Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

ምሥጋና እና አድናቆት- በሦስት ዘመን ሙዚቀኞች



ምሥጋና እና አድናቆት- በሦስት ዘመን ሙዚቀኞች
ዳንኤል ወልደኪዳን
ትውልድ ሰንሰለት ነው። አንዷ ማያያዣ ከላላች ወይም ከወለቀች ይበጠሳል፤ ቅጥልጥሎሹ ይቋረጣል። አንዷ ቀለበት ከሌላው ጋር የምታስተሳስረው እኩል ክብደትና አቅም ሲኖራት ብቻ ነው። ካልተመጣጠኑና ካልተመሳሰሉ ቅብብሎሹ ብዙ አይቀጥልም፤ አንድ ቦታ ላይ ይቋረጣል። በትውልድ ቅብሎሽና ቅጥልጥሎሽ ውስጥ መመሳሰልና መግባብት እጅግ ወሳኝ ቁምነገር ነው። ለትውልዱ ቀጣይነት ፊተኛውም ሆነ ኋለኛው በመሃል አንድ አሸጋጋሪ ትውልድ መኖሩ አይቀሬ ይሆናል።
ይህ የትውልድ ቅጥልጥሎሽ በሁሉም ሙያ ተመሳሳይነት አለው። የዛሬው ትኩረታችን ጥበብ ነው። ለዛሬ ጥበብ ጉልበት የትናንትና እና የትናንት በስቲያ መሰረት ወሳኝ ነው። ትናንትን ለነገ ለማሸጋገር ደግሞ ዛሬ እጅጉን አስፈላጊ ነው። ዛሬ ላይ በአግባቡ ያልታነጸ ጥብብ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሸጋገር ብቃት ሊኖረው አይችልም።
የሀገራችን የጥበብ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው ብዙ ጥበበኞች እልፍ መስዋእትነት ከፍለውበት ነው። የቀደሙት እንደ ሻማ ቀልጠው ለዛሬ ያደረሱትን ጥበብ ወደ ነገ የሚያሻግር ብርቱ የጥበብ ተረካቢና አድናቂ አንዲሁም አመስጋኝ ትውልድ ያስፈልጋል። ለዚህም ቅድሚያ ለሙያው ክብር የሚሰጡትን ሙያተኞች በማክበር፣ በማድነቅ እንዲሁም በማምስገን መጀመር ይቻላል።
ባለፈው ጊዜ «የወርቃማው ዘመን ወርቅ ድምጻውያን» በሚል መሪ ርዕስ በበዓል ዝግጅቶቻችን ላይ አንድ ቅኝት ማድረሳችን ይታወሳል። ዛሬም ከዛው ርዕሰ ጉዳይ ሳንሻገር ማክበርና ምስጋናን ታሳቢ ያደረገውን አንድ መርሃግብር ላስቃኛችሁ ወደድኩ።
አድናቆቴን የምጀመረው አሁንም ከፕሮግራሙ አዘጋጆች ነው። ብሬማን ፊልም ፕሮዳክሽን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር የሠሩት የመስቀል ዝግጅት ፍጹም ቁምነገር የለበሰ መዝናኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ለዚህ ቁምነገራም ሥራቸው ማመስገን ተገቢ ነውና ምስጋናችን ይድረሳቸው። የመረጃ ምንጨ ስለሆኑኝም የምስጋናው መነሻ ወደ አዘጋጆቹ ይደርስለኝ ዘንድ እየተመኘሁ ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመልሳችሁ።
ከሦስት ዘመን ሙዚቀኞች ጋር በምስል ወድምፅ መስኮት ውስጥ እንደታደምን ልብ በሉልኝ። የመስቀል ዕለት ይህችን ዓለም ተቀላቅሎ፤ አንደተከበረና እንደተወደደ ያለፍው ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ በመንፈስ፤ እንዲሁም የእነርሱን ዘመን ወካዩ የትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህምድ በአካል ተገኝተዋል።
በሁለተኛው ዘመን ደግሞ ሙዚቃን ከነክብሯ ተረክበው ያከበሯት የወርቃማው ዘመን ሙዚቀኞችን በመወከል ድምፃዊ ጸጋዬ እሸቱ፣ ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሃንስ፣ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ እና ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ተሰይመዋል። በመሃል አንድ የሙዚቃ ትውልድ ተዘሎ የዛሬዎቹን እንዲወክሉ ድምፃዊ ልዑል ሲሳይ እንዲሁም የ«እንደኛ»ዎቹ ድምፃዊት ራሄል ጌቱና ድምፃዊት ጠረፌ ካሳሁን(ኪያ) ተመርጠዋል።
ክብር ለትዝታው ንጉሥ
ዋናው የመርሃግብሩ ይዘት ማመስገን ላይ ትኩረቱን አድረጓል። ቀዳሚ ተመስጋኙ ከቀዳሚው ዘመን ሙዚቀኞች ማህሙድ አህመድ ነበር። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ማሳረፍ ከቻሉ ስመ ጥሩ ዘፋኞች ውስጥ አንዱ ነው፤ ማህሙድ።
ማህሙድን ዊኪፒዲያ እንዲህ ይገልፀዋል፤ «በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተደናቂነትን፣ ተፈቃሪነትን ማትረፍ የቻለ ፈርጥ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው ማህሙድ በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን ያዝናናል። ከአርባ ዓመታት በላይ በቆየው የሙዚቃ ሕይወቱ የተለያየ ትውልድን በሙዚቃው አንድ ላይ ማምጣት የቻለ ትልቅ አርቲስት ነው። በተለያዩ ኮንሠርቶች በሚዘፍንበት ወቅት በተለያዩ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል መልኩ አብረውት በመዝፈንም በዘፈኑ አንድነትን ያሳያሉ።
ማህሙድ የዝና ጣራ ላይ መድረስ ችሏል። በሕዝቡ ዘንድ ከመወደዱና ከመፈቀሩ በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ዝናው ናኝቷል። የአድማጮቹን ልብ አሸንፏል፤ ከኮንሠርቱ በፊት ቲኬቶቹ ተሸጦ የሚያልቅበት አጋጣሚም ብዙ ነው። የተለያዩ ሽልማቶችንም ለማሸነፍ ችሏል። ከእነዚህም ውስጥ የቢቢሲ ወርልድ ሚዩዚክ አዋርድ አንዱና ዋነኛው ነው። ምንም እንኳን ይሔን ያህል የጣራ ዝና ላይ ቢሆንም ትሁት፣ ሰዎችን የሚያከብርና በቀላሉም የሚግባባ ሰው ነው።»
አራቱም የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ሙዚቀኞች ለዚህ አንጋፋ ሙዚቀኛ የነበራቸው አድናቆትና አክብሮት የሚደንቅ ነበር። አዘጋጁ ብርሃኔ ጌታቸው(ሀረግ) በአማኑኤል ሆስፒታል በተዘጋጀው የአርት ቴራፒ ዝግጅቱ ላይ በመገኘት ህሙማኑን በሙዚቃ ያከመ፤ ሀገርና ህዝብ ወዳድ በመሆኑ ከዚህም በላይ ክብር የሚገባው ሙዚቀኛ መሆኑን መስክሯል።
ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሃንስ ማህሙድን ማሜ በማለት ይጠራዋል። አርቲስት ማህሙድ በዘመኑ ለነበሩ ሙዚቀኞች ብርታት በመሆን ለዛሬው ማንነታቸው ደጋፊ እንደሆናቸውም ይናገራል። አጋጣሚውን በመጠቀም ለማህሙድ ድንቅ አበርክቶ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ተንበርክኮ አድናቆቱን ሰጥቶታል።
«ከማህሙድ የሥራ ዲሲፒሊን መማር ይገባል። የማህሙድን የሙያ ስነምግባር ተናግሮ ለመጨርስ አይቻልም። በመጽሐፍ ተጽፎ የማያልቅ ታሪክ ያለው ነው። በተለይ በህዝብ ለህዝብ ወቅት እኛ የማናደርገውን ሁሉ በማድርግ ልብስ እስከማቀብል የደርሰ ድጋፍ ያደርግ ነበር» የሚለው ድምፃዊ ፀሐዬ «ማንብዬ ልሰይምሽ» የሚለውን ሙዚቃ ከእርሱ ጋር አብሮ ለመዝፈን ሲጠይቀው አላንገራገርም። «ማን ብዬ ልሰይምሽ፤ ምኑን ትቸ ማን ልበልሽ ፍፁም ድንቅ ልጅ ነሽ» የሚሉትን ስንኞች ብቻ እርሱ ካዜመው ሙዚቃ ጋር በማቀላቀሉ ደስታው ወደር አንዳልነበረው ይናገራል።
ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽም ማህሙድን ከእርሱ የወረሱት በርካታ ቁም ነገሮች ቢኖሩም የሥራ ሰዓት ማክበርን፤ የተጫወቱበትን የሙዚቃ መሣሪያ በአግባቡ መሰብሰብ ልዩ መገለጫው እንደነበር ይመሰክራል። እርሱ ያሳያቸውን ሙያ አክባሪነት እነርሱም ተጠቅመውበታል። እርሱ ያገኘውን ክብር ለማግኘት በኢትዮጵውያን ልብ ውስጥ ነግሦ መኖርን እንደተማረ ይናገራል። ከልቡ አመስግኖ ከዚህ የበለጠ እድሜና ጤና ተመኝቶለታል።
ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ ከማህሙድ ብዙ ነገር ወርሷል። በተለይም የእርሱን ጥንካሬ ወስዷል። አሁን ላለበት ስብእና መሰረቱ እርሱ እንደሆነም ያስባል። በተለይ በሰርግ ዜማወች ላይ ለመሥራት ከወሰነ በኋላ የእርሱን ጥንካሬና የእርሱን የሥራ ዲሲፒሊን መውረሱን ይናገራል። እርሱ ሁሉንም የሚያከብር ምርጥ ሙዚቀኛ በመሆኑ ፈጣሪ እድሜ እንዲሰጠው ተመኝቷል።
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ማህሙድ የትዝታ ንጉስ ብቻ ሳይሆን ትዝታን በተለያ አዘፋፈኖች ብዙ ጊዜ መዝፈኑን መስክሯል። «ንጉሥ መባል ሲያንሰው ነው። ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ አባት ነው ማለት ይቻላል» በማለት ከጥላሁን ጎን የሚሰለፍ ሙዚቀኛ መሆኑን መስክሯል።
ማህሙድ በበኩሉ የማይገባውን እንደሰጡት በመናገር የተሰጠውን ከብር ለኢትዮጵያ እንደተሰጠ ቆጥሮታል። መከበር ከማክበር አንደሚመነዘር ልብ ይሏል። የአሁኑ ትውልድ ወካይ ሙዚቀኞችም የማህሙድን ሙዚቃ በማዜም አድናቆታቸውን ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውንና ተተኪ እንዳለው እንዲያስብ አድርገውታል።
ክብር ለሙዚቃው ንጉሥ
የሙዚቃው ንጉሥ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ በህይወት ባይኖርም እርሱን የማክበር መርሃግብር የዝግጅቱ አካል ነበር። አዘጋጆቹ ጥላሁንን የገለፁበት መንገድ ማራኪ ነው። እንዲህም አሉ «መስከረም በጠባ ቁጥር በሰፊው ሊወራለት የሚገባ የሙዚቃ ሰው አለ። ወርሃ መስከረም ይህችን ዓለም የተቀላቀለ፤ በሙዚቃ ታሪክ ውስጥ መቼም የማይረሳ ዘላላማዊ አሻራ ያሳረፈ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ብሔራዊ አርማቸውን እንዲወዱ ያደረገ፤ የሀገር ፍቅር ዜማዎችን በስሜት ያቀነቀነ፤ ሀገሩን ከፍከፍ ሲያደርግ የነበረ ተወዳጁ ድምፃዊ ነው።
«ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ በሙዚቃ ዓለም ውስጥ ያላነሳቸው፣ ያልዳሰሳቸው፣ ያላዜመባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ተፈለገው አይገኙም። ከልጅነት እስከ እውቀት ሠርቶ ያለፋቸው ዘመን ተሻጋሪና አይረሴ ሥራዎቹ የሙዚቃው ንጉሥ የሚለውን ስያሜ እንዲቀዳጅ አድርገውታል። ሲያዜም ስለሀገር፣ ስለፍቅር፣ ስለማህበራዊ ህይወት፣ ስለፖለቲካ፣ ስለተፈጥሮ፣ ስለቤተሰብና የመሳሰሉትን ነፍስን በሚያስደስት ዜማ የተጫወተ ሰው የሙዚቃ ንጉሥ መባል ሲያንስበት እንጅ ማጋነን አይሆንበትም።
ሙዚቃ ለጥላሁን የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህይወት ቁስል ማከሚያ መደኃኒት መሆኑን የህይወት ዘመኑ ማሳያ ነው ሲሉ የሙያ አጋሮቹ ይመሰክራሉ። ኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግ መስዋእትነት ከከፈሉና ትግል ካደረጉ መካከል በግንባር ቀደምትነት ነው የሚጠራነው። ሁሉም ነገር በቂዬ ነው የሚለው ጥላሁን 'ሀብቴ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው' እያለ ሀገሩን የመክዳትና የመራቅ ሁኔታ ሳያሳይ ምድሯን ህዝቧን ታሪኳን ማንነቷን እያወዳደሰ 68 ዓመታትን ኖሮባት በክብር የተሸኘ የሙዚቃ ንጉሥ ነው»
ይህን ገለፃ ተከትሎ ማህሙድ ለጥላሁን ያለውን አድናቆት እንዲህ ገለፀ፤ «ዘፍኖ የማይጠግብ ሲዘፍን ድምፁ በሚፈልገው ዓይነት መቀያየር የሚችል ለዘፈን የተፈጠረ፤ እንደነሞዛርትና እንደነ ቤቶቨን በዓለም ላይ እንደሚጠሩት ታላላቅ ሙዚቀኞች መስመር ላይ የሚገኝ። ትውልድ የሚመሰክርለትና የሚያነሳው ጥላሁንን ነው። ጥላሁን በተነሳ ቁጥር እኛም ከኋላ መነሳታችን አይቀርም። እኔ ስነሳ የኔ ተከታዮች አብረው ይነሳሉ። መከባበሩም በዚሁ መንገድ ይቀጥላል»
ቴዎድሮስ ታደሰ፤ የከፍተኛ ኪነት አባል እያለ «የዛሬው ቴዎድሮስ ታደሰ የነገው ጥላሁን ገሰሰ» እያሉ ያስተዋውቁት እንዳነበር በማስታወስ፤ ጋሽ ጥላሁን «ልዩ ተስጥኦ ያለው ሰው ነው» በማለት በአጭር ቃል ገለፀው።
አረጋኸኝ ወራሽ በበኩሉ፤ «ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ የተሰጠ ስጦታ ነው። ጥላሁን ሞቶ የነገሠ ነው። ንግሥናው ሞቶ እንኳን ያልተወሰደበት ነው። በትውልድ ውስጥ ማሰልጠኛ ተቋም ሳይከፍት ራሱ ማሰልጠኛ ተቋም ያለው ሰው ነው። ብዙ ሰዎች አቅማቸው የሚታወቀው በእርሱ ዜማ አወጣጥ ልክ ነው። ብዙዎቹን ጎትቶ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የከተተ፤ ዳግም ሊፈጠር የማይቻል ለኢትዮጵያ የተሰጠ በረከት ነው» በማለት ነበር ተናግሯል።
ፀሐዬ ዮሃንስም ጥላሁንን የሚገልፅበት ቃላት ያጣ ይመስላል። «ጥላሁን በተፈጥሮ ምን ዓይነት የዋህ ሰው እንደነበር በዛን ዘመን የተፈጠርን እድለኞች ነበርን። ብዙ ነገሮቹ ለማመን የሚያቅቱ ነበሩ። የራሳችንን ዘፈን እስክንጠላ ድረስ ነው የሚያርመን፤ ምትክ አልባ ነው። የሚገርም ስጦታ ያለው ነው። ተተኪዎች እንዲያድጉ የነበረው ፍላጎትና ለዛሬ መድረሳቸው የነበረው ሚና በቃላት የሚገለጥ አልነበረም»
ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ ተከተለ «ጥላሁን አትዮጵያ ውስጥ ባልተፈጠረ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጭ ቢፈጠር የዓለም አንደኛ ይሆን ነበር። በእርግጠኝነት ነው የምነገራችሁ እኛን ገዝቶ ከሞተም በኋላ እንደፈለገ ነገሦ የሚኖር ነው። ይህ ሰው በሰለጠነው ዓለም ቢፈጠር ኖሮ ምን ሊሆን ይችል ነበርሲል ይጠይቃል።
«የጥላሁን ገሰሰ እውቀት እዚህ አፍሪካ ውስጥ ስለተፈጠረ ነው የተደበቀው። ሊሰጠው የሚገባው ክብር ተሰጥቶት አልፏል ብሎ ለመናገር ይከብዳል። ጥላሁን በዘፈን ደረጃ መግለፅ ከባድ ነበር። ጣራ ነክተው የቆሙ ሁለት ድምፃውያን አሉን። እነርሱም አስቴር አወቀንና ጥላሁን ገሰሰ ናቸው። የእነርሱን ሙዚቃ ይዞ የሚያድግ ዘፋኝ ካልበለጣቸው በስተቀር እውቅና አያገኝም። ምክንያቱም ጣራውን አልፈው ቁመዋልና።
ከነዚህ ሰዎች መዋስና መቅሰም ያለብንን ነገር ወስደን መውጣት አለብን እንጅ ውስጣቸው ተጣብቀን መቅረት የለብንም። ጥላሁን ወደር አልባ ሙዚቀኛ በመሆኑ ስለሱ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። እኛ እናጣዋለን እንጅ ውጭ ሀገር ቢፈጠር ትልቅ ዘፋኝ ለሚባለው ማይክል ጃክሰን ከተሰጠው ክብር በላይ ነበር የሚሰጠው።»
በእጅ የያዙት ወርቅ
ጥሎብን ጀግኖቻችንን የምናስታውሳቸው ሲያልፉ ነው። አልፈውም ቢሆን ለክብራቸውና ለሥራቸው በሚመጥን ደረጃ አናክብራቸውም። የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰም ታሪክ ከዚሁ የተለየ አይደለም። ለሥራው የሚመጥን መታሰቢያ ሀውልት እንኳ አንዲቆምለት ብዙ ተደክሞ ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሆኖ ለማየት አልታደልንም። ይህ ቁጭት በእነዚህ ጉምቱ ሙዚቀኞች ልብ ውስጥ ይበልጥ ተቀጣጥሎ ይነበባል።
አረጋኸኝ ወራሽ- ለጋሽ ጥላሁን የተሰጠው ክብር ይመጥነዋል ብሎ አያስብም። «በሀገራችን የሚሰጡ ክብሮች እንደ ኮታ የሚታደል ነው የሚመስለኝ። በሠሩት ልክ የተሰጣቸው በቂ አይደለም። የጎዳና ስያሜና በስማቸው ትምህርት ቤት መሥራት ይገባል። በህይወት እያሉ ቢከበሩ ነው የምመኘው። ካለፉ በኋላም ቢሆን እንደሀገር የሚሰጠው ክብር በቂ አይደለም።
አገርን ወክለው ብዙ ሥራዎችን የሠሩ ብዙ ሙያተኞችን የፈጠሩ እንደመሆናቸው መጠን በሌሎች ሀገራት የሚሰጠውን ዓይነት ክብርና ማዕረግ ሊሰጣቸው ይገባል። የሚመለከተው አካል በትኩረት ማየት ይገባዋል። በሌሎች ሴክተሮችም ቢሆን ሊታሰብበት ይገባል። በንጉሡ ጊዜ የነበረ ሽልማት እየተዳከመ መጥቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። እንደሀገር በቂ ነገር ተሠርቷል ብዬ አላስብም»
ፀሐዬ በበኩሉ፤ «ሀገራችን በየወቅቱ ጀግኖቻችንን እየበላች የምታድግ መሆኗ የአደባባይ
ምስጢር ነው። የሌላ ሀገር ዘፋኝ ሀውልት ያቆመች ሀገር ናት ያለችን። ጥላሁን 60 ዓመት የኢትዮጵያን ህዝብ አገልግሎ በጦር ሜዳው፣ በርሃቡ፣ በልማቱና በሁሉም መስክ ላይ ጥላሁንና ማህሙድ ያልተሳተፉበት ጊዜ የለም። ጥላሁን ከመሞቱ በፊት ሀውልት ቆሞለት ራሱ መርቆ ቢከፍተው ነበር ደስ የሚለኝ፤ ያ አልሆነም። ዛሬ መንገድ በስሙ እንዲሰየም 200ሺ ፊርማ አሰባስበን ለመዘጋጃ ቤት አስገብተን ነበር፤ አልተሳካም።
ዛሬ ላይ ቆመን የጥላሁን ቀን ሆና ተገናኝተናል። ማህሙድን እንድናከብር ስለተደረገ የፕሮግራሙን አዘጋጆች ላመሰግን እፈልጋለሁ። የሚመለከተው አካል ከዚህ ተምሮ ላለፈው ጥላሁንም ሆነ በህይወት ላሉት ለነ'ማህሙድ የተሰጣቸው ክብር እንዳለ ሆኖ አንድ አዲስ ነገር እጠብቃለሁ።»
ፀጋዬ እነዲህ ሲል ተናገረ፤ «ቦብማርሊ አደባባይ በሚባለው ሰፈር የቦብ ማርሊን ሀውልት ቁሞ ሳይ አመመኝ፤ መናገር አቃተኝ። እዚህ ቦታ ላይ ጥለሁን ነው ቦብማርሊ መቅደም ያለበት? የቦብ ማርሊን መሥራታቸው አስነዋሪ አይደለም። ግን ደረጃ አለው፤ ለእኔ ጥለሁን ነው እዛ ቦታ መቆም ያለበት። ምንድን ነው ከጥላሁን ያጣነውና ከቦብ ማርሊ ያገኘነው?
የቦብ ሀውልት መቆሙ ሳይሆን የሚያሳዝነው የጥላሁን መረሳት ነው። ስለዚህ ለውድድር የምናቀርብበትን መንገድ የረሳን ይመስለኛል። የምንሰጠውን ደረጃ አጥፍተነዋል፤ ለጋሽ ማህሙድ የመንገድ ስያሜ ቢሰጠው ለዚች ሀገር ያጎደለባት ነገር አለ? ለጥላሁን ቢሰጠው የሚያጎድለው ይኖራል? ጥላሁን ለዚች ሀገር የሠራው ነገር ለዚህ የሚመጥን ደረጃ የለውም? ጥላሁንን አጥተናል ብናጣውም ለእርሱ የሚሰጠውን ደረጃ ማየት እንፈለጋለን። ለጋሽ ማህሙድና ከነርሱ ጀርባ የነበሩትና ያለፉትን ብናከብራቸው የምንከበርበት ይሆናል እንጅ አናፍርበትም።
አዲሶቹ ድምፃውያን በበኩላቸው ጥላሁንን ሲያደንቁትና ሲያከብሩት መኖራቸውን ይናገራሉ። የስልካቸው ጥሪ ሳይቀር የጥላሁን ዜማዎች ነበሩ። «በእጃችን የያዝናቸውን ወርቆች ሳንደምቅባቸው አምልጠውናል። ያሉትንም አያያዛችን ልክ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ስቴጅ ላይ መዝፈን ማለት እኩል ሆነናል ማለት አይደለም። የወርቃማው ዘመን ሙዚቀኞች ወደታች ቀርበው ለማስተማር የተቸገሩ ይመስለኛል። መተካካትና መደናነቅ እንዳይኖር ያደረገው ይህ ይመስለኛል።
ጥላሁን ለኛ ዘመን ታሪኩና ሥራው ብቻ ነው የደረሰን። ሲዘፍን ብናየው ብዬ እመኛለሁ። እዚህ ያሉትም የተለዩ ነበሩ፤ ብቃታቸው የሚገርም ነበር። ምን ያህል ሙያውን እንደሚያከብሩት የምንረዳበት ነው። ከነርሱ የምንወርሰው ብዙ ነገር አለ።
ከምስጋናው መሀል የሚቀርቡት የመድረክ ሙዚቃዎች ያንን የወርቃማ ዘመን ወርቃማ ሙዚቀኞች ዘመን እንዴት በመለስነው የሚያሰኝ ነበር። የሁሉንም ድምፃውያንን ብቃት በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል ይህን ለመመስከር ሙያተኛ መሆን አይጠበቅም፤ ማድመጥ ብቻ በቂ ነው። በእርግጥም ስር የሰደደ ተሰጥኦ ማንም የማይሸረሽረው የዘላለም ሀብት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።
«የፍቅር ወጥወድ ነው መላ ሁሉ ገላስሽ»«እንች ልቤ እኮ'ነው ስንቅሽ ይሁን ያዥው»«ሸግየዋን ለግላጋዋ፤ ደማምዋ ጉብሊቷን» እያሉ አስደሰቱን። የአዲሱ ትውልድ ወካይ ሆነው የቀረቡት ሦስቱ ሙዚቀኞችም በርግጥም በትውልድ ቅብሎሽ ውስጥ በትክክለኛ ብቃት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ዝግጅቱን ሙሉ አድርገውታል።
የታላላቆቻቸውን ሙዚቃ በብቃትና በክብር አዚመውታል። ከታላቆቻቸውም ተገቢውን ክብርና አድናቆት በምላሹ አግኝተዋል። በመጨረሻም የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ሙዚቀኞችና ከማህሙድ ጋር የተነሱትን የመታሰቢያ ፎቶግራፍ በክብር አበረከቱለት። ሁልጊዜም የሚታወስ ድንቅ መታሰቢያ «አፍ እንኳን ባይኖረው ይናገራል ፎቶ» አይደል የሚባለው። ሰላም!

No comments:

Post a Comment