Translate/ተርጉም

Wednesday, November 7, 2018

የቅዠት መድኃኒት


የቅዠት መድኃኒት
ዋለልኝ አየለ
የአንድ ቀን አጋጣሚ ነው ብየ ላልፈው ነበር፡፡ ነገሩ ግን ተደጋጋመብኝ፡፡ አንድ ቀን መገናኛ ከታክሲ እንደወረድኩ የሆነች መኪና ውስጥ በትልቅ ሞንታርቦ (ድምፅ ማጉያ) የአንድ መጽሐፍ ጥቅም እየተዘረዘረ ነው፡፡ እንግዲህ ከተንታኙ እንደተረዳሁት መጽሐፉ ስነ ልቦና ነው፤ መንፈሳዊ ነው፤ ሳይንስ ነው… ምን ልበላችሁ ብዙ መጽሐፎችን የያዘ ነው፡፡ ዝርዝሩ ቢነበብ ደግሞ ፖለቲካም ይኖረው ይሆናል፡፡
ከመጽሐፉ ጥቅሞች ውስጥ ጥርሳቸውን ለሚያንቀራጭጩ፣ ለሚለፈልፉ፣ ሌሊት ሌሊት ለሚቃዡ፣ ለሚወራጩ… የመሳሰሉ ጥቅሞች ተዘርዝረዋል፡፡ በነገራችን ላይ መገናኛ ሰው ስለሚበዛበት እንዲህ አይነት መድኃኒት የሆኑ መጽሐፍት መሸጥ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ መቼ በዚህ አበቃና፡፡ እሱን ለምጀው ሳለ ሰሞኑን ደግሞ ፒያሳ አጋጠመኝ፡፡ ጥርሳቸውን ለሚያንቀራጭጩ፣ ሌሊት ሌሊት ለሚቃዡ እያለ ያስተዋውቃል፡፡ ይቺኛዋ ገለጻ ግን ቀልቤን ሳበችው፡፡ ሌሊት ስለምቃዥ አይደለም (ኧረ እኔስ ቀንም አልቃዥም) እነዚህ ሰዎች እንዲህ መላ ካላቸው ቀን ቀን ለሚቃዡትም መላ ይፈልጉልን፡፡ እኛ የሌሊቱ አላስቸገረንም፡፡ ሌሊት የሚቃዡ ቢያንስ ቢያንስ የሚረብሹት ቤተሰባቸውን ብቻ ነው፡፡ ቀን ቀን የሚቃዡት ግን አገር እየረበሹ ነውና አሁን መጽሐፍ የሚያስፈልገው ለእነዚህ ሰዎች ነው፡፡
የምር ግን እነዚህ መጽሐፎች ምን አይነት መጽሐፍ ናቸው? በመንፈስ የሚያድኑ ወይስ ሳይንሳዊ መጽሐፍ ሆነው ነው? መጽሐፎቹ መንፈሳዊ ካልሆኑ በስተቀር መቼም መጽሐፍ ማንበብ ጥርስን ከማንቀራጨጭ እንዴት ሊከላከል እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ሌሊት ለሚቃዡትስ ቢሆን? ያንን መጽሐፍ ያነበበ አይቃዥም ነው? ወይስ መቃዠት ሲጀምር ተነስቶ ማንበብ ነው? ሲቃዡ ተነስቶ ማንበብ ከሆነማ የትኛውንም መጽሐፍ መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ደግሞስ የሚቃዢ ሰው እንዴት ነው ይህን የሚያስበው? ይህን መጽሐፍማ ገዝቸ ማየት አለብኝ (ይህኔ መቃዠትን ለመከላከል የሚያግዙ አሥር ዘዴዎች የሚል ይሆናል)፡፡
በነገራችን ላይ (ያው ነገርን ነገር ያነሳዋል) የመጽሐፍ ነገር ከተነሳ እነዚህ በሦስትና አራት ቀን ውስጥ የሚዘጋጁ መጽሐፎች ነገርም ይገርመኛል፡፡ እንኳን መጽሐፍ ጋዜጣና መጽሔት በሁለትና ሦስት ቀን አይዘጋጅም፡፡ መጽሐፍ የብዙ ዓመታት ልምድ፣ ጥናት፣ አስተውሎት የተካተተበት ነው እንጂ እንዴት በአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ መጽሐፍ መጻፍ ይቻላል? ወቅታዊ ጉዳይ ቢኖር እንኳን ያ ጉዳይ ከሌሎች ዓመታት ሁነት ጋር መነፃፀር አለበት፡፡ በተለይ የፖለቲካ መጽሐፍ ደግሞ የታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ ታሪክ እየተሰነደ ይቀመጣል፤ መጽሐፍ ሲሆን ግን ሌሎች ሁነቶችንም በማየትና በማነፃፀር ነው፡፡
በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ቤተ መንግሥት መግባቱን ተከትሎ ብዙ የማህበራዊ ድረ ገፆች ትንበያ ነበር፡፡ «መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ ነበር» ተባለ፡፡ ወዲያው በሁለተኛው ቀን ይህን ርዕስ የያዘ መጽሐፍ ወጣ፡፡ ሰዎች በፌስቡክ ሲቀባበሉት ደግሞ አንድ ማስተባበያ ሰማን፡፡ ማስተባበያው እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንጂ መጽሐፉ ከተዘጋጀ የቆየ መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡ ማስተባበያው እውነት ነው እንበል!
የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ጎልቶ የሚታየው የዶክተር አብይ ፎቶ ነው፡፡ ዶክተር አብይ ሥልጣን ከያዙ ገና ዓመት እንኳን አልሆነም፤ ታዲያ መቼ የተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ነበር? በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በደርግ የተደረገውን ከሆነ የመጽሐፉ ዋና ሽፋን ዶክተር አብይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሙሉውን ባላነበውም መጽሐፉ የፌስቡክ ስብስብ ነው፡፡
ዶክተር አብይ የተመረጡ ሰሞን የወጣ አንድ መጽሐፍም ነበር፡፡ እዚህ መጽሐፍ ላይ ግን የሆነ ማጭበርበር የተሠራ ይመስለኛል፡፡ ይመስለኛል ያልኩት አንድ ጓደኛዬ ተጭበርብሮ ስለገዛ ነው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ እስከዳር ነጋ ይላል፡፡ እስክንድር ነጋ ታዋቂ ስለሆነ እሱ መስሏቸው እንዲገዙት የታሰበ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ ጓደኛዬ ‹‹የእስክንድር ነጋን መጽሐፍ ገዝቸ መጣሁ›› አለኝ፡፡ ሳቅኩበትና ‹‹እስክንድር ነጋ አይደለም እሰከዳር ነጋ ነው የሚለው ፤ ልብ ብለህ እየው›› አልኩት፤ ሲያየው ሌላ ነው፡፡
የእስክንድር ነጋ ካልሆነ መጽሐፉ ጥሩ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ ማንም ይጻፈው የሚፈለገው የመጽሐፉ ይዘት ነበር፡፡ ግን መጽሐፉ የፌስቡክ ስብስብ ነው፡፡
ከዚህም የባሰ ደግሞ አንድ ልጨምርላችሁ፡፡ ደግነቱ ይህኛው መጽሐፍ ፖለቲካ ስላልሆነ ማንም ልብ አላለውም፤ ግን ገበያ ላይ ተዘርግቶ ነበር፡፡ ‹‹የቦሌ ጉዶች›› ይላል መጽሐፉ፡፡ ሽፋኑ የተራቆተ የሴት ጭን ነው የሚያሳየው፡፡ መጽሐፉ የታተመው ምንም ነገር ሳይጨመርበት ከወሲባዊ የፌስቡክ ገፆች ነው፡፡ መጽሐፉ ያስቃችኋል በቃላትና በቃላት መካከል ባዶ ቦታ(ስፔስ) የሚባል ነገር ይለውም፡፡ ብዙ ጊዜ ከኢንተርኔት ኮፒ ስናደርግ ይደበላለቃል፡፡ እንደገና ነው አንቀፅ የምንሰራለት፡፡ ይህ መጽሐፍ ይሄ እንኳን አልተሠራለትም፡፡ የይዘቱ ነገር ይቅር፤ ግን ምናለ አንቀፅና በቃላት መካከል እንኳን ክፍተት ቢኖረው? እኔ የሚያናድዱኝ ጸሐፊዎች ሳይሆኑ ግዥዎች ናቸው!
ያ ለቅዠት የሚያገለግለው መጽሐፍ ግን የምር ሳያስፈልገን አይቀርም! ችግሩ ሌሊት ለሚቃዡት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ እኔ ግን የቀን ቅዥት ነው ያስቸገረኝ፡፡ ቆይ ግን መጽሐፉ ከባህል መዳኃኒት ነው እንዴ የተሰራው? ወይስ የደብተራ መጽሐፍ ነው? መጽሐፉ በዝርዝር ቢነበብ እነዚህ ነገሮች አይጠፉም፡፡
አሸን ክታብ አንገታችሁ ላይ እሰሩ፤ ያለሰዓት (ሌሊት ማለት ነው) ከቤት አትውጡ… እያለ የሚመክር ይመስለኛል፤ በዚህ ከቀጠለ ጥቁር ዶሮ፣ ገብስማ ዶሮ አርዳችሁ እንዲህ አድርጉ ማለቱም አይቀርም፡፡
እስኪ በመጨረሻ ደግሞ ምክር ብጤ ጣል ላድርግ፡፡ ይህኔ እኮ የእነዚህ መጻሕፍት ባለቤቶች ‹‹አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል›› እያሉኝ ይሆናል፡፡ እንደ አጠቃላይ በአገራችን የንባብ ባህል ላይ ብዙ ሃሜት ቢኖርም ከዚያውም ብሶ ደግሞ ያውም ያለው አሉቧልታ ያስደስተዋል፡፡ የሳይንስና የጥናትና ምርምር ሥራን የያዙ መጻሕፍት ማንም አያነባቸውም፡፡ የመንደር አሉቧልታ ያሰባሰበ ግን እስከ 10ኛ ዕትም ድረስ ይቸበቸባል። ጎበዝ ሁሌም ተመሳሳይ ነገር ብቻ ከምናነብ የሳይንስና የምርምር ሥራዎችንም እናንብብ! ካነበብን ከቀንም ይሁን በሌሊት ከመቃዠት እንድናለን!

No comments:

Post a Comment