ጌዴኦን
ስንቃኛት
ጌትነት
ተስፋማርያም
መነሻዎን
ከአዲስ አበባ አድርገው፤ ውቢቷን ሐዋሳ ከተማ
አቋርጠው፤ ለምለሙን የደቡብ ክልልን በመንገድዎ
እየቃኙ 365
ኪሎ
ሜትሮችን ከተጓዙ በኋላ የጌዴኦ ዞን ዋና
መቀመጫ ዲላ ከተማን ያገኟታል። ዲላ የጌዴኦ
ስድስት ወረዳዎች የአስተዳደር ማዕከል ናት።
ጌዴኦዎችም ከተማዋን ለንግድ ማዕከልነት
ይጠቀሟታል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች
የመጡ ነዋሪዎች መገኛ በመሆኗም በሃይማኖትና
ባህል ተቻችለው ይኖሩባታል።
በጣሊያናዊው
የታሪክ አጥኚ ኮንቲ ሮሲኒ አገላለጽ «ኢትዮጵያ
የሕዝቦች ሙዚየም»
ተብላ
ትታወቃለች። ለዚህ ስያሜ ምክንያቱ በኢትዮጵያ
በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች
የራሳቸው የሆነ ቋንቋ፣ ታሪክና ወግ ያላቸው
መኖሪያ፤ ልዩ የሆነ ማኀበራዊና ባሕላዊ ዕሴቶች
የተገነባባት የጋራ ሐገር መሆኗ ነው፡፡ ሕዝቦቹ
የየራሳቸውን ባህል ለዘመናት አስጠብቀው
ይኑሩ እንጂ ባሕላዊ ሥርዓታቸውም ሆነ የማንነታቸው
ታሪክ በጥናት ላይ ተመርኩዞ የተጻፈ አይደለም።
የጌዴኦ ሕዝብም ከእነዚህ ሕዝቦች መካከል
አንዱ ነው፡፡
የጌዴኦ
ብሔር ታሪክ እና የዘር ግንድ
የጌዴኦ
ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የመስህብ ጥናትና
ጥበቃ እና ግብይት የስራ ሂደት አስተባባሪ
ወይዘሮ አዜብ በቀለ እንደሚሉት፤ የጌዴኦ
ሕዝብ ቋንቋ ከምሥራቅ ደጋ የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ
ይመደባል። ጌዴኦፋ (Gede’uffa)
ተብሎ
ይታወቃል። ዞኑ በሰሜን ከደቡብ ክልል ሲዳማ
ዞን፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ እና በደቡብ
ከኦሮምያ ክልል ከቦረና ዞን ጋር ይዋሰናል።
ሕዝቡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ክልል ከሚገኙት 56
ብሔር
ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አንዱ ነው፡፡ የአካባቢው
መሬት በእጅጉ ለም፣ ምርታማ በመሆኑ ከ95
በመቶ
በላይ የሚሆነው ነዋሪ በጥምር ግብርና ይተዳደራል።
ከ1960ዎቹ
አንስቶ ጥቂት ምዕራባዊ ምሁራን ስለጌዴኦ
ብሔረሰብ ጥናቶች ለማድረግ ቢሞክሩም ስለብሔሩ
ቅድመ ታሪክ አመጣጥ በስፋትና በብዛት የተጻፋ
መረጃ አላገኙም፡፡ ምክንያቱም እንደሌሎች
ብሔሮች ሁሉ ስለ ጌዴኦ ብሔር ታሪካዊ አመጣጥ
በዘመናዊ የታሪክ ምርምርና ጥናት የተደገፈና
የተረጋገጠ አንትሮፖሎጂያዊ ጥናት በአግባቡ
ተሰንዶ አይገኝም። ይሁን እንጂ ሰፊ የትውፊት፣
የሥነ ቃል እና አፈ ታሪኮች ይገኛሉ።
በ20ኛው
ክፍለዘመን ላይ የጌዴኦ ሕዝብ በተሻለ መልኩ
እንዲታወቅ ከሚያስችሉ ክስተቶች መካከል
በ1952 ዓ.ም
የተፈጠረው የጌዴኦ ገበሬዎች አመጽ ወይም
የምችሌ ገበሬ አመጽ ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡
ይህ አመጽ የጌዴኦ ገበሬዎች የኢትዮጵያ ሕዝብና
በተለይም የተማሪዎች ንቅናቄ «መሬት
ላራሹ»
ትግል
የሚካተት ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥም የጌዴኦ
ገበሬዎች በይበልጥ የሚታወቅበት አንዱ ክስተት
ሆኖ ይገኛል።
የጌዴኦ
ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህልና ቅርስ
ጥናትና እንክብካቤ ባለሙያ አቶ አበራ ኢያሱ
እንደሚናገሩት ደግሞ፤ የጌዴኦ ጥንታዊ የዘር
ግንድ ከኦሮሞ ብሔር ጋር ግንኙነት እንዳለው
ታሪክ አዋቂዎች ይገልጻሉ፡፡ የጌዲኦ ሕዝብ
እና የኦሮሞ ብሔር የጋራ አያት ያላቸው ስለመሆኑም
ያብራራሉ፡፡ ጥንት ሦስት ልጆች የነበሩት
አንድ ሰውዬ ነበር፣ የልጆቹም ስም ዳራሶ፣
ኡራጐ እና ቦሩ ነው፡፡ ዳራሶ ታላቃቸው ሲሆን
ይህም ሰው የዛሬው የጌዶኦ ብሔር አባት ነው።
ኡራጐ አሁን ኡራጋ ለሚባሉት የጉጂ የኦሮሞ
ሕዝቦች አባት ሲሆን፤ ቦሩ ደግሞ የቦረና ኦሮሞ
አባት እንደሆነ ይናገራሉ።
ዞኑ
ባስጠናው የታሪክ ጥናት ላይ እንደሰፈረው፤
ዳራሶ በትዳር ህይወቱ ሁለት ሚስቶች አግብቷል።
ከአንደኛዋ ሚስቱ አራት ልጆች ሲወልድ ስማቸውም
ደራሻ፣ ሐኑማ፣ ደባአና ጐርጐርሻ ይባላሉ።
እነዚህም ሾሌ ወይም አራት ቤት ተብለው ይጠራሉ፡፡
ከሌላኛዋ ሚስቱ ደግሞ የወለዳቸው ሐምባአ፣
ሎጐዳና በካሮ ሲባሉ እነዚህም ሳሴ ወይም ሦስት
ቤት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ጐሣዎች
በውስጣቸው ትናንሽ ጐሣዎች አቅፈው የያዙ
ሲሆን፤ በዋናነት ሰባቱ የጌዴኦ ብሔር ጐሳሣዎች
ተብለው ይጠራሉ፡፡
የሕዝቡን
አሰፋፈር ሲታይ ደግሞ በተለየዩ የአየር ንብረት
ክፍሎች ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ደጋማው የአየር
ክልል «ሱቦ»
ሲባል
በጣም ቀዝቃዛ ሆኖ የቀንድ ከብት፣ የጋማ
ከብት፣ ፍየልና በግ በስፋት የሚረቡበት ነው።
ከሰብል ምርት ደግሞ ገብስ፣ ስንዴ፣ እንሰት
እና ሌሎችን ያበቅላል። የወይና ደጋው የአየር
ክልል «ሪጋታ»
ሲባል
ትልቁን የሕዝብ ቁጥር ይይዛል። ቡና፣ እንሰት፣
የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች፣ የጋማና የቀንድ
ከብቶች በስፋት ይገኙበታልም።
የቆላማው
የአየር ንብረት ክልል «ዲባታ»
ይባላል።
ዘርዛራ የሕዝብ አሰፋፈር የሚታይበትም ነው።
ካለው የሙቀት መጠን ከፍተኛነት የተነሳም
ለሰው ልጅ አኗኗር እምብዛም አይመችም፡፡
ወባና የመሳሰሉት በሽታዎች ስለሚከሰትበት
ከምርታማነት አንፃር ከሌሎች የአየር ንብረት
ጠባይ ከሚታይባቸው ቦታዎች ዝቅተኛነት
ይታይበታል። በዲባታ ውስጥ ቡና፣ ሸንኮራ
አገዳ፣ ስኳር ድንች፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓዬ፣
ሙዝ፣ ወዘተ በብዛት እንደሚመረትበት አቶ
አበራ ያስረዳሉ።
የጌዴኦ
ገዳ ባሌ ሥርዓት
በጥናቱ
መሰረት፤ በጌዴኦ ብሔር ባህል ውስጥ ጎልቶ
የሚታየው የገዳ ሥርዓት (Gadaa
System) ሲሆን፤
በርካታ የውጪና የሀገር ውስጥ ምሁራን ሰፊ
የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አካሂደውበታል።
የምሁራን ጥናትና ምርምር ውጤት ደግሞ ከጌዴኦ
የባባል አባቶች እምነትና ትርጉም ጋር ይጣጣማል።
የገዳ ሥርዓት በአጭሩ ሲገለጽ ወንድ ልጅ
በዕድሜ ዕርከን የሚከፋፈልበት የመደብ ሥርዓት
ሲሆን፤ እያንዳንዱ ገዳ ስምንት ዓመት እርከን
አለው፡፡ ይህም ከኦሮሞዎች ገዳ ስርዓት ጋር
ያመሳስለዋል።
የጌዴኦ
ገዳ ሥርዓት ዘጠኝ መደቦችን ያቀፈ ዴሞክራሲያዊ
አስተዳደር ሥርዓት አለው፡፡ የተወሰነ ዑደት
ያለው ሆኖ በየስምነት ዓመቱ ከአንዱ የገዳ
ዕርከን ወደሚቀጥለው ዕረከን የሚተላለፍበትና
ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገርበት
ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ገንብቷል፡፡
መደቦቹም ቃዳዶ፣ ሲዳ፣ ሉማሳ፣ ራባ፣ ሉባ፣
ዩባ፣ጉዱሮ፣ ቁሉሎ እና ጫዋጄ ይባላሉ።
ከመጀመሪያው ደረጃ ቃዳዶ እስከ መጨረሻው
ጫዋጄ ለመድረስ 72
ዓመታትን
ይወስዳል።
እንደ
አቶ አበራ ገለጻ፤ የገዳ ሥርዓት እንደ ዘመናዊ
የፖለቲካ ድርጅት አወቃቀር እና አደረጃጀት
ያለው ነው። ከባህላዊ ሥርዓተ-አምልኮ
ተግባራት ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳለው
መረጃ ሰጪዎች ያስረዳሉ። የገዳ ሥርዓት መሪ
አባገዳ ሲባል፣ የገዳ ሥርዓቱም በካቢኔ
ይመራል። ይህም «ያአ»
በመባል
ይታወቃል፡፡ የደቡቦቹ የገዳ ሥርዓት ጥንት
ለኀብረተሰቡ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አመራር
ሲሰጥበት የቆየ አሰራር ነው። የዚህ ሥርዓት
ባለሥልጣኖች በሕዝብ ተመርጠው የመረጣቸውን
ሕዝብ በታማኝነት ያገለግላሉ፡፡ ለዚህ
ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ሃይማኖታዊ ድርጅት
ጠቅላላ ጉባዔ ነበረው፡፡ የጌዴኦ ብሔር በገዳ
ሥርዓቱ መሠረት በሦስት ትልልቅ የአስተዳደር
ክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
እያንዳንዱ
ክልል «ሮጋ»
ይባላል፡፡
ይህ ማለት በጌዴኦ ደጋ ወይና ደጋና ቆላማ
አካባቢዎች ናቸው። «በያአ»
ካቢኔ
ወይም ጉባኤ ውስጥ አባል የሚሆኑ የሦስቱ
ክልሎች «ሮጋ»
መሪዎች
አሉ። ከፍተኛ ረዳት ባለሥልጣናትም ናቸው።
የዚህ ክልል አስተዳዳሪ ወይም ሹም በተመሳሳይ
«ሮጋ»
ይባላሉ፡፡
ተጠሪነቱም ለአባገዳው ነዉ፡፡ የጌዴኦን
ብሔር የማስተዳደር ኃላፊነት በእነዚህ መሪዎች
ጫንቃ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህ የፖለቲካ አካል
በዋና ዋና ወሳኝ የብሔሩ ጉዳዩች ላይ ማለትም
በሰላም ስምምነት፣ በዘመቻ፣ ከጎረቤት ሕዝቦች
ጋር በሚኖረው ግንኙነት፣ በልማት እና በሌሎች
ጉዳዮች ዙሪያ የመወሰንና መልካም አስተዳደር
የማስፈን ኃፊነት አለበት፡፡ ሰፊውን ሕዝብ
ለማስተዳደር የሚችሉትን ባለሥልጣትን የመምረጥ
ሥልጣን ያለውም አካል ነው፡፡
«በያአ»
ጉባዔ
አማካኝነት የገዳ ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ
ሁለት ፓርቲዎች በምርጫ እየተተካኩ የሚመሩት
ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት እንዳለው
የዞኑ የታሪክ ጥናት ያሳያል። እያንዳንዱ
የገዳ መደብ ለስምንት ዓመታት በሥልጣን ላይ
ይቆያል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩም ፍጹም ሰላማዊና
በክብረ በዓል የታጀበ ስርዓት ያለው ነው።
የገዳ ስርዓት በአካባቢው የሕዝብ ኩራት ውርስ፣
የሥነ-ምግባር
ዋልታና ማገር፣ የእውነት፣ የእኩልነትና
የፍቅር ምንጭ እንዲሁም ከሰማይ አምላክ
«ማጌኖ»
የተሰጠ
ገፀ በረከት ተደርጎ የጌዴኦ ብሔር መተደደሪያ
በመሆን ለዘመናት ማገልገሉን አዛውንቶች
ይናገራሉ።
የአመራር
ምሰሶ የሚሆኑት አባጋዳ፣ ጃላባ፣ ሮጋ፣
ጃልቃባ፣ ሁላቲ ሐይቻ፣ ባጤቲ ሐይቻዎች፣
ዳባሊቻና ዋሙራ ተብለው የሚታወቁ በሥርዓቱ
መዋቅር መሠረት ለሚያስተዳድሩበት የስምንት
ዓመት ዘመን ቃለመሃላ ይፈጽማሉ፡፡ «ጃላባ»
የአባ
ገዳው ምክትል ስልጣን አለው። ከአባገደው
አመራር እየተቀበለ ከሥሩ ላሉት ባለሥልጣናት
መመሪያ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪ እንደ አባገዳው
ሁሉ ቅዱስ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ሮጋ
ደግሞ የክልሎች አስተዳዳሪ ነው። የጌዴኦ
ብሔር በገዳ ሥርዓቱ መሠረት በሦስት ትልልቅ
የአስተዳደር ክልሎች የተዋቀረ በመሆኑም
ሮጋው እነዚህ ክልሎች ያስተዳድራል። ተጠሪነቱም
በቀጥታ ለአባገዳው ነዉ። ጀላባ በበኩሉ የሮጋ
ረዳት ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለሮጋ ይሆናል፡፡
እርሱም በሮጋ አመራር ሰጪነት ለበታች ሹማምንት
አመራር ይሰጣል፡፡ ሑላቲ ሐይቻ ደግሞ የአንድ
ቀበሌ መሪ ወይም ተጠሪ ነው፡፡ በተዋረድም
ሕዝቡን በቅርብ ሆኖ ይመራል። ከበላይ አካል
የሚተላለፉለትን መመሪያዎችን ተግባሪዊ
የማድረግ ኃላፊነት አለበት።
«ዳባሌ»
የሚባለው
ደግሞ የሑላቲ ሐይቻ ረዳት ነው፡፡ የቀበሌው
መሪ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ኀብረተሰቡን
ያስተደድራል፡፡ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ብዙ
ዳባሌዎች ይሾማሉ፡፡ «ዋሙራ»
ደግሞ
የመረጃ አቀባይነት ሚና አለው። ከቀበሌ መሪና
ረዳቶቹ የሚሰጡትን ትዕዛዞች ለሕዝቡ ጆሮ
የሚያደርስ ሰው ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ ሰው
ቢሞት የአካባቢው ሕዝብ ወጥቶ እንደያስቀብር
ያዛል፣ ወንጀል እንዳይፈጸም ይቆጣጠራል፡፡
ተፈጽሞ ከተገኘም ለቀበሌው ሹም ወይም ረዳት
ያስተላልፋል፡፡ የቀበሌው ሹም ጉዳዩ ከአቅሙ
በላይ ከሆነበት ለጎሣ አለቃ ያስተላልፋል፡፡
የጎሣ አለቃው የበኩሉን እርምጃ በመውሰድ
ለሮጋው ያቀርባል፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ ከበድ
የሚል ሆኖ ከተገኘ ለሥርዓቱ መሪ ለአባገዳው
ይቀርብና የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል፡፡ በሥልጣን
ተዋረዱ አማካኝነት ጉዳዩ እልባት ካላገኘ
ጠቅላላ ጉባዔው «ያአ»
ይወስናል።
የገዳው
ምክር ቤት አባላት አፈ-ጉባኤ
«ቦባሳ»፣
ጠቅላይ ፍትህ አስተዳዳሪ «ሙርቲቻ
እና ፋቴ»በመባል
ሲጠሩ ዋና ዋና የስርዓቱ መሪዎች ናቸው፡፡
የጌዴኦ ባሕላዊ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት
በሕዝብ የሚመረጥ ባለሁለት ፖርቲ አስተደደር
ይመሰርታል፡፡ ይህም «ባሌ»
ይባላል።
ፓርቲውም የዳላና ባሌ እና የቢልባና ባሌ
ይባላሉ። የዳላና ባሌ መናገሻው በሔባኔ ሶንጎ
በቡሌ ወረዳ ነው። የቢልባና ባሌ ደግሞ
በባላያ ሶንጎ የንግሥ ሥርዓታቸው ተፈጽሞ
እያንዳንዱ ፖርቲ ለስምንት ዓመት ብሔሩን
ያስተዳድራል፡፡
አባገዳ
ከቢልባና ወይም ከዳላና ከአንደኛው ፖርቲ
ውስጥ በቀደምት አባገዳዎች የቅርብ ዝምድና
ያለው መሆን አለበት፡፡ ለዚህም በሰውነቱ
ጠባሳ የለሌበት፣ ተክለሰውነቱ ምሉዕ የሆነ፣
በቅድስና የተመሰገነ፣
የገዳ ሹመት መሥፈርቶችን
አማልቶ ለማገልገል
ቃልኪዳን ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆን
አለበት። ከሁሉም
በላይ የሰማይ አምላክን የሚያምን፤ ቁምቤ
የሚባለውን ከእንጨት የሚገኘውን ማር ወይም
ቦካ በመሃላ የቀመሰ መሆን ይኖርበታል።
አባገዳው
ትዳር
መሥርቶ ልጆች ያፈራ፣ ምንም ዓይነት በደልና
ግፍ ያልሰራ መሆን
አለበት።
የገዳን ሥርዓትና ደንብ ጠንቅቆ የሚያውቅና
የሚያከብር፣ የማያዳላ፣ የማይዋሽ፣ ብልህ፣
የንግግርና የአመራር ችሎታ ያለው መሆን
ይገባዋል።
የሶንጎ
ስርዓት
እንደ
ወይዘሮ አዜብ በቀለ ከሆነ፤ የጌዴኦ ብሔር
ያልተፃፈ ሕገ መንግሥት አለው፡፡ ሴራ በመባል
ይታወቃል። በእያንዳንዱ ብሔር አባል ላይ
ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን
ያስቀምጣል፡፡ የጌዴኦ ብሔር የባህላዊ ዳኝነቱን
ሥራ ሲያከናውን ለዚህ እና ለሌሎችም ማኀበረሰባዊ
ጉዳዩች ችግሮች መፍቻ ሥርዓት በሶንጎ ላይ
ይከናወናል፡፡ ሶንጎ በጌዴኦ ብሔር ሕይወት
ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለውና በባህሉ ውስጥ
ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ተቋም ነው፡፡ ሶንጎ
ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና በዓል ነክ ሥነሥርዓት
ማከናወኛ ሥፍራ ነው። የተለየዩ የባህላዊ
አስተዳደርና ፍትሃዊ ጉዳዩች እንደየደረጃቸው
ውሳኔ የሚያገኙበት ሥፍራም ነው፡፡ እንደ
መገናኛም ሆኖ ያገለግላል፣ ሰው እንዲያድርበትና
እንዲያርፍበት ይደረግበታል።
ሶንጎዎች
የተዘጋጁበት የእራሳቸው ታሪክ አላቸው።
ጌዴዎች ከጥንት መኖሪያቸው ሥፍራ ማለትም
ሐርሱ ሐዋጣ አንስቶ ረጅም መልካምድራዊ
አካባቢዎችን እያቋረጡ ሐሮወላቡ /ቡሌ
ወረዳ/
ደርሰው
መስፈራቸውን ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። ሐሮ
ወላቡ ኩሬ መሰል ሐይቅ ረግረጋማ ሥፍራ ነው።
የብሔሩ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት፣ ማኀበራዊ
ሕይወት እና ሌሎችም ባህላዊ ሥርዓቶች እምብርት
ተደርጐ ይወስዳል፡፡ ሐሮ ወላቡ ከዞኑ ዋና
ከተማ ከዲላ በ35
ኪሊ
ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ጌዴኦኖች ለዘመናት
ከኖሩበት በኋላ ከተራራማው አካባቢ በመውረድ
በረባዳማ አካባቢ ሠፍረው መኖር እንደጀመሩ
ይነገራል። ዛሬም በአጋምሳ ኮልባ አካባቢ
ከሐሮወላቡ ዝቅ ብሎ የሚገኙ የኮሊሻ ካራ፣
የሂጃ፣ የአጋምሳ ዳኩዋ አካባቢዎች ጥንታዊ
የጌዴኦዎች መኖሪያ አካባቢዎች መሆናቸውን
የዞኑ ጥናት ያመለክታል።፡
በረጅሙ
የተዘረጉ ተራሮች ተዳፋት ላይ የሚገኙ እነዚህ
አካባቢዎች ጌዴኦዎች የሚተዳደሩበትን የገዳ
ሥርዓት ማኀበረሰቡ ሲቀበል እንደሥርዓቱ
ማዕከል ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሥርዓቱ እውን
ከሆነ በኋላም አባጋዳዎችን፣ ሮጋዎችን፣
ሐይቻዎችንና ሌሎችንም የባህላዊ እምነታዊ
ስጦታዎች ለመከፋፈል ሶንጎዎች ተመንጥረው
ተዘጋጅተዋል። በጌዴኦ ብሔር ህልውና ውስጥ
ሶንጎ ትልቅ ቦታ አለው። ሶንጎ ሃይማኖታዊ፣
ባህላዊና በዓል-ነክ
ሥርዓቶች ብቻ የማፈጸምበት ቦታ አይደለም።
የተለያዩ አስተዳደራዊ፣ ባህላዊና ፍትሐዊ
ጉዳዩች እንደየደረጃቸው የሚፈጸምበትና
ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ሰፊ ቦታም ነው፡፡
የብሔሩ
ትልቁና የመጀመሪያው ሶንጎ «ኦዳያአ»
የተመነጠረውና
የተዘጋጀው በዚሁ አካባቢ ነው፡፡ ኦዳያአ
ማለት ጉባዔው መረጃ የሚለዋወጥበት ማዕከል
እንደማለት ነው፡፡ በአዳያአ ሶንጎ ህብረተሰቡ
አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ በሥፍራው
እየተገኘ ይመክርበታል፣ ጦርነት ሲነሳ፣
በሸታ ሲቀሰቀስ፣ ድርቅ ሲከሰት፣ ዝናም
ሳይዘንብ ቢቆይ፣ ቸነፈር ሕዝቡን ሲጎዳ፣
ሀገር ለከፋ አደጋ ሲጋለጥ የሰማይ አምላክ
/ማጌኖ/
ይለመንበታል፣
ምህላ ይካሄድበታል። ሁለተኛውና ትልቁ ሶንጎ
ደግሞ ከኦዳያአ በቅርብ ርቀት የሚገኘው «የካራ
ሶንጎ»
የተሰኘው
ነው፡፡ ሶንጎው ቃለመሃላ የሚፈጸምበት እንዲሁም
የብሔሩ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የሚመከርበት
ቦታ ሆኖ ያገለግላል። ሦሰተኛው ትልቁ ሶንጎ
ደግሞ «ባላያ»
ሲሆን፤
የምክር ቤቱ መቀመጫ ነው፡፡
ሶንጎ
የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ ትልቁ ሶንጎ
ሰፋ ያለ መልክዐ ምድራዊ ክልልን ይይዛል።
አንዱ ሶንጎ ለሌላው ሶንጎ ትልቅ እየሆነ በሥሩ
ከአምስት እስከ ስምንት ሶንጎች ሲኖሩት
ሶንጎውን የሚመሩት ሐይቻዎች ይኖራሉ። የሥልጣን
ደረጃቸውም በሶንጎው ልክ ነው። ሐይቻ ማለት
ብልህ፣ አዋቂ ማለት ነው፡፡ በሕዝቡ እጅግ
ይከበራሉ፡፡ በባህላዊ ሥርዓት ማዕረግ ሐይቻ
ሲሾም ተቀባይነትና ችሎታው በሕዝቡ ተመዝኖና
ታይቶ ነው፡፡ ለጎሣው፣ ለወገኑ ወይም ለቤተሰቡ
እንዳያዳላ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ቃለመሃላ
ይፈጽማል፡፡ ችግር ቢያጋጥመው እንኳ ራሱን
ለሕዝብ አሳልፎ ይሰጣል። የተወከለለትን
ሕዝብ ችግሮች በጽናት ይጋፈጣል፡፡ ሐይቻ
ከግል ሕይወትና ክብር ይልቅ ለሕዝብ ጉዳይ
ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ከሕዝብ የሚፈልገውም ሆነ
የሚጠብቀው አንዳችም ጥቅም አይኖርም፡፡
የሕዝቡን አክብሮትና ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር፡፡
ሐይቻዎች
በአካባቢያቸዉ የሚከበሩ፣ የሚፈሩና በእጅጉ
ተሰሚነት ያላቸዉ ስለሆኑ ግጭት ሲከሰት ወይም
ሰዉ ከሰዉ ጋር ተጣልቶ ተበዳይ ቅሬታዉን
የሚያሰማዉና የበዳዩን ማንነት እንዲሁም
የደረሰበትን በደል የሚገልጸዉ በሶንጎው
ላለው ሐይቻ ነዉ። ሐይቻዉ ምናልባት የበዳዩ
ወገን ከሆነና የቅርብ ዝምድና ያለዉ ቢሆን
ጉዳዩን ከማየት ራሱን አቅቦ ግጭቱ እስከሚፈታበት
ድረስ ጉዳዩ በሌላ ሐይቻ ወይም ሽማግሌዎች
እንዲካሄድ በማስጀመር ዝምድናዉ ወደሚያደላበት
ሆኖ ወገንተኛነቱን ይገልፃል። ይህ የሚደረግበት
ቁልፉ ምክንያት ፍትህ እንዳይዛባ ከሚደረገዉ
ጥንቃቄ አንፃር በሚሰጠዉ ብይን ወይም ዳኝነት
ላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ የጥርጣሬ ስሜት
እንዳይፈጠር አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል
ነዉ።
ሶንጎ
ሥራው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የጌዴኦ ብሔር
በሠፈረባቸው እና በሚኖርባቸው አካባቢዎች
ሁሉ በቅርብ ርቀት ተዘጋጅቶ ይገኛል። በአንድ
ጋሻ መሬት ሦስትና ከዚያም በላይ ቁጥር ያላቸው
ሶንጎዎች አሉ። ዙሪያው ተከልሎም ሰርዶ
ይተከልበታል። በአንድ አማካይ ጥግ ላይ
በተለይም በመንገዶች ዳር ላይ ዝናብ እንዳያፈስ
ተገርጎ ሣር ቤት በጥንቃቄ ይሠራል፡፡ ጎጆ
ቤቱ ከፊትና ከኋላ ሁለት በሮች ይኖሩታል።
መዝጊያ ግን አይሰራለትም። ከበራፉ ፊት ለፊት
ደግሞ የጦር ወይም በጌዴኦ የቦ የተባለ ማስደገፊያ
ይደረግበታል። በደጃፉ ላይ ተንቀሳቃሽ የሆነ
የገበጣ መጫዎቻ ይቀመጣል፡፡
ወንዶች
ከልጅ እስከ አዋቂ በሶንጎው በመገኘት ከሽማግሌዎች
ስለ ባህላዊ አስተዳደር በአንክሮ እየተከታተሉ
ያዳምጣሉ። ታዳጊዎች የትግል ጨዋታ ያካሂዱበታል።
በሶንጎ መካከል የጥላ ዛፍ ይኖራል። በጌዴኦ
ለእንደዚህ ዓይነት ተልዕኮና አሠራር በባህላዊ
ዘዴ የተዋቀሩ ከ535
በላይ
ሶንጎዎች እንደሚገኙ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም
ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የሶንጎ
አገልግሎት በአካባቢ የሚነሱትን ማንኛውንም
ዓይነት ማኀበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶችንና
ሌሎችንም የብሔሩን ጉዳዮች በውይይትና
በማግባባት ለመፍታት ነው፡፡ የማኅበረሰቡ
ዋና የመረጃ መቀበያና ማስተላለፊያ ማዕከል
ሆኖ ያገለግላል። አባቶች መረጃ ለማግኘት፣
ለማዳመጥ እና ለመለዋወጥ በአብዛኛው በሶንጉ
ዙሪያ ይሰፍራሉ። በጌዴኦ ባህላዊ የፍትህ
አሰጣጥ ሥርዓት በመጀመሪያ በቤተሰብ ደረጃ
ወይም በጎረቤት ደረጃ በተወሰነ ውሳኔ ላይ
ቅሬታ ያለው ሰው ደረጃዎችን ጠብቆ እስከ
አባገዳ ወይም እስከ ጠቅላላ ጉባዔ ያአ ቅሬታውን
ማቅረብ ይችላል፡፡ ከዚያ ካለፈ ወደ የኦዳያአ
ሶንጎ ይዞ ይሄዳል፡፡ በዚህም የመጨረሻ ውሳኔ
ይተላለፋል፣ ይግባኝም የለውም፡፡ በመጨረሻ
በአባጋዳ ውሳኔ ይደመደማል።
No comments:
Post a Comment