጨረሻ ከቻይና ልንማር ይገባል የምለው የሰነድ አያያዝ ባህላቸውን ነው። በቻይናውያን ዘንድ ምንም ዓይነት መረጃ ዋጋ አለው። በተለይም ታሪክ አስረጅ መረጃዎች ቦታቸው ላቅ ያለ ነው። ከዓመት ዓመት የሚሠሩ ሥራዎችና ለውጦች ለመጪው ትውልድ ተሰንደው ይቀመጣሉ። የድሮ የሚባሉበት ጊዜ ይመጣል ተብሎ ስለሚታመን አሁን ያሉ ማንኛውም ክስተቶች ይጻፋሉ። አምና የተመሰረተው ተቋም እንኳን በአንድ ዓመት ቆይታው ምን ይመስል እንደነበር ለጎብኝዎች የሚያስረዳበት ሁኔታ በስነድ የተቀመጠውን በማውጣት ነበር።
የዛሬውን ለነገ ለማስረከብ የዛሬውን ዛሬ እንሰንደው። ታሪክና ባህልን አውራሽ ዜጋም እንፍጠር ከቻይና ባህል የምንወስደው ልምድ ብዙ ነውናም እንጠቀምበት። ተግባራዊ ማድረግ እንቻልና ለለውጣችን አንድ እርምጃ እንራመድበት መልዕክቴ ነው። ሰላም!

No comments:

Post a Comment