የተሳሳተ
አስተሳሰብን ማረቅ
ዳግም
ከበደ
ሠላም
ልጆች እንዴት ሰንብታችኋል?
በዚህ ሳምንት
በድጋሚ መጥቻለሁ። ይህ ወር ለእናንተ ታዳጊዎች
ትምህርቱ ተጋግሎ የሚቀጥልበት እና ከክረምቱ
እረፍት ተመልሳችሁ በሙሉ ልብ እውቀትን
ከመምህሮቻችሁ የምትገበዩበት ነው። ይሄን
ያልኳችሁ የጥቅምት ወር ልክ እንደ መስከረም
በዓላት እና የአዲስ ዓመት የእረፍት ቀናት
የማይበዛበት ስለሆነ ነው።
ሆኖም
ግን ልጆች ወሩን ታሪካዊ የሚያደርግ እና
ጥቅምት በመጣ ቁጥር ትውስታን የሚያጭር
ክስተቶችን አስተናግዷል። ለምሣሌ ያክል
የኢትዮጵያ ንጉሥ አፄ ምኒልክ በእንጦጦ
«መንበረ
ፀሐይ ቅድስት ማርያም»
ቤተ ክርስቲያን
ውስጥ በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዓ
መንግሥት ተቀብተው፣ ዳግማዊ ምኒልክ ተብለው
የንጉሠ ነገሥት ዘውድ የጫኑት በዚሁ የጥቅምት
ወር ነው። ታዲያ የታሪክ ምሁራን እና ታላላቅ
አባቶች ይህን ወር የሚያስታውሱበት ክስተት
አላቸው ማለት ነው።
ከላይ
የጠቀስኩላችሁን እውነት በመጽሐፍት ላይ
ከማንበቤ በፊት አያቴ ነበረች የነገረችኝ።
የታሪክ መጽሐፍትን ሳገላብጥ ደግሞ ይበልጥ
ስለ ጥቅምት ወር እና ስለ ንጉሠ ነገሥት አፄ
ምኒሊክ በስፋት ለማወቅ ቻልኩ። እንደምታውቁት
አያቴ በርካታ አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ ታሪክ
ቀመስ ክስተቶችን እንዲሁም ተረቶችን ታወጋኛለች።
እኔም አያቴ ከመጽሐፍት የበለጠ ታሪክን
የምታስተምረኝ፣ የምትመክረኝ እና በጎውን
መንገድ ሁሉ የምታሳየኝ እንደሆነች ነው
የማስበው። ለዛም ነው የነገረችኝን በርካታ
ታሪኮች የማልረሳቸው።
ልጆች
ዛሬም እንደተለመደው ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ
ተሰምቶ የማይጠገበውን፤ ተነግሮ የማያልቀውን
የአያቴን ታሪኮች ላጫውታችሁ ነው። እናንተም
መቼም እጅግ አዝናኝ እና ቁምነገር አዘል
የሆኑትን ታሪኮች ለማንበብ ጓጉታችኋል።
ለመሆኑ በዚህ ሳምንት ምን አይነት ታሪክ
የማጫውታችሁ ይመስላችኋል?
መልካም!
ዛሬ አስተሳሰብ
ላይ የሚያተኩር ልዩ ታሪክ ነው የምነግራችሁ።
አያቴ
እንደተለመደው ከቤተክርስቲያን መልስ በረንዳዋ
ላይ ቁጭ ብላ የጠዋት ፀሐይ ትሞቃለች። እኔና
እናቴም አብረናት በረንዳው ላይ ተቀምጠናል።
አያቴ ከእናቴ ጋር አንዳንድ ጉዳዮች ላይ
እየተጨዋወቱ ነበር። በመሃል ግን ወሪያቸውን
አቆሙና በመካከላቸው ዝምታ ሰፈነ። በድንገት
ግን እናቴ አንድ ጥያቄ ጠየቀችኝ።
«ልጄ
የፈተና ውጤቶችህን አየኋቸው። በሂሳብ እና
እንግሊዘኛ ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ነው
ያመጣህው ምንድነው ምክንያቱ»
ስትለኝ። እኔም
«እናቴ
እነዚህ ትምህርቶች ይከብዱኛል ወደፊትም
በቶሎ የሚገቡኝ አይመስለኝም። እኔ ሁሌም
በነዚህ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት ማምጣት አልችልም»
አልኳት። እናቴ
በምላሼ ደስተኛ አልሆነችም። ጠንከር ብላም
እንዳጠና ተቆጣችኝ። በዚህ መሃል አያቴ
ወሬያችንን ታዳምጥ ስለነበር ለእናቴ የሰጠኋት
መልስ ትክክል አለመሆኑን በእርጋታ ነግራኝ
አንድ ታሪክ አጫወተችኝ። የአያቴ አስተማሪ
ወግም በጣም ነበር የጠቀመኝ። ይህ ታሪክ
እንዲህ የሚል ነበር።
ከዘመናት
በፊት የአንድ ጥንታዊ መንደር ነዋሪ የሆነ
አብርሃም የሚባል ሰው ነበር። ይህ ሰው ጠንካራ
ሠራተኛ እንዲሁም አስተዋይ ነበር። ሁሌም
በሳምንቱ ውስጥ ያሉ የሥራ ቀናቱን በግብርና
ሥራ ላይ የሚያውል። እራሱን እና ቤተሰቡን
በደስታ የሚያኖርም ነበር። ሁሌም በሳምንቱ
የመጨረሻ ቀን ደግሞ ቤተሰቡን በተለያዩ ቦታዎች
እየወሰደ ያዝናናል።
አብርሃም
ከዕለታት በአንዱ ቀን እንደተለመደው ቤተሰቡን
ወደሚያዝናናበት ስፍራ ይዟቸው ይሄዳል።
የመረጠው ስፍራም የሰርከስ ትርኢት የሚታይበት
ትልቅ የመዝናኛ ቦታ ነበር። በዚህ ስፍራ
በርካታ ትእይንቶች ይታዩ ነበር። ሁለቱ ልጆቹ
እዚህ ቦታ ሲመጡ ምርጫቸው የሚያደርጉት
መንሸራተቻ እና ልዩ ልዩ መጫወቻ ያላቸው
ቦታዎችን ነው። ባለቤቱ ደግሞ ሰዎች ዘፈን
እና ዳንስ የሚያሳዩበትን ቦታ ትመርጣለች።
እርሱ ደግሞ የእንስሳትን ትርኢት መመልከት
ያስደስተዋል። እናም በዚህ ቀን ሁሉም
እንደምርጫቸው ወደሚያስደስታቸው ስፍራ ሄደው
መዝናናት ጀመሩ። የሁሉም ምርጫ ግን አንድ
ቦታ ላይ ስለነበር አልተቸገሩም ነበር።
አብርሃም
እንደሁል ጊዜው የእንስሳ ትርኢት የሚታይበት
ስፍራ ሲደርስ ሁለት ልዩ እንስሳትን አስተዋለ።
እነዚህ እንስሳት ዝሆኖች ነበሩ። ከዚህ ቀደም
በዚህ ሰርከስ ስፍራ ዝሆኖች አልነበሩም።
እነሱን በተመለከተ ጊዜ በጣም ተደሰተ። እና
ወደ ቆሙበት የማቆያ ስፍራ ሊመለከታቸው ተጠጋ።
ወደ
ዝሆኖቹ በቀረበ ጊዜ ግን አንድ አስገራሚ ነገር
አስተዋለ። ሁለቱም ዝሆኖች ፊታቸውን አዙረው
በተለያየ ገመድ ትናንሽ እንጨት ላይ አንገታቸው
ታስሮ ተመለከተ። ሁኔታው በጣም አስገረመው።
ምክንያቱም ዝሆኖቹ በጣም ግዙፍ ከመሆናቸው
የተነሳ የታሰሩበትን ገመድ በጥሰው ወደ
ፈለጉብት ስፍራ መሄድ ይችሉ ነበር። ነገር
ግን ይህን ቀጭን ገመድ እና ቀጭን እንጨት
ምንም ሳያደርጉት ለማምለጥም ሙከራ ሳያደርጉ
አሳዳጊያቸው ባስቀመጣቸው ስፍራ ላይ ቆመው
የሚያሳዩትን ትርኢት በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
በዚህ ጊዜ አብርሃም የተመለከተው ነገር እጅግ
አስገርሞት ስለነበር ምክንያቱ ምን ሊሆን
እንደሚችል ለማረጋገጥ ከውሣኔ ላይ ይደርሳል።
አብርሃም
ከዝሆኖቹ ትንሽ ራቅ ብሎ አንድ የእንስሳት
አሰልጣኝ የሆነ ሰው ተመለከተ። በአዕምሮው
ሲያብሰለስለው የነበረውን ጥያቄ ለዚህ ሰው
ነግሮ ምላሽ ለማግኘት ፈለገ። «አንተ
ሰው እነዚህ ዝሆኖች የታሰሩበት ገመድ በጣም
ቀጫጭን እና እንጨቱም ቶሎ ሊሰበር የሚችል
ነው። ነገር ግን አንድ ቦታ ቆመዋል። ሊያመልጡም
አይሞክሩም። ምክንያቱ ምንድነው?»
በማለት
ያስገረመውን ጥያቄ ነገረው።
ሰውየውም
ፈገግ ብሎ እንዲህ አለው «ምን
መሰለህ ወዳጄ እነዚህን ዝሆኖች ያሳደግናቸው
ከህፃንነታቸው ጀምሮ ነው። በጣም ትንንሽ
በነበሩበት ወቅት እንዳያመልጡ እና በየቦታው
እየሄዱ እንዳያስቸግሩ በሚል እናስራቸው
ነበር። ያን ጊዜ ስናስራቸው አሁን እንደምንጠቀመው
አይነት ተመሳሳይ ገመድ እና እንጨት ነበር»
ሲል ነገረው።
እያደጉ ሲመጡም ይህንን ማሰሪያ ለመዱት በማለት
አስረዳው። ልጅ እያሉ ሊበጥሱት ባይችሉም
አሁን ግን አቅሙ አላቸው። ነገር ግን ከልጅነታቸው
ጀምሮ ገመዱን መበጠስ እንደማይችሉ እያሰቡ
ስላደጉ አሁንም ይህንኑ ነው የሚያደርጉት
እያለ አስገራሚውን ታሪክ አጫወተው።
አብርሃም
የእንስሳት አሰልጣኙ በነገረው ነገር እጅግ
ተገረመ። ዝሆኖቹ የታሰሩበትን ገመድ መበጠስ
ይችላሉ ነገር ግን ከልጅነታቸው ጀምሮ እራሳቸውን
እያሳመኑት በመምጣታቸው አሁን ይህን ማድረግ
አይችሉም። ከዚህ ሁኔታ በርካታ ነገር መማር
እንደሚቻል ተገነዘበ። ዝሆኖቹ አንድ ጊዜ
እራሳቸውን አሳመኑ እንጂ በድጋሚ ምንም
አልሞከሩም። በዚህ ምክንያት እስካሁን ድረስ
በተመሳሳይ ማሰሪያ ሊታሰሩ ችለዋል። ስለዚህ
የሰው ልጅም ቀድሞ የያዘውን አስተሳሰብ
ለመቀየር እና በአዲስ መንገድ ውጤታማ ለመሆን
ከነዚህ ዝሆኖች ጥበባዊ ትምህርት መማር ይችላል
ሲል ድምዳሜ ላይ ደረሰ።
አበርሃም
የእንስሳት አሰልጣኙ ጥያቄውን በተገቢው
መንገድ ስለመለሰለት አመስግኖት በቦታው
የነበረውን ትርኢት ተመልክቶ እና እራሱን
አዝናንቶ ቤተሰቦቹን ወደሚያገኝበት ስፍራ
ተመለሰ። በዚያች ቀን ከተመለከተው ነገር
ትምህርት በመውሰዱ ቤተሰቦቹን ይበልጥ ስኬታማ
እና ደስተኛ ለማድረግ የዝሆኖቹን ታሪክ
ሊነግራቸው ወሰነ። ይህ ታሪክ በውስጣቸው
መጥፎ አስተሳሰብና ሳይሞክሩ አልችልም የማለት
ችግር ካለባቸው እንኳን ትክክለኛውን መንገድ
እንደሚያሳያቸው እርግጠኛ ነበር። በዕለቱ
ከቤተሰቡ ጋር ሲቀላቀል ፍፁም ደስተኛ እና
የተረጋጋ ስሜት ይታይበት ነበር።
አያቴ
ከላይ የፃፍኩላችሁን አስተማሪ ታሪክ ደስ
በሚል ሁኔታ ተረከችልኝ። እኔም በታሪኩ ብዙ
ነገር ተማርኩ። ከእናቴ ጋር በምናወራበት
ወቅት የሂሳብ እና እንግሊዘኛ ትምህርት
እንደማይገባኝ እና ወደፊትም እንደማልችል
ጠቅሼ የመለስኩላት መልስ ተገቢ አለመሆኑን
መገንዘብ ቻልኩ።
እርሷንም
ይቅርታ ጠይቄ በውስጤ የነበረውን የተሳሳተ
አመለካከት ማሸነፍ እንደምችል ለራሴ አሳመንኩት።
ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ እና የአጠናን ዘዴዬን
በመቀየርም በትምህርቴ ስኬታማ መሆን ቻልኩ።
ለሆነው ሁሉ አያቴንም አመሰገንኳት። ልጆች
እናንተም ከዚህ ታሪክ ብዙ እንደምትማሩ ተስፋ
አደርጋለሁ። ሳምንት እስከምንገናኝ መልካም
ጊዜ ይሁንላችሁ። ሠላም!
አንዳንድ
እውነታዎች
ዳግም
ከበደ
ዓለማችን
በሚያስደንቁ ተፈጥሯዊና ሳይንሳዊ ነገሮች
የተሞላች ነች። ልጆች በሳይንሳዊ ምርምር
እና የሰው ልጅ በግሉ ሁሉንም የተፈጥሮ፣
የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምስጢሮች መረዳት
አለመቻሉ ምን ያህል ረቂቅ (ጥልቀት
ያለው)
እንደሆነ
የሚያስረዳን ነው። እኛ የሰው ልጆች ደግሞ
ከሁሉም ፍጥረታት ለየት የሚያደርገን ዓለማችን
ላይ ያሉ ልዩ ነገሮችን ለመረዳት በምናደርገው
ጥረት እና ጉጉት ነው።
ታዲያ
የሰው ልጆች ፍላጎትን ተመስርተን አመቺ በሆነ
አጋጣሚ ሁሉ ለእናንተ በዚህ ገጽ ላይ ስለ
አንዳንድ እውነታዎች እንነግራችኋለን። ለዛሬ
«በቴክኖሎጂ
ምርምር ስለተገኘው ኢንተርኔት»
የተመለከተ
እውነታ መረጃዎችን እንንገራችሁ።
አሁን
አሁን የየዕለት ሥራችን ከኢንተርኔት ውጭ
ለማከናወን ማሰብ ከባድ እየሆነ መጥቷል።
ለሥራም ይሁን ለመዝናኛ አልያም ወቅታዊ
መረጃዎችን ከዓለም ዙሪያ ለመቃኘት ኢንተርኔት
ሁነኛው ድልድይ
መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን 10 የኢንተርኔት እውነታዎችን ደግሞ የበለጠ ስለ ቴክኖሎጂው ያስረዱናል።
መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን 10 የኢንተርኔት እውነታዎችን ደግሞ የበለጠ ስለ ቴክኖሎጂው ያስረዱናል።
- ሦስት ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ ሰው ኢንተርኔት ይጠቀማል። ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮኑ እስያውያን ናቸው። ኢንተርኔት በአንድ ቀን ቢቋረጥ 200 ቢሊዮን የኢሜል መልዕክቶች እና3 ቢሊዮን የጎግል ፍለጋዎች ነገን መጠበቅ ግድ ይላቸዋል ተብሎ ይታሰባል።
- ቻይና የኢንተርኔት ሱሰኞች የሚታከሙበት ክሊኒክ አላት። በቻይና 200 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ዕድሜያቸው በ15 እና 35 ዓመት መካከል ነው። እናም አብዛኞቹ ወጣቶች ራሳቸውን የመቆጣጠር አቅማቸው አናሳ በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤጂንግ በአገሪቱ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ የኢንተርኔት ሱሰኞች መንከባከቢያ ክሊኒክ ተከፍቷል።
- በየቀኑ 30 ሺህ ድረ ገፆች መረጃ እንደሚበረበር ይነገራል። የመረጃ መዝባሪዎች በቀላሉ የሚሰበሩ ድረ ጎፆችን የሚያሳውቁ በጣም ስኬታማ የኮምፒውተር ሶፍትዌር ፕሮግራሞችን ይጠቀማሉ።
- የመጀመሪያው ፊት ለፊት እየተያዩ ማውራት የሚያስችል የድረ ገፅ ካሜራ (ዌብ ካም) የተሠራው በ1991በካም ብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ 128 በ128 የምስል ጥራት የሆኑ ደብዛዛ ምስሎችን ማየት
ያስችላል ነበር። - ኢንተርኔት በደቂቃዎች ውስጥ 240 ሚሊዮን የኢሜል መልዕክቶችን የሚልክ ሲሆን፤ 70 በመቶው ምንጫቸው ያልታወቁ አላስፈላጊ መልዕክቶች ናቸው። አንድ የኢሜል መልዕክት ለማዘጋጀት2 ቢሊዮን ኤሌክትሮኖች ያስፈልጋሉ።
- በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ሥራውን ለመቀጠል 50 ሚሊዮን የፈረስ ጉልበት ያስፈልገዋል። በፈረንጆቹ 2005 የብሮድባንድ ኢንተርኔት ከፍተኛ ፍጥነት በሰከንድ 2 ሜጋ ባይትስ ብቻ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በሰከንድ 100 ሜጋ ባይት የሆኑ ፋይሎችን የሚያወርድ የኢንተርኔት ፍጥነት ያለባቸው አገራት በርካታ ናቸው። ነገር ግን ባለሙያዎች ሳይንስ የመጨረሻ ጣሪያው ላይ እየደረሰ መሆኑንና የፋይበር ኦፕቲኮች ተጨማሪ መረጃዎችን የመያዝ አቅማቸው እየተሟጠጠ ነው በማለት ያስጠነቅቃሉ።
- ለመጀመሪያ ጊዜ «ትዊት የተደረገው» የፅሁፍ መልዕክት የተለጠፈው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 21 2006 ላይ በጃክ ዶርሴይ ነው። ዩቲዩብ ላይ የመጀመሪያው ቪዲዮም «Meet At Zoo» በሚል ርዕስ እሁድ ሚያዝያ 23/ 2005 ጠዋት 2 ሰዓት ከ27 ደቂቃ ላይ ነበር የተጫነው።
- ዘጠኝ ሚሊየን የሚጠጉ ብሪታንያውያን ወጣቶች እና ከጣሊያን ህዝብ ሲሶ የሚሆኑት ኢንተርኔት ተጠቅመው እንደማያውቁ ይነገራል።
- አብዛኛው የኢንተርኔት መጨናነቅ የሚከሰተው በሰዎች ሳይሆን የተለያዩ ተግባራትን በሚያከናውኑ ሶፍትዌሮች እና ቫይረሶች ነው። በቅርቡ በኢንካፕሱላ የተደረገ ጥናትም 61 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው የድረ ጎፆች መጨናነቅ የሚፈጠረው በሶፍትዌር አፕሊኬሽኖች የተነሳ መሆኑ ተረጋግጧል።
ምንጭ፦
ፎስ ባይት የተባለ ድረ ገጽን ተጠቅመናል
ተፅኖ
ፈጣሪ ሰዎች
ዳግም
ከበደ
ልጆች
እንዴት ናችሁ?
በዚህኛው
አምድ ላይ ታዋቂ ፈላስፋዎችን፣ ፖለቲከኞች
እና የአገር መሪዎች ሳይንቲስቶችን እና ለዓለም
ስልጣኔ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ ሰዎችን
እናስተዋውቃችኋለን።
እስቲ ልጆች የዓለም ስልጣኔ እዚህ እንዲደርስ
ትልቅ ድርሻ አላቸው የምትሏቸውና
ከዚህ ቀደም እናንተ ከምታውቋቸው ሰዎች መካከል
ጥቂቶቹን አስታውሱ። ሊደነቁ ይገባል አይደል?
መልካም
ልጆች ሁሉም ሰው በዕኩል ደረጃ ለዓለም መሰልጠን
እና ዘመናዊ መሆን ድርሻ ባይኖረውም ነገር
ግን የራሱን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል።
አቅማችን
ከተጠቀምንበት አዲስ ነገር ለመሥራት እና
ለመፍጠር እኛ የሰው ልጆች ከሌላው የዓለም
ፍጡር በተለየ መንገድ ልዩ ስጦታ ታድለናል።
ታዲያ እናንተ ምን አሰባችሁ?
አዲስ
እና ጠቃሚ ነገር ለአገራችሁ ብሎም ለዓለም
ህዝብ ለመሥራት ተዘጋጃችሁ?
መልካም
ለዛሬ ጥሩ ምሣሌ እንዲሆናችሁ በአገራችን
ታሪክ በውጭ ዲፕሎማሲ በዘመናቸው የሚደነቅ
ተግባር የሠሩ እንዲሁም አሁን ላይ የመጀመሪያዋ
ሴት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን በቅርቡ
ስለተሾሙት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.
ፕሬዚዳንት
ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥቂት እንንገራችሁ።
- ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ 4 ኛዋ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፈረንሳይ አገር ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል ተከታትለዋል፡፡ ሥራቸውን የጀመሩት ደግሞ በትመህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ በመሆን ነበር።
- በመቀጠልም በውጭ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ሴት አምባሳደር በመሆን ጀቡቲ፣ ሴኔጋል፣ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ አግልገለዋል።
- የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ውስጥም የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን ሠርተዋል፡፡
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሠርተዋል በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ በርካታ ልምድ ያለቸው ሴት እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል።
- አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ከአፍሪካ የመጀመሪያ ሴት ተወካይ ነበሩ። ለብዙ ዘመናትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።
- እ.ኤ.አ በ2011 ደግሞ በወቅቱ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ባን ኪሙን በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሥራ መደብ ሾመዋቸው ለዓመታት አገልግለዋል።
- በቅርቡ ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይነት እያገለገሉ ነበር፤ ከሳምንት በፊት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዚዳንት ሆነው በመሾማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።
No comments:
Post a Comment