Translate/ተርጉም

Tuesday, October 23, 2018

ባለ ንስር ዓይኑ የእግር ኳስ ቅመም- ስዩም አባተ


ባለ ንስር ዓይኑ የእግር ኳስ ቅመም- ስዩም አባተ
ቦጋለ አበበ
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚሰሙ ሰዎች አንዱ ነው። በተጫዋችነት ቆይታው በአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በውጤታማነት እንዲጓዝ አድርጓል። በአሰልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ ከቡናማዎቹ ጋር ብቅ ብሎ ሌላ የእግር ኳስ ታሪክ ፅፏል-አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ።
በብሔራዊ ቡድንና በአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በተጫዋችነት በመሰለፍ በትናንቱ የአገሪቱ የእግር ኳስ ውጤታማነት፤ ብሎም ማራኪነት ላይ ቅመም መሆኑን በእግር ኳሱ የህይወት ጉዞ አብረውት ያሳለፉ ሰዎች ይመሰክራሉ። ከእግር ኳሱ ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት ለ50 ዓመታት የተጓዘበት ሂደት ጅማሮውን 19 65 .ም ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓመት የእግር ኳስን ሀ ሁ በክለብ ደረጃ ጀመረ። በየትኛውም ቦታ በመሰለፍ በብቃት በመጫወት የእግር ኳስ ጥበበኛነቱን ማሳየቱን ተያያዘው።
ብዙዎች በመሀል ሜዳ ሞተርነቱ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ስዩም እግሩን እንደፈለገው በማዘዝ የሚጫወት ደፋር የእግር ኳስ ጥበበኛ ነው›› ይላሉ፡፡ የያኔው ታዳጊ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሕፃናት ቡድን ፍሬ ምርጥ አቅምና ብቃቱን አሳይቷል። ከ1965 .ም እስከ 1970 .ም ድረስ በታዘዘበት ቦታ ሁሉ በመሰለፍ እናት ክለቡን አገልግሏል።
በኢትዮጵያ ወርቃማው የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስሙ ጎልቶ የሚጠቀሰው መንግሥቱ ወርቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫዋችነት ጊዜው ሲያበቃ ተተኪ በነበረው ስብስብ ውስጥ ስዩም ተካቷል። በ1970 .ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሲፈርስ እግር ኳስን የጀመረበትን ክለብ ለመልቀቅ ተገደደ።
በወቅቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለመልቀቅ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠርም የክለቡ ፍቅር ከውስጡ እንዳልወጣ በአንድ ወቅት ከክለቡ ድረ ገፅ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡« ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ከታዳጊ ጀምሮ በዋናውም ቡድን ታላላቅ ጨዋታዎችን በማድረግ ቡድኔን ባለድል አድርጌአለሁ፡፡ ሆኖም ግን ቡድናችን እንዲፈርስ ሲደረግ ሁሉም በየፊናው ተበታተነ፡፡ ወደ ሌሎች ቡድኖች ገባን፡፡ በየሜዳው እየተገኘ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይዘምር የነበረ ደጋፊ እጅግ አዘነ፡፡ እኛም የምንወደውን ማሊያ ለብሰን የመጫወታችን ፍላጎት ሳይታሰብ አከተመ» በማለት ቁጭቱን እንደገለፁ ድረ ገፁ ዘግቧል፡፡
1975 .ም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደገና ሲቋቋም በድጋሜ ወደ ክለቡ በመመለስ አገልግሏል። ከክለቡ ጋር በነበረው ቆይታም ስኬታማ የሚባሉ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ገናና ስሙን እንዲጽፍ የበኩሉን አበርክቷል። በተጨዋችነት ዘመኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጠራባቸው ዓመታት ሁሉ የሚጠበቅበትን ተወጥቷል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስም በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪቃ ክለቦች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ለስኬቱ ሞተር እንደነበር ይነገራል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የሱዳኑን አል ሜሪክን 91 ሲያሸንፍ የስዩም አባተ ጥበበኛ እግሮች ሚና መቼም አይዘነጋም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ሁሌም ያስታውሱታል። በክለቡም ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ክስተት በክለቡ ብቻ ሳይሆን፤ የአገሪቱ የእግር ኳስ ገናናነት ሲወሳም አብሮ ይነሳል፡፡ የተጫዋችነት ቆይታ ሲያበቃ የአገሪቱን የስፖርት ከፍታ ለማሳደግ ሌላ ታሪክ ለመጻፍ ተንደረደረ። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አድጎ በአገሪቱ የእግር ኳስ ግለት ላይ አሻራውን ያሳረፈው ስዩም ፊቱን ወደ አሠልጣኝነት ሙያ አሸጋገረ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ሆኖ ብቅ አለ። ይሄ እርምጃው ከልጅነት ክለቡ ጋር በማኮራረፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጀርባቸውን እንዲሰጡት አድርጓል። ይሁንና በሂደት ነገሮች ወደ መልካምነት ሊቀየሩ ችለዋል፡፡
በተጫዋችነት ጊዜው በሜዳ ላይ የሚያሳየውን ጥበብና ማራኪ አጨዋወትን ወደ ቡና ክለብ ይዞ በመምጣት በአሠልጣኝነትም ስኬትን ለመድገም ችሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድምቀት በሆነው ኢትዮጵያ ቡና ሌላ የታሪክ አሻራውን አሳረፈ። በቡና የእግር ኳስ ጥበብን ማሳየት ችሏል፡፡በተጫዋችነት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያሳለፈው ስዩም፤ በቡና የአሠልጣኝነት ቆይታው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተፎካካሪ ቡድን መፍጠሩ ይነገርለታል፡፡ በዚህም ለፕሪሚየር ሊጉ ጥንካሬ መሰረት መጣሉ በጥንካሬ ይጠቀስለታል፡፡
ቡና አሁንም ድረስ ለሚከተለው ኳስን መሰረት ያደረገ ውብ ጨዋታ የመሰረት ድንጋዩ ስዩም እንደሆነ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ይመሰክራሉ። በዘመኑ አብረውት ከተጫወቱ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደማቅ ታሪክ ካላቸውና ከጓደኝነትም በላይ ወንድማዊ ትስስር ካለው መካከል አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ አንዱ ነው፡፡ አስራት ስለ ስዩም ብዙ ይላሉ፡፡ ‹‹ስዩም በተጫዋችነት ዘመኑ ሁለገብ ነበር፡፡ አጥቂ፣ ተከላካይና አማካይ ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስን አገልግሏል፡፡ ደፋር እና እልኸኛ ነው፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው ፍቅር ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡መረታትን በፍፁም አይፈልግም›› ይላል፡፡ እንደውም «አቶ ጭቅጭቅ» በሚል ቅፅል ስም ይጠሩት እንደነበር በአንድ ወቅት አሰልጣኝ አስራት ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሮ ነበር።
«እኔና ስዩም የአንድ ቡድን ልጆች ነን፡፡ ብዙ ባለታሪኮችን ያፈራው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውጤቶች በመሆናችን ልምዳችን ተመሳሳይነት አለው፡፡ በአሠልጣኝነት ዘመን ቡናን ውጤታማ ያደረገው ስዩም ነው›› በማለት በአሠልጣኝነት ዘመኑም ውጤታማ እንደነበር ይመሰክራል።
አሠልጣኝ ስዩም ከ1976 .ም ጀምሮ እስከ 1998 .ም ድረስ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ውስጥ ገባ ወጣ እያለ መሥራቱ ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ክለቦችን ቢያሠለጥንም የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ቆይታው ሚዛን ይደፋሉ፡፡ በተጫዋችነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን መነሻ አድርጎ በቡና ክለብ በአሠልጣኝነት የተቃኘው የ50 ዓመታት የእግር ኳስ ህይወት ጉዞ ተደምድሟል።
ይህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ ለረጅም ጊዜ ከአልጋ ውሏል። አንጋፋው አሠልጣኝ ስዩም አባተ በሳምባ ምች በሽታ ምክንያት ለረጅም ጊዜ አልጋ ከያዘ ውሎ አድሯል። በአገር ውስጥ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቷል። የተወሰኑ ለውጦች በመታየታቸው ቤቱ ውስጥ ሆኖ ህክምናውን እንዲከታተል ተደርጓል። ነገር ግን ህመሙ በአገር ውስጥ ህክምና መዳን የሚችል አልነበረም። በመሆኑም ወደ ውጭ አገር ሄዶ መታከም ነበረበት። ለህክምናው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በተነገረበት ወቅትም በአሰልጣኝነት ዘመኑ ጓደኛም ተቀናቃኝም ሆኖ ያሳለፈው አሠልጣኝ አስራት ሃይሌ እንዲሁም የአሠልጣኞች ማህበር ለህክምናው የሚሆን ገንዘብ ከተለያዩ አካላት እና ተቋማት በማሰባሰብ ትልቅ ጥረት አድርገዋል።
ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ የአንጋፋውን አሠልጣኝ ህይወት ለመታደግ ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ውይይት ተገርጓል። የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራው በክለቦች አካባቢም ሲከናወን ነበር። በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ በተጫዋችነት ያሳለፈበትና የሚወደው ክለብ ነው፡፡ በአሠልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ ቡና ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ መሰረት ጥሎ ማለፍ ችሏል፡፡ በዚህም መሰረት የመጀመሪያው የድጋፍ ጅማሮ የነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ማድረግ ነበር።
ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ታላቁ አሰልጣኝ ለተወሰነ ጊዜ ያገገመ ቢመስልም በሃምሳ ዓመታት የእግር ኳስ ታሪኩ ያልተበገረው ስዩም አባተ አሁን ለሞት እጅ ሰጥቷል። የአንድን ታዳጊ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ለመለየት ከአምስት ደቂቃ በላይ የማይፈጅበት ባለ ንስር ዓይኑ ታሪካዊ የእግር ኳስ ሰው ከሳምንት በፊት ስርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 2/2011ሳሪስ በሚገኘው የፃድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ (ሳሪስ አቦ) ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።















No comments:

Post a Comment