Translate/ተርጉም

Tuesday, October 30, 2018

ማሲንቆው አናጋሪው


ማሲንቆው አናጋሪው
ጌትነት ተስፋማርያም
አርቲስት ለገሰ አብዲ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ወለል ካለው መስክ ላይ ነጭ የአገር ባህል ልብሳቸውን እንደለበሱ፤ ማሲንቋቸውን አንግተው በአይረሴ ድምጻቸው እንዲህ ሲሉ አዚመዋል።
«አዋ ሺራን ሌማኒ /2/
አኒ በዱዳ ከኤ
ናሂ ደኒ ቴ ጳኒ 2
ቴጳቀላ ዴረኒ
አሸንኪታቢ ኪያ
ነፉደቹ ፊዴመኒ»
ትርጉሙም «ከአዋሽ ቀጥሎ ሌመን የሚባል አለ፤ አንቺ የኔ አሸንክታብ ሊወስዱኝ መጥተዋል እኔ ልጠፋ ተነስቻለሁ እሰሩኝ በቀጭን መጫኛ» እንደማለት ነው።
የአርቲስት ለገሰ አብዲን ሙዚቃ ሲሰሙ ልዩ ስሜት የሚሰማቸው ቋንቋውን የሚሰሙና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን የማያውቁትንም ጭምር መሆኑ የአርቲስቱን የጥበብ ክህሎት እንዲደነቅ ያደርገዋል። አርቲስት ለገሰ ከ60 ዓመታት በላይ ባህላዊ ሙዚቃ፤ በማሲንቆ የኦሮምኛ ሙዚቃዎቻቸው እና በጥልቅ ግጥሞቻቸው ይታወቃሉ።
ከሙዚቀኛ ለገሰ አብዲ ስራዎች መካከል ተወጃጅ የሆነው እና በማሲንቆ እና በዘመናዊ መሳሪያ የተቀነባበረው ጥዑመ ዜማ ግጥሙን እናስታውሳችሁ።
«ያቦና ያቦና ዲዴ ወሊጎ
ማሎ ያ ወሌቶ
አዋዋ ሺ/አዝማች/
ቤኑ በቾ ቡና
አወወ ዋሺ
አወሾ በሎኒ
አወወ ዋሺ
ፎሊንኬ ኡርገኤ
አካጩርቃ ሎሚ
የሾሌ ካራ አለምገናዳ
ዮም ራገድኔ ገናዳ
የሾሌ ከራ አለምገናዳ
ዮምታጳኔ ገናዳ»
ትርጉሙን «ነይ ነይ የኔ ኩራተኛ፤ ምንያደርጋል እምቢ አልሽ፤ ነይ በበሎ አድርገን ወደበቾ እንሂድ፤ ጠረንሽ እንደሎሚ አወደኝ፤ የኔ ቆንጆ ጉዞ ወደ አልምገና ነው፤ መቼ ጨፈርንና መቼ ተዝናናንና» እንደማለት ነው። ይህን እና ሌሎችን ስራዎቻቸውን ለአድማጭ ያቀረቡት አንጋፋ አርቲስት ባለፈው ሳምንት ነበር ከዚች ዓለም የተለዩት። ህልፈተ ህይወታቸው ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ከውጭ አገራት እና አገር ውስጥ ያሉ አድናቂዎቻቸው ሃዘናቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።
አንጋፋው የኦሮምኛ የማሲንቆ ሙዚቀኛው ለገሰ አብዲ የኦሮምኛ የባሕላዊ ሙዚቃ አምባሳደር እየተባሉ በብዙዎች ዘንድ ይወደሳሉ። ምክንያቱ ደግሞ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን በባህላዊ ዜማዎች እና አቀራረባቸው ለረጅም ዓመታት በመላ አገሪቱ እና በጎረቤት አገራት ስላስተዋወቁም ጭምር ነው። አርቲስቱ የመጀመሪያው የኦሮምኛ የማሲንቆ ሙዚቀኛ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል። 
አርቲስት ለገሰ አብዲ
 
ከድምጻዊነታቸው በተጨማሪ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ግጥምና ዜማዎችን በመድረስ ይታወቃሉ። ግጥም እና ዜማ ለእራሳቸው ሙዚቃዎች ከማዘጋጀት በተጨማሪ ለሌሎችም ሰጥተዋል። «አማ ስኳሬ» እና «አወይ የገላ ሳሙና» የተሰኙ የጥላሁን ገሰሰ ታዋቂ የዘፈን ግጥሞችንም የደረሱት አርቲስት ለገሰ ናቸው።
ሱዳን አገር ከክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ጋር ሄደው በማሲንቆ ሲጫወቱ የማሲንቆው ድምጽ እና የአርቲስቱ የአዘፋፈን ስልት የማረካቸው የሱዳን ሙዚቀኞች አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። እርሳቸው ግን አገራቸው ላይ መስራት በመፈለጋቸው ግብዣውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል። ለታሪክ የሚተላለፍ የኪነጥበብ ስራዎቻቸውን እያፈለቁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በሙያው ላይ ቆይተዋል።
የኦሮምኛ የባሕላዊ ሙዚቃ አምባሳደሩ የተወለዱት በቀድሞው የሰላሌ አውራጃ ልዩ ስሙ ያያ ቀጫማ በተባለ አካባቢ ነው። በ1931 .ም ከአባታቸው ከአቶ አብዲ ዳዲ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፎሌ ጉደታ የተወለዱት ሙዚቀኛ የእናታቸውን ፍቅር ሳይጠግቡ ነበር በሞት የተነጠቁት።
ለወላጆቻቸው ብቸኛ ልጅ የሆኑት አርቲስት ለገሰ የአባታቸው ጓደኛ የሆኑትን የማሲንቆ ተጫዋች ወሰኑ ዲዶን የመመልከት እድል በልጅነታቸው ገጠማቸው። ይህ አጋጣሚ ወደ ሙዚቃው ስለሳባቸው በማሲንቆ የሙዚቃ ጥበብ ላይ ያላቸው ፍላጎት እያደገ መጥቶ፤ የህይወታቸው መሰረት አስከመሆን አደረሳቸው።
ከልጅነታቸው ጀምሮ የሙዚቃው ፍቅር የነበራቸው አርቲስት ለገሰ በተለያዩ ድግሶች ላይ በተለይም በሰርግ ስነስርአቶች ላይ በማሲንቆ በማዝናናት ይታወቁ ነበር። ከሰላሌ ተነስተው ወሊሶ እና ጅማ፤ ወለጋ እና ኢሊባቦር ድረስ በመሄድም በልጅነት ጊዜያቸው የማሲንቆ የሙዚቃ ችሎታቸውን በመላው ኦሮሚያ ማስመስከር ችለዋል። በየሰርግ ቤቱ የሚያዜሙት ለገቢ ማግኛም ጭምር መሆኑን የተረዱት እና ያለእናት ያሳደጓቸው አባታቸው አቶ አብዲ ሙያቸው አናንቀው ነቅፈዋቸው አያውቁም ነበር። ይልቁንም ደስተኛ ስለነበሩ ለአርቲስቱ የሞራል ስንቅ በመሆን ያበረታቷቸው ነበር።
አርቲስት ለገሰ በወቅቱ በሙዚቃ ችሎታቸው እየታወቁ ስለመጡ፤ በአርቲስት ወሰኑ ዲዶ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገቡ። በአዲስ አበባ ቆይታቸው በክብር ዘበኛ በወታደርነት በመቀጠር ስራ ጀምረው በኋላም የሙዚቃ ችሎታቸው ታይቶ ወደ ሙዚቀኛ ክፍል ተዛወሩ። ጥበብን፣ ፍቅርን፣ ውበትን፣ አካባቢን፣ ባህልን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሱ በማሲንቋቸው ተጫውተዋል፤ አጫውተዋል፤ በጥበብ ማህበረሰቡን አገልግለዋል።
አርቲስት ለገሰ በአጠቃላይ በክቡር ዘበኛ ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል። በመጀመሪያ ሲቀጠሩ ግን እድሜያቸው ገና 17 ሲሆን በ13 ብር የወር ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር። በክቡር ዘበኛ ሙዚቀኝነታቸው ከነ ካሳ ተሰማ እና ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ጋር አብረው በመስራት የጥበብ አፍቃሪያንን አድናቆት አግኝተዋል።
ከክቡር ዘበኛ በኋላ ያቀኑት ወደ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቤት ነበር። በቴአትር ቤቱ በሙያቸው ሲያገለግሉ በወር 70 ብር ደመወዝ ነበር የሚከፈላቸው። በቴአትር ቤቶች ውድድር በነበረበት ወቅትም በማሲንቆ ችሎታቸው ተወዳዳሪዎቻቸውን በልጠው በመገኘት ይሸለሙ ነበር። በሙዚቃ መሳሪያ ችሎታቸው አማካኝነት «ማሲንቆን እንደ ሰው ማነጋገር ይችላሉ» እስኪባል ድረስ ታዳሚውን የማስደመም ብቃት ነበራቸው። ከዚያም በግላቸው ማሲንቋቸውን አንግተው ቦረና እና አዶላ ድረስ እንዲሁም የተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተዘዋወሩ በመስራት ማህበረሰቡን ያዝናኑ፣ ህይወታቸውን ይመሩ፤ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩም ነበር። አንጋፋው የጥበብ ሰው በሙዚቃ ሕይወታቸውም በተለያየ ጊዜ በመድረክ ካቀረቧቸው ሙዚቃዎች በተጨማሪ ደርዘን የሚደርሱ የዘፈን ካሴቶችን አሳትመው ለገበያ አቅርበዋል።
ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሱ በነፃነት መዝፈንም ሆነ ሃሳብን መግለፅ በማይቻልበት በዚያ ወቅት በኦሮሞ ቋንቋ በሚደረድሯቸው ስንኞቻቸው በማሲንቆ ታጅበው በድፍረት ስለሚዘፍኑ ከማህበረሰቡ ታላቅ ፍቅርና አክብሮትን አትርፈው እንደነበር ይነገርላቸዋል። ለቋንቋው እድገትና ዕውቅና ታላቅ ተጋድሎን ካደረጉ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች መሃከል እንደሆኑ መሆናቸው ለሙያው ቅርብ በሆኑ አጋሮቻቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡ በስራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችም አግኝተዋል።
የዛሬ ዓመት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ማዕከል ጋር በመተባበር በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደዴሳ ከተማ ባዘጋጁት መርሃግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ከሰዓሊ ለማ ጉያ ጋር የህይወት ዘመን ተሸላሚ ነበሩ። ምንም አይነት ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርትን ሳይማሩ አራቱንም የሙዚቃ ቅኝቶች በመጫወት የሚታወቁት አርቲሰት ለገሰ አብዲ በየአገሩ እየተዘዋወሩ በሚያሳዩት የማሲንቆ ጨዋታ ጥበብ የየወረዳ እና የከተማ ኪነት ቡድን አባላት እንደ አርአያ ያይዋቸው ነበር።
የአርቲስቱ የታሪክ ዶሴ እንደሚያስረዳው፤ አንጋፋው ሙዚቀኛ በኢትዮጵያ ብብሔራዊ ቴአትር፣ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ በፖሊስ ኦርኬስትራና እና በማዘጋጃ ቴአትር ቤት እንዲሁም እንደ ሀብተሚካኤል ደምሴ አይነት የባህል ሙዚቀኞች ጋር በመሆን በተለያዩ የምሽት ክለቦች ሰርተዋል። በሙዚቃ ሕይወታቸውም አስር ስራዎችን አሳትመዋል፤ በስራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶችም ተቀብለዋል።
ከሙዚቃ ችሎታቸው ባለፈ በተለይ በኢትዮጵያ ራዲዮ ህጻናት የኦሮምኛ ቋንቋ ፕሮግራም ላይ ማሲንቆ በማናገር ልዩ ችሎታ እንዳላቸው አስመስክረዋል። እርሳቸው በቃላት የሚያወጡትን «አካም ጅርታ» እና ሌሎች የኦሮምኛ የሰላምታ ልውውጦችን ከማሲንቋቸው ጋር በማድረግ ህጻናትን ያዝናኑ ነበር። ይህም የሆነው እያንዳንዱን የማሲንቆ ድምጽ አቅጥነው እና አወፍረው ከሰው ልጅ ንግግር ጋር እንዲመሳሰል አድርጎ ማሲንቆ የመግረፍ ጥበብን ስላዳበሩ ነው።
ማሲንቆ አናጋሪው አርቲስት ለገሰ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበብ የሚገኘው ከባህላዊ ሙዚቃ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። «ማሲንቆን እንደ ሰው ማነጋገር ይችላሉ» የሚባልላቸው አንጋፋው የጥበብ ሰው በስራዎቻቸው የሚገባቸውን ጥቅም እና ክብር አላገኙም የሚል ሃሳብ አድናቂዎቻቸው ሲነሱ አንደነበር ይነገራል። ይሁንና በመድረክ ዝግጅታቸው ወቅት እስከ 15 ሺህ ብር ድረስ ከታዳሚው ተሸልመው የሚያውቁ አድማጭን በማሲንቆ ችሎታቸው ቁጭ ብድግ የሚያስብሉ ጥበበኛ መሆናቸው በበርካቶች በህይወት እያሉ መስክረውላቸዋል።
ማሲንቆ በኦሮሚኛ ሙዚቃ ውስጥ ያለውን ጣዕም ያስተዋወቁ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ድምጻዊ ለገሰ አብዲ፤ የሶስት ሴቶችና የ4 ወንዶች ልጆች አባት ነበሩ። ባጋጠማቸው የጤና ችግር ከስድስት ዓመታት በላይ ማሲንቋቸውን ሰቅለው አልጋ ላይ ቆይተዋል። አርቲስት ለገሰ ብቻቸውን የማሲንቆ ትምህርት ቤት ናቸው እያሉ የሚያወድሷቸው ሙያተኞች በርካታ ናቸው። ከ 60 ዓመታት በላይ የኦሮምኛን ሙዚቃ በማሲንቆ በመጫወት ለሙዚቃው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ከባለቤታቸው ከወይዘሮ እጅጌ አበበ ጋር ትዳር መስርተው ሰባት ልጆችን አፍርተዋል። ይሁንና የእሳቸውን ሙያ የያዘ አንድም ልጅ እንደሌለ አርቲስቱ ተናግረው ነበር። ልጆቻቸው በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው «የእኔ ድምጽ ወደ ቤተሰቤ አልተላለፈም» ሲሉም ተደምጠዋል። በአንድ ወቅት ወድቀው ባጋጠማቸው የጀርባ አጥንት ህመም ምክንያት በርካታ ጊዜያትን ወደ ሆስፒታል ተመላልሰዋል።
የማሲንቆው አጫዋች ቃላት ፈጥረው ማሲንቆውን ያናግራሉ የሚባሉት አርቲስት ለገሰ ጥዑም የጥበብ ስራዎቻቸውን ትተውልን በተወለዱ በ84 ዓመታቸው አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ጥቅምት 12 ቀን 2011 .ም ተፈፅሟል፡፡

No comments:

Post a Comment