ታሪክን
የሚያወሱት-
ጥንታዊ
የአዲስ አበባ ሰፈሮች
ጌትነት
ተስፋማርያም
አዲስ
አበባ ከአራት ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይኖርባታል
ተብሎ ይገመታል። ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት
የመጡ ዜጎች እና የውጭ አገር ሰዎች በከተማዋ
የተለያዩ ቦታዎች ኑሯቸውን መመስረታቸው
ይታወቃል። በመዲናይቱ ሀያ እና ሃያ አምስት
ሺ ሰዎች ብቻ በነበሩበት ወቅት ሰፈሮችዋ
በተለያየ አጋጣሚዎች ስያሜቻቸውን እንደያዙ
ይነገርላቸዋል። የቀድሞ ሰፈሮችዋን የሚያወዳድሱ
ዘፈኖችም በተለያዩ ሙዚቀኞች ተዚመዋል።
እነዚህ የተዜመላቸው ሰፈሮችዋ ታዲያ ስያሜያቸውን
እንዴት እንዳገኙ ታሪኩን ከሚያውቁት ሰዎች
መረዳት ተገቢ ነው።
«ሰፈር
ማለት ወጥተህ የምትገባበት፤ አድረህ የምትሄድበት
ብቻ አይደለም» የሚሉት
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ከፍተኛ የቅርስ
ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት ባህል እና ጥበብ በአንድነት
ተዋህደው ለመላ ኢትዮጵያውያን የቀረቡባቸው
በርካታ ሰፈሮች በመዲናይቱ ይገኛሉ። የአዲስ
አበባ ሰፈሮች የሚገኙ ጥንታዊ ቤቶች ቅርስ
እንደሆኑት ሁሉ ሰፈሮቹ ደግሞ የማይዳሰሱ
ቅርሶች ናቸው። የመዲናዋ ጥንታዊ ሰፈሮቹ
ስያሜ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ
ታሪክ አላቸው። በተለይ በአፄ ምኒልክ እና
በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተሰየሙት ይበረክታሉ።
ስያሜዎቹ ከውጭ አገር ዜጎች ጋር ተያይዞ፣
ከብሔረሰብና ከክፍላተሀገራት እና ከመኳንንቶች
እንዲሁም በዋነኛነት ከአርበኞች ጋር የበለጠ
ቁርኝት አላቸው። የሰፈር ስያሜዎቹ ቀድሞ
ካርታ ባልነበረበት ወቅት እንደመጠቆሚያ
አገልግለዋል።
እያንዳንዱ
የአዲስ አበባ ቀደምት ሰፈሮች የየራሳቸውን
ታሪካዊ አሰያየም ለመመልከት በቅድሚያ በጀግና
አባቶች እና አርበኞች ስም የተሰየሙትን ማየት
እንደሚገባ መምህር መክብብ ይናገራሉ። አንድ
ብለን ብንጀምር የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ
ሰፈር ልደታ አካባቢ ይገኛል። ደጃዝማች ባልቻ
አባነፍሶ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ
ወቅት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ አርበኛ ናቸው።
«ገበየሁ
ቢሞት ተተካ ባልቻ፤
መድፍ
አገላባጭ ብቻ ለብቻ»
በተባለላቸው
አርበኛ ስም የተሰየመ ታሪካዊ ሰፈር ነው።
ሌላው ደጃዝማች በቀለ ወያ ሰፈር ነው። ሰፈሩ
በተመሳሳይ ልደታ አካባቢ ይገኛል። ደጃዝማች
በቀለ የወሊሶ ተወላጅና አርበኞችን አሰማርተው
ጣሊያንን መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡ ጀግና ናቸው።
ልክ እንደ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ /ሊሴ
ገብረማርያም ትምህርት ቤት የተሰየመላቸው/
ከወሊሶ ጀምረው
ጣሊያንንን እያባረሩ አዲስ አበባ የገቡ ጀግና
በመሆናቸው ሰፈሩ በስማቸው ተሰይሟል።
ሼህ
ሆጄሌ ሰፈር ደግሞ ሩፋኤል አካባቢ እናገኘዋለን።
ሼህ ሆጄሌ የተባሉ የአሶሳ ንጉስ በጣሊያን
ወረራ ወቅት አገራቸውን ኢትዮጵያን ለመጠበቅ
በዱር በገደሉ የተጋደሉ ሰው ናቸው። አንድ
እግራቸውን በጥይት ተመተው ጣሊያን በግፍ
የገደላቸው አርበኛ በመሆናቸው ሰፈሩ በስማቸው
ተሰይሞላቸዋል። ሌላው ደጃዝማች ኡመር ሰመተር
የተሰኘው በመርካቶ አካባቢ የሚገኘው ሰፈር
ነው። ደጃዝማች ኡመር ሰመተር በኦጋዴን ጦርነት
ወቅት እንግሊዞች ከእኛ ወገን ሆነህ ኢትዮጵያን
እንውጋ ብለው በርካታ ሃብት ማባበያ ቢያቀርቡላቸውም
«ኢትዮጵያዊ
ነኝ አገሬን አልከዳም»
በማለት በጀግንነት
የተዋጉ አርበኛ ናቸው። ከምስራቁ የኢትዮጵያ
ጦርነት በኋላ ወደአዲስ አበባ ሲመጡ ቤታቸው
መርካቶ ከራጉኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት
ስለነበረ ለጀግንነታቸው ሰፈሩ በስማቸው
ተሰይሟል።
መርካቶ
ላይ በሰጡት ቦታ ራጉኤል ቤተክርስቲያን እና
አንዋር መስጊድ እንዲሰራ ያደረጉ ፊታውራሪ
ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አካባቢው በስማቸው
ይታወቅ ነበር። አባመላ በመባል የሚታወቁት
አርበኛው አሜሪካን ግቢ በተባለው ቦታ ላይ
ችሎት ይሰጡ ነበር።
ራስ
ካሳ ኃይሉ ሰፈር ደግሞ ፈረንሳይ ለጋሲዮን
ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ይገኛል።
ራስ ኃይሉ ሰፈር ደግሞ አበበ ቢቂላ ስታዲየም
አካባቢ ያለው ሰፈር ነው። ራስ ኃይሉ አርበኛ
ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ መስዋዕተነት
የከፈሉ እና በጀግንነታቸው ቦታ ተሰጥቷቸው
የኖሩበት ሰፈር በስማቸው ሜዳ ጭምር ተሰይሞለት
ይገኛል። ደጃች ውቤ ሰፈር ደግሞ ከአራዳ
ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወደ አፍንጮ በር
መሄጃው ላይ ይገኛል። ደጃች ውቤ መኳንንት
እና ባለሃብት የነበሩ እንዲሁም ዘውዲቱ
ምኒልክን አግብተው የኖሩ ታዋቂ ሰው ናቸው።
አዲስ አበባ ሬስቶራንት መኖሪያቸው ነበር።ታዋቂ
ስለነበሩም ሰፈሩ በስማቸው ተሰይሞ እናገኘዋለን።
በሌላ
በኩል አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን
የውጭ አገር ዜጎችም መኖሪያ እንደነበረች
የሚያሳየው የህንድ፣ የግሪክ እና የአርመኖች
ታሪክ ነው። ህንዶች በብዛት ወደ ኢትዮጰያ
መጥተው በተለያየ ሙያ ይሰማሩ ነበር። ወሌ
መሃመድ የተባሉ ህንዳዊም በምህንድስና ሙያቸው
ታላቁን ቤተመንግስት እና ግቢ ገብርኤል
ቤተክርስቲያንን ያነጹ ባለሙያ ናቸው። የአዲስ
አበባን ታሪካዊ ቤቶች በመገንባት እና የከተማዋን
ፕላን በመንደፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
መኖሪያቸውም ከግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን
ጀርባ በመሆኑ አካባቢው በወሌ መሃመድ ስም
ይጠራ ነበር። ህንዳዊ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊ
አግብተው እና ዜግነት ተሰጥቷቸው የኖሩ ባለሙያ
ናቸው።
አትክልት
ተራ አካባቢ ደግሞ መሃመድ አሊ ሰፈር ይባላል።
መሃመድ አሊ ህንዳዊ ነጋዴ ናቸው። መኖሪያ
አካቢያቸው በወቅቱ በነበረው ህዝብ ዘንድ
ታዋቂ ስለነበረ መሃመድ አሊ ሰፈር እየተባለ
ሊጠራ ነበር። ቢኒን የተባሉ ሰውም መስጊድ
ጭምር በስማቸው የተሰየመላቸው እና ፒያሳ
ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አካባቢ በስማቸው
ሰፈር ተሰይሞላቸዋል።
ከራስ
መኮንን ድልድይ ጀምሮ በቅድስተ ማርያም
ቤተክርስቲያን በኩል ያለውን መስመር ይዞ
ያለው ሰፈር ደግሞ አርመን ሰፈር ይባላል።
አርመኖች በአድዋ ድል ወቅት ትልቅ አስተዋጽኦ
በማድረጋቸው በአካባቢው ሰፍረው ነበር።
በአካባቢው ሰባደረጃን የገነቡ እና ለመዲናዋ
የመጠጥ ውሃ በወቅቱ የምትሰጠውን የራስ መኮንን
ምንጭን የገነቡ ናቸው። በከተማዋ የሚገኙ
በርካታ ድልድዮችን የሰሩ እና በጠንካራ
ስነህንጻ ግንባታቸው የሚያወቁ ናቸው።
ስነህንጻቸውን ለማድነቅ የአርመን ቤተክርስቲያንን
እና በአካባቢው ያሉ ጥንታዊ ህንጻዎችን
ለአብነት መመልከት ይቻላል።
መምህር
መክብብ እንደሚናገሩት፤ ግሪኮች በተመሳሳይ
በፒያሳ ወርቅ ቤቶች አካባቢ ቤተክርስቲያን
ገንብተው እና በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው
ስለነበረ ሰፈሩ ግሪክ ሰፈር ይባላል። ከአቡነ
ጴጥሮስ ወደ መርካቶ በሚወስደው መንገድ ላይ
ጣሊያን ሰፈር ይገኛል። ሰፈሩ በአድዋ ጦርነት
ወቅት የተማረኩ ጣሊያናውያን ህክምና እንዲያገኙና
እንዲሰፍሩ የተደረገበት አካባቢ በመሆኑ
ጣሊያን ሰፈር ተብሏል። በአካባቢውም የጣሊያኖች
አሻራ ያረፈባቸው ግንባታዎች ይገኛሉ።
ከዚህ
ባለፈ ደግሞ አራዳ የሚባል ሰፈር ነበር። አራዳ
ማለት እንዳሁኑ አይነት ትርጉም ሳይሰጠው
«እርድ»
ማለት ነበር።
እርድ የሚለው ቃል ለሁለት የተከፈለ የሚለውን
ይገልጻል። ከሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አንስቶ
በአቡነ ጴጥሮስ አድርጎ ፒያሳ ራስ መኮንን
ድልድይ ያለው አካባቢ በወንዞች ተከፍሎ ብቻውን
ስለነበረ አራዳ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል።
ፒያሳ
አካባቢ ደግሞ ሰራተኛ ሰፈር የሚባል አለ።
በወቅቱ ለቤተመንግስት የእደጥበባት፣ የብር
እና የነሃስ ዋንጫዎች እና ጌጣጌጦች እንዲሁም
የቤት ውስጥ መገልገያዎችን የሚያመርቱ
የከጎጃምና ከጎንደር መስቀሎችን እና ጌጣጌጦችን
የሚሰሩ ሰዎች የሰፈሩበት ነበር። ከወሊሶ
እና ከኮኖ ቂሌ የመጡ ወንበር እና የእጅ ጌጦችን
የሚሰሩ፣ ከጅማ ስጋጃ እና መጋረጃዎችን
የሚያዘጋጁ ከአክሱም የመጡ የተለያዩ እደጥበባት
ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሰራተኛ ሰፈር ኖረዋል።
በመሆኑም ሰፈሩ አሁንም ድረስ ሰራተኛ ሰፈር
ይባላል።
እጨጌ
ሰፈር ደግሞ ልደታ ይገኛል። 57ኛው
የኢትዮጵያ እጨጌ እና ኢትዮጵያ ከግብጽ ጳጳስ
ማስመጣት ስታቆም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ
ጳጳስ ሆነዋል። የቤተክርስቲያንን የህገደንብ
ያወጡ ምሁር ነበሩ። ገዳም ሰፈር ደግሞ ዳግማዊ
ምኒሊክ ከአድዋ ጦርነት ሲመለሱ የተመሰረተ
ነው። በአድዋ ድል ወቅት ከተለያዩ የኢትዮጵያ
አካባቢዎች የሄዱ የቤተክርስቲያን ሰዎችና
ታቦታት በድሉ ማግስት ወደአዲስ አበባ መጥተዋል።
ካህናቱ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጀርባ ወደ
ሰሜን ሆቴል መሄጃ ላይ ሰፍረው ነበር። ሰፈሩ
አሁን ላይ ጭፈራ ቤቶች ቢበዙበትም ቀድሞ
የቀሳውስት እና ዲያቆናት መኖሪያ በመሆኑ
ገዳም ሰፈር የሚለውን ስያሜ መያዙን መምህር
ምክብብ ያስረዳሉ።
ሰፈር
ሲባል ከብሔርና ከሀገር ጋር የተያያዘ ታሪክም
አለው። በሌላ በኩል የአንድ አካባቢ ማህበረሰብ
ሰዎች አንዱ አንዱን እየሳበ በብዛት የኖሩባቸው
ሰፈሮች በብሄሩ ስም ተሰይሞ እናገኛቸዋለን።
ወሎ ሰፈር ቦሌ አካባቢ ለንግድ የመጡ ወሎዬዎች
በብዛት የኖሩበት ነበር። መርካቶ ጎጃም ሰፈር
ደግሞ ቅቤና ማር የሚሸጡ የጎጃም ሰዎች ስለነበሩ
ሰፈሩ በስማቸው ተሰይሟል። ወለጋ ሰፈር ደግሞ
ከመዘጋጃ ጀርባ ፖስታ ቤት አካባቢ ይገኛል።
በብዛት የወለጋ ተወላጆች ስለነበሩበት ወለጋ
ሰፈር ይባላል። ጅሩ ሰፈር ደግሞ እሪበከንቱ
አካባቢ ከጅሩ ለንግድ የመጡ ሰዎች በብዛት
የሚኖሩበት ነበር። ወደተክለሃይማኖት አካባቢ
ደግሞ ስለጤዎች በብዛት ስለነበሩ ሰፈሩ
በስማቸው ተሰይሞላቸዋል።
ሽሮሜዳ
አካባቢ ጋሞ ሰፈር፣ አዲስ ከተማ ትምህርት
ቤት ጀርባ ቸሃ ሰፈር፣ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ
ችሎት አካባቢ ደግሞ ሶዶ ሰፈር እንዲሁም ኮልፌ
አካባቢ ምሁር ጉራጌ ሰፈር ይባላሉ። ቀድሞ
ዘመድ እና ዘር እየፈለጉ የኖሩ ሰዎች ከተማዋን
እየተላመዱ እና ከሌላው ብሔር ተወላጅ ጋርም
እየተግባቡ ሲመጡ ከሰፈሮቻቸው ወጥተው በአራቱም
አቅጣዎች ላይ ሰፍረው እናገኛቸዋለን።
«የሁሉም
መኖሪያ የሆነችውን አዲስ አበባን ሰፈሮች
ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ሰፈሮቿ በማይዳሰሱ
ቅርስነት ተመዝግበው ሊጎበኙ እና የህብረብሔራዊነትን
ምሳሌ በመሆናቸው ልናውቃቸው ይገባል»በሚለው
በምክረ ሃሳብ ቅኝታችንን ያሳርጋሉ የመረጃ
ምንጫችን መምህር መክበብ ገብረማሪያም።
ቆንጆ ፅሁፍ
ReplyDelete