Translate/ተርጉም

Wednesday, November 7, 2018

የጌዴኦ ሸማ


ጌዴኦ ሸማ
ጌትነት ተስፋማርያም
ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ከእንስሳት ቆዳ እና ከተክል ቅጠሎች የተሠሩ ልብሶችን ያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከዚያም ስልጣኔ ሲመጣ ደግሞ የሃር ፈትል ተጠቅመው ደርባባ ልብሶችን ለንጉሣውያን ቤተሰብ ያዘጋጁ የነበሩ የእደጥበብ ባለሙያዎች ነበሩ። በድንቅ ጥበብ የተሠሩ እጀ ጠባቦች፣ ቡልኮና ካባዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ይዘጋጁ ነበር። ለዚህ ደግሞ በኦሮሚያ የወለጋ ሙዚየምን ሲጎበኙ የንጉሥ ኩምሳ ሞረዳን አልባሳት፤ በጎንደር የንጉሣውያኑን ልብሶች፤ በጅማ የአባጅፋርን እና የነዋሪዎችን አለባበስ አሻራዎች፤ በደቡብ ደግሞ የጋሞዎችን ጥንታዊ ሙዚየምን መመልከት በቂ ማስረጃ ይሆናል።
የኋላ ኋላ የአገራዊው አለባበስ በምዕራባውያኑ ሱፍ እና ካፖርት መቀየሩ ደግሞ የኢትዮጵያውያን አለባበስ ባህል ላይ ሌላ ምዕራፍ እንደከፈተ ይታመናል። የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ ከማጠናከራቸው ጋር ተያይዞ እንደ ሱፍ እና ሌሎች የስፌት ልብሶች የመተዋወቃቸው ጉዳይ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ታሪክ አለው። አሁን ላይ ወደሥራ ሲሄዱ በመንገድ ላይ ከሚያገኙት ሰው በግምት 90 በመቶው ከባህላዊ ውጪ በሆኑ አልባሳት እንደሚጠቀም መታዘብ ይቻላል።
በፋሽኑ ኢንዱስትሪ ወደቀደመው ባህላዊ ልብሶች ላይ ተመርኩዞ ነጮችን የሚያስደንቅ ዲዛይን የመሥራት አካሄድ እየተለመደ ነው። ወትሮም የእራስ ቢያስከብር እንጂ እንደማያዋርድ የተገነዘቡ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር ታዋቂ ያደረጋቸውን የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ አልባሳት በዘመናዊ መልክ በማቅረብ ላይ ናቸው። ህብረተሰቡ ግን ባህላዊ አልባሳቱ በበዓላት ወቅት እና ለልዩ ዝግጅት ካልሆነ በቀር እምብዛም ጥቅም ላይ ሲያውለው አይታይም።
እዚህ ላይ የጃፓናውያንን ተሞክሮ ማንሳት ይገባል። ሩቅ ምሥራቆቹ ስለእራሳቸው ሲናገሩ «አንድ ጃፓናዊ እስከ ሠላሳ ዓመት ዕድሜው ድረስ የአውሮፓን ባህል እና አለባበስ እንዲሁም ሙዚቃዎች ላይ ይንጠለጠላል። ከሠላሳ ዓመቱ ሲያልፍ ግን የአገሩን ባህል መያዙ አይቀርም» የሚል አባባል አላቸው። ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በሙዚቃው ረገድ እንደጃፓናውያኑ የአውሮፓ እና አሜሪካን ቢመኙም ዕድሜያቸው ሲጨምር ግን የአገር ውስጥ ሙዚቃዎች ላይ ትኩረት የማድረግ ዝንባሌ እንዳላቸው ይስተዋላል። ይህ ልምድ አለባበሱ ላይም ቢደገም አያሌ የዕደጥበብ ውጤቶችን ወደገቢ መለወጥ ብቻ ሳይሆን ባህሉን የጠበቀ ትውልድ ማፍራት ያስችላል።
ኢትዮጵያ የባህላዊ ልብሶች እና እደጥበብ ውጤቶች ሀብታም ናት። ምክንያቱም በአራቱም ማዕዘናት ቢሄዱ የየእራሱ ቀለም ያለው ባህላዊ ልብስ የለበሰ ማህበረሰብ አይታጣም። እኛም ወደ ጌዴኦ በአቀናንበት ወቅት ያስተዋልነውን የጌዴኦዎችን ጥንታዊ አለባበስ ጥበብ ልናስቃኛችሁ ወደናል። በጌዴኦዎች የአለባበስ ስርዓት መጠበቅ በታላላቆች ዘንድ አንቱታን ያስገኛል። የአለባበስ ስርዓት ተብሎም ለሕፃናት ለወጣቶች እና ለአዛውንቶች የእየራሳቸው ምርጫ አላቸው።
የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ቅርስ ጥናትና እንክብካቤ ባለሙያ አቶ አበራ ኢያሱ እንደሚገልጹት፤ የጥንታዊ ጌዴኦ የአለባበስ ዓይነቶች ከሰባት በላይ ናቸው። «ሩፋ»«ሂቶ ሃፋሬ»«ፋሎ» የተባሉ የልብስ ዓይነቶች በተለያየ ቅርጽ ከሕፃን እስከ አዋቂ ይለብሷቸዋል። እያንዳንዳቸውንም በተመለከተ ምን ዓይነት ልዩነት አላቸው የሚለውን ባለሙያው ያስረዳሉ።
ሩፋ እና ሂቶ
«ሩፋ» መጎናጸፊያ ወይም ረዘም ያለ ሻሽ መሰል ከጥጥ ፈትል የሚሠራ የልብስ ዓይነት ነው። ልብሱ የጌዴኦ አባገዳዎች ስለመሪነታቸው በሚያደርጉት «ካላቻ» ለተሰኘ ምልክት ስር ይውላል። በአባገዳ ጭንቅላት እንደጥምጣም ይታሰራል። «ሂቶ» ደግሞ በጌዴኦ የገዳ ስርዓት «ባሌ ገዳ» የተባለው እርከን ላይ የደረሱ ሰዎች ሀብታም እና ጀግና ከሆኑ በወገባቸው ዙሪያ የሚታጠቁት መቀነት ነው። የመቀነት ጨርቁ በሽመና ጥበብ ከጥጥ ይሠራል። አንድ «ሂቶ» የታጠቀ ሰው የሚከበር ከመሆኑም ባለፈ ለማህበረሰቡም ሆነ ለአገሩ አንድ አስተዋጽኦ ያበረከተ ጀግና መሆኑ ሳይናገር ይለያል። «ሂቶ» ታጥቆ በአስተዳደር ጥሪዎች ላይ፣ በሠርግ እና ዘን ቦታዎች የተገኘ ሰው ከሚሰጠው ክብር የተነሳ ልዩ ቦታ ሊዘጋጅለት ይችላል።
ሃፋሬ
ወንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ በመጀመሪያ ቆዳው የሚያገኘው በአገሬው አጠራር «ጡቡቆ» የተሰኘውን ጨርቅ ነው። ከዚያ ግን ሰው ነው እንደአዕምሮው ሁሉ ሰውነቱም እያደገ ሲሄድ ሃፍረተ ሥጋውን ለመሸፈን ተብሎ ቁምጣ መሰል ልብስ ይዘጋጅለታል። ይህ ቁምጣ መሰል ሰፋ ያለ ልብስ ነው «ሃፋሬ» የሚባለው። በአብዛኛው ጊዜ የሃፋሬን ጥሬ ዕቃ በቤት ውስጥ የሚያዘጋጁት እናቶች ናቸው። ጥጥ ፈትለው እና አደውረው ያቀርባሉ። ከዚያም ሸማ ሠሪው ባለአንድ ፈርጅ ቡልኮ አድርጎ ሃፋሬውን ያዘጋጃል። ሃፋሬ በብዛት እስከ ዘጠኝ እና አስር ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት በዕለት ተዕለት ጊዜያቸው ይለብሱታል። ለጨዋታ የሚመች እና ሕፃናቱ እንደፈለጉ እንዲዘሉ የሚረዳ በመሆኑ ለልጅ ሰውነት ይመቻል። ሲቆሽሽም በቀላሉ ለማጠብ የሚመች በመሆኑ እና ለመሥራትም ብዙ ጊዜ ስለማይወስድ ለአንድ ልጅ ሁለት እና ሦስት ሃፋሬ ሊሠራ ይችላል።
ፈሎ
ሌላው የጌዴኦዎች ባህላዊ ልብስ የሆነው በአንድ መንደር ውስጥ በበርካታ ሰዎች የሚለበሰው የወጣቶች ልብስ የሆነው «» ነው። ፈሎ አንዳንዶች «ፌሎ» እያሉ ይጠሩታል። «ፈሎ» በብዛት ወደጉርምስና የዕድሜ ክልል በገቡ ወጣቶች ዘንድ ይዘወተራል። ወደጎን በተዘረጋ ባለዘርፍ ንድፍ ያለው ሆኖ በርካታ መስመሮች እና በተለያዩ ቀለሞች ያጌጠ ነው። ይህን ልብስ በንጽህና የለበሰ ጎረምሳ የሚወዳትን ኮረዳ ለመሳብ ሊጠቀምበት ይችላል። በአካባቢው ባህል ያማረ «ፈሎ» ለብሶ በኮረዶች ፊት የሚንጎራደድ ወጣት የትዳር አቻውን ለማግኘት ያለው ዕድል ይጨምራል። ምክንያቱም ሴቶቹ ፈሎ ያማረበትን ወጣት ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ልብሱን በጥንቃቄ አሠርቶ ወይም እራሱ አበጃጅቶ የማይለብስ ወጣት እንደሰነፍ ስለሚታይ እና በኮረዶች ዘንድም ስለሚናቅ «ፈሎ» ለወጣቶች እንደክብር ልብስ ይታያል። ልብሱ የሚያውድ ጠረን እንዲኖረው ደግሞ ወጣቶቹ የተለያዩ ተክሎችን ያጥኑታል። ወይራ፣ ቡካራ የተባለ ተክል እና ጽድን በመቀባት እና በማጠን ልብሱ መልካም ጠረን እንዲኖረው ይደረጋል። የዚህን ጊዜ «የእገሌ ፈሎ ጠረኑ ከሩቅ የሚጣራ ነው» እየተባለ በኮረዶች ዘንድ ይወደሳል።
«ቆሎ» ጥንት በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ታዋቂና እጅግ ተወዳጅ የነበረ፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሚመርጡት ልብስ ነው። ቆሎ በእጅ የሚሠራ ሲሆን ከወገብ በላይ የሚለበስ በመሆኑ እንደሸሚዝ ያገለግላል። የተለያየ ቀለም ያላቸው ድርና ማግ የተዋሃዱበት የጥበብ ውጤት ስለሆነ የዲዛይን ውበቱ የውጭ ዜጎችንም ቀልብ ይስባል። ልብሱ በጌዴኦዎች ዘንድ እንደ ብሔሩ ባህላዊ ልብሶች ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ከዘመናዊ ሱሪ እና ቀሚስ ጋር አጣምረው የሚለብሱ ወጣቶች ለሥራ የማይከብድ እና ጥሩ ዲዛይን ያለው መሆኑን ይመሰክሩለታል።
ጲሶ
ይህ የባህላዊ ልብስ በተለየ መልኩ እናቶች በቅቤ አርሰው ከስር ሌላ ጨርቅ አድርገው ነው የሚለብሱት። በድር እና ማግ ቢሠራም በጥልፍ ደግሞ የተለያየ ማስዋቢያ ይደረግበታል። አሠራሩም አንድ ወጥ ልብስ ከተዘጋጀ በኋላ መሃል ለመሃል ይታጠፍና ለአንገት ማስገቢያ እንዲሆን በእጥፋቱ አጋማሽ ላይ በክብ ይቀደዳል። አንገት ማስገቢያው በጥልፍ በክብ ቅርጽ ይዋብና ዙሪያውን ዛጎል ይደረግበታል። ከእጅ ማስገቢያዎቹ በታች ሰፋና ወገብ ላይ ሰፋ እንዲል ተደርጎ ይሠራል። ከታች በኩል ደግሞ ዘርፍ እንዲኖረው ጥለቶቹ ቋጠራሉ ወይንም ሌላ ዛጎል መሰል ነገር ይታሰርለታል። ጲሶ ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አይለበስም። አስፈላጊ ሲሆን ሴቶች ለማጌጥ የሚመርጡት የክት ልብስ ነው።
ኤጃ
ይህ የባህላዊ ልብስ ባለ አራት ፈርጅ ቅርጽ ያለው ቡልኮ ነው። በየፈርጆቹ ዳር ላይ «ጥቅር» ወይም ቀይ ጥለት፤ ወይም ዘርፍም አለው። ኤጃን አዛውንቶች፣ ያገቡ እና ሀብታም ሰዎች ይለብሱታል። ልብሱ ስፌት የሌለው እና ሲፈለግ የሚወለቅ ሲያስፈልግ ደግሞ ለመልበስ የማያስቸግር አሠራር አለው። ከውፍረቱ የተነሳ ሙቀት የሚሰጥ በመሆኑ በሌሊት እንደብርድ ልብስ ሊያገለግል ይችላል። በተጨማሪ እንደ «ኤጃ» ሁሉ ወፍራም ባይሆንም «ዱዳ» የሚባል ሳሳ ያሉ ቡልኮች ጌዴኦዎች አላቸው። ከኤጃ ጋር ተመሳሳይ አሠራር ያለው ቢሆንም ነገር ግን ነጠላ ቡልኮ ነው። «ኤጃ»ን ለማሠራት ወይም ለመግዛት አቅም የሌላቸው ሰዎች «ዱዳ» የተሰኘውን ቡልኮ ይመርጣሉ።
በጌዴኦ የሽመና ሙያ የተከበረ ነው ጥልፍ መጥለፍ እና የቤተሰቦቿን ልብሶች ማስዋብ የምትችል ሴት ትወደዳለች። ነገር ግን የቻይና ሱሪዎች እና ጨርቆች ያልገቡበት የኢትዮጵያ አካባቢ የለም በሚያስብል ሁኔታ በጌዴኦ ገጠራማ አካባቢዎችም ባህላዊ ልብሶችን እየተኩ ይገኛሉ። ይሁንና ባህላዊ ልብሶቹን በዘመናዊ አሠራር በማዘጋጀት ባህልና ወግን የጠበቀ አለባበስ መለመድ ይገባዋል። የባህልና ቱሪዝም ሰዎች እንዲሁም መምህራንና የአስተዳደር ሰዎች ባህላዊ ልብሶቹን በመጠቀም የዕደጥበብ ባለሙያዎችን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ ሊመክሩ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ታሪክ እና ትውፊትንም ጠብቆ ለመሄድ ባህላዊ አልባሳቱ መረሳት እንደሌለባቸው ይበልጥ ሊሠሩ ይገባል መልዕክታችን ነው!

No comments:

Post a Comment