Translate/ተርጉም

Wednesday, November 7, 2018

የሴቷ ጉዞ- በኪነጥበብ መነጽር


የሴቷ ጉዞ- በኪነጥበብ መነጽር
ሊድያ ተስፋዬ
ሰዎች በኪነጥበብና በእያንዳንዱ የጥበብ ዘውግ ሰዎች ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን ሲገልጹ ኖረዋል። የደገፉትንና የሚቃወሙትን ተናግረውበታል፤ የሚፈልጉትንና የሚጠሉትን ጠቁመውበታል፤ ለመብታቸው ታግለው አዳዲስ የትግል ሃሳቦችንም አቀብለውበታል። በኪነጥበብ ገድሎች ተነግረዋል፤ አሸናፊዎችና ብዙ ፈተናን የተመለከቱትም አረአያነታቸው ታትሞ እንዲቀር ሆኗል።
በኪነጥበቡ ብዙ ከተነገሩና ከታዩ ትግሎች መካከል አንዱ የቀለም ልዩነት ጉዳይ ነው። ከዚም ባሻገር የኑሮ መደብ ያመጣቸውን ልዩነቶች በማንሳት የተጨቆኑትን የምስኪኖቹን ድምፅ ለማሰማትና ታሪካቸውን ለመንገር ኪነጥበብ አቻ የሌለው መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሌላው ተመሳሳይ እይታ ያለው የሴቶች ጉዳይ ነው። ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ያለው የሴቶች «እንደ ሰው እንታይ» ጥያቄ፤ ለዘብ ባለ ሁኔታም ቢሆን በኪነጥበብ ሥራዎች ተቃኝቶ እያንዳንዱን ማኅበረሰብ ለመድረስ ተሞክሯል።
መቼም በያዝነው ዓመት በመንግሥት በኩል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በካቢኔያቸው እንዲሁም በፕሬዚዳንትነትና ከፍተኛ የሥራ ቦታዎች ላይ ሴቶችን ሰይመዋል። ይህ ማለት፤ ወደድንም ጠላንም የሴቶችን ጉዳይ ለመስማት ሁላችን ግድ አለብን ማለት ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ሴቶችም በ«እንችላለን» መንፈስ ያቆዩትን ሁሉ ወደ ተግባር ለውጠው እንዲያሳዩ የሚጠበቅበት ጊዜም ነው።
ይህ በዚህ ይቆየንና የጥበብን ምልከታና የሴቶችን ጉዞ እናንሳ። በጥበብ ሥራዎች በአንድ በኩል አዳዲስ ሃሳቦችን ማቅረብና ማኅበረሰብን ማነቃቃት ሲቻል በተጓዳኝ የቀደሙ ታሪኮችን ፈልፍሎ በማውጣትና በማራኪ መንገድ በማቅረብ ንቃትን መፍጠር ይቻላል/ተችሏልም። ይህ እንደየአገሩ የተለያየ መልክና ገጽታ ያለው ሲሆን፤ እንደ ኪነጥበብ ባለሙያዎች የምልከታ ርቀትም ይወሰናል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ስለአንዲት ጥቁር አሜሪካዊት የሚተርክ ፊልም በሆሊውድ ለእይታ ቀርቦ ነበር። የታሪኩ መነሻና ሊነገር የተፈለገው ክስተት የዛች ጥቁር አሜሪካዊት ሴት እንቢ ባይነትና ጽናት እንዲሁም ድፍረት ነው። እንዲህ ነው፤ በ1955በዚያው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር፤ ሮዛ ፓርክስ የተባለች ሴት ከሥራ መልስ ወደቤቷ ባቡር ተሳፍራለች። በባቡሩም ቦታ ይዛ ተቀምጣለች።
በጉዞው መካከል አንድ ነጭ ቀለም ያለው አሜሪካዊ ቀርቦ ከተቀመጠችበት እንድትነሳ አዘዛት፤ ለሌላ አይደለም ጥቁር ስለሆነች ብቻ። ጊዜው ጥቁሮች ይገለሉና ይናቁ እንዲሁም ብዙ መከራን ያዩ የነበረበት ነው። ሮዛ ታድያ ከወንበሯ ንቅንቅ አላለችም፤ «አልነሳም» በማለት መብቷ መሆኑን አረጋገጠች። የዚህች ሴት ታሪክ ታድያ በዘመኑ ለነበሩ መነቃቃትን አልፈው ለሚሰሙ ደግሞ ብርታትን የሚሰጥ ሆነ። በቀለም እንዲሁም በሴትነት የሚደርስን በደል የተቃወመችው ሮዛ ፓርክስ፣ ራሷን፣ የዘመኗን ጥቁር አሜሪካውያን አድምቃለች። አልፎ ታድያ ዜናው በዓለም የናኘው በኪነጥበብ ሥራዎች ማንነቷና ሥራዋ ጎልቶ እንዲታይ በመደረጉ ጭምር ነው።
አሁንም ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር አልወጣንም፤ በ1973 ነው። ቢሊ ጂን የተባለች ሴት እና ቦቢ ሪግስ የተባለ ወንድ ቴኒስ ተጫዋቾች ፊት ለፊት ተፋጠዋል፤ ይህም እውነተኛ ታሪክ ነው። ወቅቱ በስፖርቱ ዓለም በተለይም በቴኒስ ውድድር ላይ የሴቶች ተሳትፎ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው። በውድድሮች የተሳተፉና አሸናፊ የሆኑ ሴቶች ቢገኙ እንኳ የወንዱን ያህል ሽልማት አይሰጣቸውም ነበር።
ቢሊ ጂን ይህን ተቃውማ ነው እንግዲህ በ1973 ላይ ምርጥ የቴኒስ ተጫዋች ከተባለው ቦቢ ሪግስ ጋር ፍልሚያ የገጠመችው። በውድድሩ አሸናፊ መሆንም ችላለች። የዚህችን ሴት ታሪክ የሚዘክረው «Battle of the Sexes» ፊልምም ከአንድ ዓመት በፊት ለእይታ ሲቀርብ፤ የሴቶችን ትግልና ብርታት እንዲሁም መቻልን በቃል እንዴት መግለጥ እንደሚገባ ማሳያ ሆኗል። እነዚህን ከቀረቡን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ በመጽሐፍትና በሌሎች ስነጽሑፋዊ ሥራዎችም የተነሱ በርካታ ተመሳሳይ ታሪኮችን እናገኛለን።
ይህ የሚያሳየን፤ በባህር ማዶ የፊልም ዘርፎች በሴቶች ንቅናቄዎችና ትግሎች ላይ በርካታ ፊልሞች እንደተሠሩ ነው። ወደአገራችን መለስ ብለን ደግሞ ንቃኝ፤ በእኛ አገር ደረጃ አዲስ ሃሳቦችን በማቀበልና ለሴቶች የመብት ትግል ተጨማሪ ግብዓት በመሆን ብዙ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን መጥቀስ ይከብዳል። እንደውም የኪነጥበብ ሥራዎች በአገራችን የሴቶችን ድርሻ እያሳነሰና እያንቋሸሸ የሚታይበት ጊዜ በብዛት ይስተዋላል።
ይሁንና የቀደሙ ታሪኮችን በመንገር በኩል የተሻለ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ታድያ በቂ ሆኖ አይደለም፤ እጅግ ጥቂትም ቢሆን ግን ደምቆና ጎልቶ የሚነሳ አይጠፋም። በፊልሞችም ባይሆን በስነጽሑፍ ደምቆ እናየዋለን። ወደቴአትር ሥራ ስናቀና ታድያ «የቃቄ ውርድወት» የተሰኘው እውነተኛ ታሪክ እናገኛለን። እንድውም በዓለም መድረክ ቴአትሮቻችንን ይዞ መውጣት ወይም ተመልካች እንዲያገኙ ለማድረግ ችሎታና አቅማችን እንዲሁም ተነሳሽነታችን ዝቅተኛ መሆኑ እንጂ በዓለም ሊደነቅ የሚገባው ታሪክ ነበር፤ የቃቄ ውርድወት።
በቅድሚያ ስለቃቄ ውርድወት ታሪክ በአጭሩ እናንሳ። በ1830ዎቹ የተከሰተ እውነተኛ ታሪክ ነው። ታድያ በየዘመኑ ህግ ሲጠነክርና ሲበረታ ባለው ላይ ነውና፤ ዘመኑም ህግና ስርዓት የጠበቀበት ጊዜ ሆኖ በሴቶች ላይም ጫናው በርትቶ ነበር። ሴቶችም እንደ ታዛዥ ወታደር የተባሉትን ከማድረግና እናቶቻቸው የሆኑትን ተከትሎ ከመሆን ባሻገር ቀና ብለው ለመናገርም ሆነ ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚከተሉት ምሳሌ አልነበረም።
በዚህ መካከል ነው ከጉራጌ ምድር ውርድወት የተወለደችው። የቃቄ ልጅ። የቃቄ ውርድወት ከእናቷ ከወ/ሮ አሚና እና አንቱ የተባሉ ባለሀብት ከሆኑት አባቷ ቃቄ በጉራጌ ዞን ሙህር አክሊል ወረዳ ልዩ ስሙ ዠርመኘ ከሚባል አካባቢ ነው የተወለደችው። በቤተሰቧና በአካባቢው ነዋሪዎችም ተወዳጅ ሆና አደገች።
ውርድወት ነፍስ ካወቀች በኋላ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል መቃወም ጀመረች። መነሻ የሆናትና ነገሩን ሁሉ ያፈነዳው ደግሞ ትዳር ከመሠረተች በኋላ የተከሰተው ነገር ነው። ውርድወት በደማቅ ስነስርዓት ከአንድ ጀግና ወጣት ጋር ትዳር ትመሰርታለች፤ ይሁንና ቆይታ አንድ እውነት ታውቃለች፤ ለባሏ ሦስተኛ ሚስት መሆኗን።
ነገሩ የባህል ጉዳይ ነበር፤ እርሷ ግን አልተቀበለችውም። ስለዚህ ንቅናቄውን ጀመረች፤ እያንዳንዱን ዕርምጃም ራሷ እየተራመደች የጉራጌ ምድር ሴቶች ሁሉ እንዲከተሏት ጠየቀች። እንደውም እንደ ወንዶች ሁሉ ሴቶችም ሦስት እንዲያገቡ መፈቀድ አለበት አለች። ጥያቄው ለባህላዊው የጉራጌ ምድር ሸንጎ /ጆካው/ አዲስ ነገር ነበር። ውርድወት የሴቶችን መብት ይመለከታል ያለችውን ጉዳይ ጠቅሳ አስር የስርዓት ማሻሻያ ነጥቦችን ዘረዘረች፤ አገር ጉድ አለ።
ከነጥቦቹ መካከል ከአንድ በላይ ጋብቻ ይቅር፣ ትዳር በፍላጎት ብቻ ይመሥረት፣ የፍቺ ጥያቄ በሴቶች ይወሰን፣ የልጅ መጠሪያ ስም በእናት ይሁን የሚሉት ይገኛሉ። የሸንጎው አባቶች ቢጨንቃቸውና የሴቶቹ ንቅናቄ ቢያስደነግጣቸው፤ የውርድወት ባል እንደፈቃዷ እንዲፈታትና እርሷ እንደልቧ እንድትሆን ሲሉ ባሏን ቃል አስገቡት። የእርሷ ነፃ መሆን ምንአልባት ጥያቄዋን ከማንሳት የሚያግዳት ይሆናል ብለው በማሰብ ነው።
ያም ቢሆን እርሷ ግን መጮኋን አላቆመችም ነበር። ለውጥ እንዲመጣና የሴቶች መብት እንዲከበር ብዙ ታግላለች። የውርድወት ትግል በትግልነት ታሪክ ሆኖ ይነገር እንጂ፤ በጊዜው ሰሚ አልነበራትም። ሴቶችም የባሎቻቸውን ተጽእኖና ዱላ ፈርተው በየቤታቸው ተከተቱ። ለራሷ ግን ነፃነትን አግኝታለች፤ የታገለች ሴትም የት ድረስ አቅም ሊኖራት እንደሚችል አሳይታለች።
እንግዲህ ይህ ታሪክ ነው፤ በቴአትር ባለሙያው ጫንያለው በቀለች ወልደጊዮርጊስ ተደርሶ በዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ የተዘጋጀው። «የቃቄ ውርድወት» ቴአትር ለዓመታትም በብሔራዊ ቴአትር ሲታይ ቆይቷል። ምንአልባትም ቴአትሩ ሴቶችን በሚመለከት ከተሠሩ ታሪካዊና ትውፊታዊ ቴአትሮች በአንደኝነት የሚቀመጥ ነው ማለት ይቻላል። አንጋፋና ወጣት ተዋንያንን ጨምሮ ከአንድ መቶ በላይ ባለሙያዎችን ያሳተፈው ይህ ቴአትር፤ የሁለት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ቆይታን ከተመልካች ጋር ያደርጋል።
ከዚህ ቀደም ደራሲው ጫንያለው ይህን የውርድወትን ታሪክ ወደ ቴአትር ለመቀየርና ለመድረክ ለማብቃት መነሻ የሆነውን ምክንያት ተጠይቆ ሲናገር፤ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት በጉራጌ ምድር የሆነው ድንቅ ታሪክ ራሱንም ያስገረመው በመሆኑና የውርድወትን ቃል ተፈጻሚነት ለማወጅ እንደሆነም ተናግሯል። ውርድወት በዘመኗ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች አሁን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምትኖር ሴት ታስበዋለች ብሎ መገመት እንደሚያዳግትም ይገልጻል።
እንደውም የውርደወት የሴቶች መብት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ አኳያ ሲታይ ሀገራችንን ቀደምት እንደሚያደርጋት ጫንያለው ተናግሯል፤ ታሪኩ ለኢትዮጵያውያን አይደለም ለአፍሪካውያን ጭምር መኩሪያ እንደሆነም ነው ያነሳው። ወደኋላ አንድ መቶ ስድሳ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የተፈጸመው ይህ ገድል፤ ምንአልባትም ኢትዮጵያንም በሴቶች እንቅስቃሴና ትግል ላይ በቀዳሚነት የተነሳች አገር ሳያሰኛት አይቀርም።
ከላይ የጠቀስናቸውና ከአውሮፓ የመረጥናቸውን ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፤ ፊልሞቹ በቅርብ ዘመን የተሠሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የተከሰቱበት ዘመንም እንዲህ እንደ ውርድወት ታሪክ የቀደመ አይደለም። እንደውም በዓለማችን ላይ አሁን የሚሰማውን የሴታዊነት ወይም ፌሚኒዝም አስተሳሰብ አውሮፓውያኑ ያደመቁት በራሳቸው አቆጣጠር በ1837 አካባቢ ነው። ይህም የውርድወት ገድል ከተፈጸመበት ዘመን ጋር ተቀራራቢ ነው።
ሌላው፤ ይህ ቴአትር መድረክ ላይ መታየት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተዋንያን ስም ላይ አዳዲስ ለውጥ ማየት ጀምረን ነበር፤ በእናት ስም መጠራት። ጫንያለው በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቆ ሲናገር፤ የውርድወት ታሪክ መነሻ ሆኗቸውና አነቃቅቷቸው በቴአትሩ ላይ የተሳተፉ ሁሉ በእናታቸው ስም መጠራት እንደጀመሩ ገልጾ ነበር። ይህ ማለት፤ ከቃቄ ውርድወት ታሪክና ገድል በተጨማሪ የቴአትሩ መሠራትና መድርክ ላይ መቅረብ ይህን ተጽእኖ መፍጠር ችሏል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ተጽእኖ ፈጣሪ ሥራዎችን ደግሞ በቴአትር ቤቶቻችን መድረክ ላይ፣ በሲኒማ ቤቶች እስክሪን ላይ ልናይ እንጓጓለን።
ቴአትሮቻችን፣ ፊልሞቻችን፣ መጻሕፎቻችንና ሌሎችም ጥበባዊ ውጤቶች እነዚህን እውነቶች በማውጣት ለአገርም ለሴቶችም የሚበጀውን ሥራ መሥራት ይችላሉ። አሁንም ገና ያልተነኩ ብዙ ታሪኮች፤ ያልተነገሩ እውነቶችና ማንነቶች እንዳሉ እናምናለን። ይህን በማውጣት በኩል ደግሞ የኪነጥበብ ባለሙያው ከማንም በላይ ኃላፊነት አለበት። ጥበብ ነፃነትን ከፈለገች፤ ነፃ ላልወጡትም ብርሃን እንድትሆን ይገባልና፤ ይህም በእኛ አገር መድረክ እውን ሆኖ፤ የቃቄ ውርድወትን አረአያነት የሚከተሉ ሴቶች ብቻ ሳይሆን የቴአትሩን ፍሬ ዓይተው ሌላ ፍሬ ለማፍራት የሚሯሯጡ ባለሙያዎችን ለማየት በተስፋ እንጠብቃለን። ሰላም!


No comments:

Post a Comment