Translate/ተርጉም

Wednesday, November 7, 2018

ግብርና እና ባህል


ግብርና እና ባህል
ዋለልኝ አየለ
ባህል ሲባል አለባስና አጨፋፈር ብቻ ነው አይደል ትዝ የሚለን? በነገራችን ላይ ይህ የሆነው በጣም ከመደጋገሙ የተነሳ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን የባህል ፕሮግራም ቀረበ ከተባለ አለባበስና አጨፋፈር አለፍ ሲልም አመጋገብ ነው፡፡ ደግሞ እኮ ባህልን ስናብራራ ‹‹ባህል ሰፊ›› ነው የሚለውን እንጠቀማለን፡፡ እንዲህ ብለን ግን የምናቀርበው ጠባቡን ብቻ ነው፡፡ ሰፊ ነው ከተባለ ስለሁሉም ማውራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ባህል የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው›› የሚል የተለመደና ተደጋጋሚ ማብራሪያ አለ፡፡ አንድ ማህበረሰብ ግን የሚለየው በአለባበስና በአመጋገብ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ የሚለይባቸው ነገሮች ይኖሩታል፡፡
እስኪ ለዛሬ ግብርና እና ባህልን እንይ፡፡ መግቢያ ላይ ያለውን ሐተታ የተጠቀምኩት ‹‹ደግሞ ግብርና ከባህል ጋር ምን አገናኘው?›› የሚል ሃሳብ ይነሳል ብዬ ስለሰጋሁ ነው፡፡ በእርግጥ ሥጋቴ እውነት የመሆኑ ነገር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ባህላዊ ግብርና፣ ባህላዊ አስተራረስ፣ የግብርና ስነ ቃል›› የሚሉ ከግብርና ጋር የተያያዙ ዜናና ፕሮግራሞችን እንሰማለን፡፡ እነዚህም ግን ግብርና እና ባህልን በትክክል አልገለጹልኝም፡፡ እንዲያውም ባህላዊ ግብርና እና ባህላዊ አስተራረስ የሚሉት ነገሮች ኋላቀርነቱን ለመግለጽ እንጂ በውስጡ ያለውን የአካባቢውን ባህል ሲገልጹት አይስተዋልም፡፡ እስኪ ስለግብርና እና ባህል ትስስር እናውራ! የተሠራ ጥናትም ዋቢ እናደርጋለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን እኔም የማውቀውን ልንገራችሁ፡፡
ወቅቱ የመኸር ወቅት ነው፡፡ የመኸር ወቅት ነው ማለት አዝመራው ደርሶ የሚሰበሰብበት ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ግብርና እና ባህልን በጥብቅ የሚያቆራኛቸው ወቅት ቢኖር ይሄ የመኸር ወቅት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የአውድማ ላይ ስነ ሥርዓቶች የተለየ ክዋኔ አላቸው፡፡ ሰብሉን መሰብሰብ ላይ ያን ያህልም ጎላ ያለ ባህላዊ ይዘት የለውም (ከአሠራሩ በስተቀር)፡፡ የአውድማ ላይ የባህል ህግና ደንቦችን ልንገራችሁ፡፡ ምናልባት ከአካባቢ አካባቢ የሚለያይ ሊሆን ስለሚችል ይህ ጽሑፍ በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የሚመለከት ነው፡፡
ምናልባት ጤፍ ውድ ስለሆነ ይመስላል ጣጣው የሚበዛው የጤፍ አውድማ ላይ ነው፡፡ የዚህ ልማዳ ዋና ዓላማም ከፍተኛ ምርት ለማግኘት ነው(በረከት፤ ረድኤት) ይሉታል እነርሱ፡፡ ገና ከአውድማ ልቅለቃው ልጀምርላችሁ፡፡ አውድማ መለቅለቅ ማለት የጤፉ ምርት የሚመረትበት አቧራም ሆነ ጠጠር የሌለው ምቹ ቦታ መፍጠር ነው፡፡ በከብት እበት ይለቀለቃል፡፡
አውድማው ከተለቀለቀበት ሰዓት ጀምሮ ሰው ከአጠገቡ አይለየውም፡፡ አንደኛው ምክንያት ሰይጣን ገብቶ የምርቱን በረከት እንዳይቀንሰው ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ከብትም ሆነ ሌላ አካል የተለቀለቀውን አውድማ እንዳያበላሸው ነው፡፡ ከአውድማው መሃል (እምብርት ይሉታል) ላይ ብረት ነክ ዕቃ(ማጭድ፣ ምሳር…) ከእሬት ተክል ጋር ይቀመጣል፡፡ የብረት ዕቃው አስፈላጊነት ብረት ሰይጣንን ስለሚያርቅ ነው፡፡ ምናልባት እሬቱም ስለሚመር ይሆን? ጤፉ በበሬ ከተበራየና ከመረተ በኋላም ብዙ ባህላዊ ደንቦች አሉት፡፡ ልክ ቤተ መቅደስ ሴት አይገባም እንደሚባለው ሁሉ አውድማው ውስጥም ሴት አይገባም፤ ለየት የሚያደርገው ልጅአገረድ የሆኑ ሴቶች ግን መግባት ይፈቀድላቸዋል፡፡
ሌላው ደግሞ ምርቱ ሲሰፈር ያለው ስነ ሥርዓት ነው፡፡ ምርቱ ሲሰፈር ትክሻ ላይ ነጠላ ተለብሶ ነው(አለባበሱ የራሱ ሥርዓት አለው)፡፡ የመጀመሪያውን ዙር አባት(ሽማግሌ) ይሰፍረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ማንም ቢሰፍረው ችግር የለውም፡፡ ምርቱ ሲሰፈርም እንደ ቡና፣ ቆሎ እና እንጀራ የመሳሰሉ ምግቦች ይቀርባሉ፡፡ በበራይ ሥራውም ከጠዋት ጀምሮ የሚዘጋጁ ምግቦች አሉ፡፡ የምሳ ሰዓቱና የእራት ሰዓቱ የተለመደው የምግብ ዓይነት ሲሆን ጠዋት ቁርስ ላይ የሚበላው ግን ጤፍ በሚወቃ ጊዜ ብቻ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ይህ ምግብ «ርህጥ» ወይም «አግማስ» ይባላል፡፡
አሁን ከልማድ እንውጣና በግብርና እና ባህል ላይ ወደተሠራ ጥናት እንለፍ፡፡ ጥናቱ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ ነው፡፡ አጥኚው ዶክተር ሰዋገኝ አስራት ‹‹የባህላዊ ግብርና ዕውቀት ትንተና በጓጉሳ ሽጉዳድ ወረዳ›› በሚል ርዕስ በሠሩት ጥናት ባህላዊ የግብርና ዕውቀት ያልተጻፈ ዕውቀት ነው፡፡ ይሄውም ባህላዊ ግብርና ማህበረሰቡ በአካላዊ እንቅስቃሴ፣ በዘፈን፣ በእምነት፣ በተረትና ምሳሌ፣ በአፈ ታሪክ፣ በቁሳዊ መሳሪዎች እና በማህበረሰብ ህግ አብሮት የኖረ ነው፡፡ ግብርና ለገበሬው በሕይወት ከመቆየት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡
ገበሬው አካባቢውን የሚረዳው በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የዝናብ ዑደትን፣ የሰብል ዝርያንና የመዝሪያ ጊዜያቸውን የሚለየው በባህላዊ ዕውቀት ነው፡፡ ይህ ባህለዊ ዕውቀት ለዘመናት የተለማመዱት ስለሆነ መደበኛ አሠራራቸው ሆኗል፡፡ እያደገ ሲሄድም ባህላዊ ህግ ሆኗል፡፡
በባህላዊ የግብርና ዕውቀት ከሌሎች ባህላዊ ዕውቀቶች የተለየ ባህሪ እንዳለው የዶክተር ሰዋገኝ ጥናት ያሳያል፡፡ ይሄውም እንደግለሰቡ አስተሳሰብና የፈጠራ አቅም ሊለያይ ይችላል፡፡ እንኳን ከአካባቢ አካባቢ ከግለሰብ ግለሰብም ሊለያይ ይችላል፡፡ የዶክተሩን ጥናት እውነት የሚያደርግለን የገበሬዎችን ባህሪ ማየት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ ዘር የማብዛት ባህሪ አለው፤ አንዳንዱ ደግሞ ዘር የማሳሳት ባህሪ አለው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ምክንያት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ዘር የሚያበዙ ሰዎች ሰብሉ የዝናብ እጥረትን የመቋቋም አቅም እንዲኖረው፣ ለአረም ተጋላጭ እንዳይሆን ያደርገዋል ሲሉ ዘር የሚያሳሱት ደግሞ ሰብሉ ይፋፋል(ይወፍራል) ፍሬያማ ይሆናል የሚሉ ምክያቶችን ያቀርባሉ፡፡ በሰብል ዓይነት እንኳን አንዳንዱ ለጥቁር መሬት ይሄ ነው ሲል ሌላው ደግሞ አይ ለጥቁር መሬትማ ይሄኛው ሰብል ነው ይባባላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ውጤቱን የሚለኩት በሚገኘው ምርት ነው፡፡
አርሶአደሩ ባህላዊ ግብርናን የሚመርጥበት ምክንያት በቀላሉ መጠቀም ስለሚያስችለው ነው፡፡ በራሱ ባህል፣ በራሱ ቋንቋና በራሱ እውቀት መጠቀም ስለሚያስችለው ነው፡፡
ባህላዊ የግብርና ዕውቀትን በውርስ የሚገኝ እና በልምድ የሚዳብር ሲሉ ዶክተር ሰዋገኝ በሁለት ይከፍሉታል፡፡ በውርስ የሚገኘው ማህበረሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ እሴቶች በጋራ የሚጠቀመው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ደቦ፣ ወንፈል የመሳሰሉት ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ባህላዊ እሴቶች ናቸው፡፡ በሰብል ምርት ስብሰባ ጊዜም ይሁን በሌላ የግብርና ሥራ ላይ የሚጠቀሟቸው የስነ ቃል ዘፈኖችም ሆነ የአውድማ ላይ ስነ ሥርዓቶች በማህበረሰቡ ሲወራረሱ የመጡ ናቸው፡፡ የሚጠቀሙት የግብርና መሳሪያ ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚዘሩበት ወቅት ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰኔ ላይ እህል ሲዘሩ የትኛውንም ሳይንሳዊ የአየር ትንበያ ተጠቅመው አይደለም፡፡ ሰኔ የክረምት ወር መግቢያ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዝናብ ሳይጥል አድሮ እንኳን ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ይጥላል በሚል መተማመን ዘር ይዘራሉ፡፡ ባህላዊ ማዳበሪያ(ፍግ) መጠቀም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል ነው፡፡ ለጤናአዳምና አሪቲን የመሳሰሉ የጓሮ አትክልት አመድን መጠቀም በባህል የጋራ ባህል ነው፡፡ የጋራ ባህል መሆኑ የሚታወቀው አመዱ አትክልቱን ቢያደርቅ እንኳን በሌላ ምክንያት እንደደረቀ እንጂ አመዱ እንዳደረቀው አይታመንም፡፡ ይህን የሚያደርግ ገበሬ ከማን ነው የተማርከው ቢባል ከአባቴ ከወንድሜ... እያለ ነው የሚመልሰው፡፡
አጥኚው ዶክተር ሰዋገኝ በውርስ የመጣው ባህላዊ እውቀት ቢሆንም የቡድን ባህሪ እና የግለሰብ ባህሪ ሊኖረው እንደሚችል ያብራራሉ፡፡ የቡድን ባህሪ ማለት ደግሞ በጋራ የሚሠሩ ማለት ሳይሆን የጋራ ባህሪ የሚጋሩ ማለት ነው፡፡ የግብርና መሳሪያዎችን የመጠቀም፣ የመሥራትና ሌሎች የአሠራር ዘዴዎች ላይ የጋራ ባህሪ ያላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ የሞፈርና ቀንበር አበሳስ፣ የምራን አቀዳደድ፣ የተለያዩ ዕቃዎችን አገጣጠም የጋራ ባህሪ ያላቸው ብዙ ገበሬዎች ሲኖሩ ሌላኛውን አሠራር የሚይዙ ደግሞ ሌላ ቡድን ይኖራል፡፡
ግብርና በበዓላት ቀን አይሠራም፤ ይህም የአንድ አካባቢ የጋራ ባህል ነው፡፡ አንድ ሰው መሥራት ቢፈልግ እንኳን አካባቢውን በመፍራት ይተወዋል፡፡ ሲሠራ ቢገኝም ይጠየቃል፡፡ በበዓላት ቀን መሥራት ከፈጣሪ ቁጣን ያመጣብናል ተብሎ ይፈራል፡፡ ሰብሉ በበረዶ ሊመታ ይችላል(የክፉን ጎረቤት መብረቅ ይመታዋል የተባለውም ከዚህ ሳይሆን አይቀርም)፡፡ ድንበር መግፋት ከህግ በላይ በእምነት በጣም ይፈራል፡፡ በራሱም ሆነ በልጆቹ ቁጣ እንደሚወርድበት ያስባል፡፡ እንዲያውም አንድ ልማድ አላቸው፡፡ አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍና የቀብር ጉድጓድ ሲቆፈር ጉድጓዱ ካስቸገረ ‹‹ድንበር ይገፋ ነበር እንዴ!›› የሚል ሀሜት ይነሳል፡፡ ይሄ ማለት ድንበር የሚገፋ ሰው በመንግስተ ሰማያትም ኃጢአተኛ ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡
የግለሰብ ባህሪ የሚሆነው ግለሰቡ በራሱ ፈጠራ ለየት ያለ አሠራር ሲያመጣ ነው፡፡ ይሄ አሠራር ነው የፈጠራ የግብርና እውቀትን የሚፈጥረው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባህል በራሱ ሊጥሰው ይችላል፡፡ ለምሳሌ እንደ አርቲና ጤናአዳም የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች ላይ አመድ ይደረጋል፡፡ አትክልቱ ቢደርቅ አመዱ ነው ያደረቀው ብሎ መመራመር ይጀምራል፡፡ ውጤቱን ካየ በኋላ አመድ ለማዳበሪያነት እንደማያገለግል ያረጋግጣል ማለት ነው፡፡
ተባይንና ሌሎች ሰብል የሚበሉ ነፍሳትን ለመከላከልም የራሱን ፈጠራ የሚጠቀም አለ፡፡ ለምሳሌ በቆሎን ከነቀዝ ለመከላከል አረቂ የሚቀባ ገበሬ አለ፡፡ ከተሳካለት ይህን አሠራር ለሌሎች ጓደኞቹ ይናገርና ሌሎችም መጠቀም ይጀምራሉ፡፡ ገበሬው ይህን ሲያደርግ ዝም ብሎ በደመነፍስ አይደለም፤ የሚያመጣውን ውጤት ይለካል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ ከሳይንሳዊው አሠራር ጋር አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ በማዳበሪያ የተዘራ ጤፍ ቁመቱ ብቻ አድጎ ፍሬው ካላማረ በሚቀጥለው ዓመት አይጠቀምም፡፡ የምርቱን ብቻ ሳይሆን በተጋጋረ እንጀራ ላይ እንኳን የሚኖረውን ልዩነት ያጤናል፡፡ መዲሃኒት የተረጨበትን ጤፍ እና በእጅ የታረመን ጤፍ የምርቱን ልዩነት ያስተውላል፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ ልብ ማለት ያለብን ነገር ለሳይንሳዊ የግብርና ግብዓቶች አዲስ ከመሆናቸው የተነሳ የአጠቃቀም ክፍተትም ይፈጠራል፤ ያም ሆኖ ግን እህሉ የወዝ ልዩነት እንደሚኖረው አይስቱትም፡፡
ይህ ባህላዊ አሠራር ነው እንግዲህ እያደገ መጥቶ የሳይንስ ዕድገት ላይ የደረሰው፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ በሳይንሳዊ አሠራር ጊዜና ጉልበትን መቆጠብ ተችሏል፤ ከፍተኛ ምርት ማምረትም ተችሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ባህላዊ አሠራሩ ከፍተኛ መሰረት ነው፡፡ ዛሬም እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ ምናልባትም ራሳቸው ገበሬዎች እንደሚሉት የአረም መዲሃኒት ከተረጨበት ሰብል ይልቅ በእጅ የታረመው የተሻለ ማዕድን ይኖረው ይሆናል፡፡ የሚወስደው ጊዜና ጉልበት ከፍተኛ እንደሆነ ቢታወቅም ለእነርሱ ደግሞ የምርት ጥራት አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ የግብርና ሥራ የአገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራልና ባህላዊ የግብርና አሠራርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment