ደጋፊና
ገዳፊ
ሊድያ
ተስፋዬ
«ቆይ
ቆይ! እዚህ
ጋር ያዝልኝ...» እትዬ
የሻሽወርቅ ድምጻቸው በድንገት ተሰማ፤ ሳቅ
ሳቅ ሲለው የቆየ የሚመስለው ተሰብሳቢ ዕድሉን
ለመጠቀም ነው መሰለኝ፤ ሳያንገራግር በፍጥነት
ሳቁን ለቀቀው። ስብሰባው ለጥቂት ሰከንዶች
በሳቅ ተቋረጠ። ሰብሳቢዎቹ አዳዲስ የወረዳ
ሹመኞችና ከቀደሙት አመራሮች የተረፉ ርዝራዥ
ዟሪዎች ናቸው፤ በእነርሱ ገጽታ ላይ አንዳችም
ፈገግታ አይታይም፤ እንደውም ቆጣ ብለዋል።
«ጥያቄ
ካለ እጅን አውጥቶ በሥርዓት ነው መጠየቅ እንጂ
እንዲህ ከንግግር መካከል ጣልቃ መግባት ትክክል
አይደለም» አለ
አንደኛው ሰብሳቢ። እትዬ የሻሽወርቅ አጠገቤ
ስለተቀመጡ ግራ ቀኙ፤ ፊት ለፊት የተቀመጠው
ሳይቀር እየዞረ ወደ እኛ ያያል፤ ይጨንቃል።
ግን ሁሉም ፊት ላይ አሁንም መሳቅ መፈለጋቸው
ቁልጭ ብሎ ይታያል። ለመሳቅም የእትዬ የሻሽወርቅን
ምላሽ ጓግተው የሚጠብቁ መሰሉኝ።
«እንግዲህ
አንዴ ጣልቃ ገብቻለሁና ልቀጥላ...ይቅር
ይበሉኝ መጻፍያ ስላልያዝኩ ሃሳብዎ ላይ ጥያቄ
ባገኝ ጊዜ በኋላ እንዳልረሳው ሰግቼ ነው»
አሉ። ነገሩ ምንም
የሚያስቅ ባይሆንም የተወሰኑ ሰዎች ያቋረጡትን
ሳቅ ቀጠሉ፤ አራገፉት። «ቅድም
ጥያቄ ስንቀበል መጠየቅ ነበረብዎ!
አሁን ወዳነሳነው
ሀሳብ ልመለስና እንቀጥል...» ሌላው
ሰብሳቢ ሊቀጥል ሲጀምር...አቋረጡት።
«ቆይ
ቆይ! ልጠይቅ
አትጠይቂ ብለን ሙግት ከምንገባ ነገሬን ለምን
አይሰሙኝም? ባይሆን
ከዚህ በኋላ ምንም ሌላ ንግግር ሳያስፈልግዎ
እገላግልዎ ይሆናልኮ!» አሁንም
ሰው ሳቀ። የሰው ለሳቅ ያለው ፍጥነትና ለመሳቅ
ያለው ጉጉት አሳቀኝ እንጂ የለመድኳቸው ሻሼ
እንኳ አልተሰሙኝም። እንደውም ስብሰባው
አልቆ ወደሰፈር እስክመለስ ቸኩያለሁ፤ መላኩን
ካየሁት ቆየሁ።
«ስሙኝ!
መቼም ፈጣሪ ለአገሬ
ደግ የሆነ መሪ ሰጥቷታል፤ መድኃኒዓለም ክብር
ምስጋና ይግባው...ቅዱስ
ገብርኤልን ነው የምላችሁ ደስ ብሎኛል። እርሱን
ይጠብቅልን እንጂ ሁላችን ነው በእርሱ ደስ
ያለን። ታድያ ግን እናንተን የሾመ...የሰየመ
እርሱ ነውና ፍፁም ነን ብላችሁ ባታስቡ መልካም
ነው» ሰው
አሁንም ይስቃል፤ ገሚሱ ደግሞ ያጨበጭባል።
የወረዳችን
አስተዳደሮች ከተሾሙ ወራት አልፈዋል፤ ሰፈራችን
ግን ከችግር አልተላቀቀም። በእርግጥ የእኛ
አካባቢ ነዋሪም ለውጥ በአንድ ጀንበር የሚናፍቀው
ስለሆነ ቀስ ብሎ ሥራን ለማሠራት ትዕግስት
የለውም። ቢሆንም ደግሞ አዳዲሶቹ ተሿሚዎች
ተስፋን እንዳስያዙን በቀደመው አካሄድ
እየወሰዱን መሆኑ በግልጽ ይታያል። ለምሣሌ
ሃሳብ ይቀበላሉ እንጂ ሃሳቡን ለመመርመር
አይደለም የሚሰሙት፤ ለማጣጣል ነው። ትክክል
እንደሆኑና ከሁሉም የወረዳው ነዋሪ የተሻሉ
ስለመሆናቸው እርግጠኛ ናቸው፤ ንግግራቸው
ያስታውቃል።
አይይ!
መቼም እኛ ማማረሪያ
ነገር አናጣ! ሁሌም
የጎደለ ነገር አይጠፋብንም። ግን ደግሞ
የጎደለውን በትኩሱ እንዲስተካከል ሃሳብ
ማቅረብ ክፋት አይደለም።
«እውነቴን
ነው! መሪው
ልበ ቀና እና አዋቂ በመሆኑ...በመወደዱ
ሁላችን እንጠቀማለን። እናንተም ለማገልገል
ተጠቀሙበት እንጂ የተሻላችሁ ተብላችሁ
እንደመጣችሁ እያሰባችሁ አትታበዩብን። የእኛ
ወረዳ በሙስና የተጨማለቀ ነው፣ የእኛ ወረዳ
ቤት ያለውም ሆነ የሌለው ኪራይ ይሰበስባል፣
እኛ ወረዳ ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ የሚሠሩ አሉ፣
የእኛ ወረዳ ሕዝብ የሚሉትን አይሰማም፣ የእኛ
ወረዳ ሰው ብዙ ጊዜ በረብሻ የሚታሰሩ ወጣቶዎች
አሉበት...
«እንዲህ
ያለውንና ሌላ ሌላውን ሃሳብ ሰምታችሁ መጥታችሁ
ችግራችንን ሁሉ ያወቃችሁልን እየመሰላችሁ
ነው። የቸገረንን እኛ እንናገር እናንተ ደግሞ
ስሙንና እንዴት እንሥራ ለሚለው መንገድ
አሳዩን። ጥድ መትከልና
ጥላ መዘርጋት፤ አካባቢን ማሳመር ጥሩ ነው...ግን
ውጭውን አሳምረው ውስጡን ንቀው ካዩት ምን
ዋጋ አለው?
«የሾማችሁም
ቢሆን ውጭውን አይቶ የሚፈርድ አይደለ፤
ብንነግረው ይገባዋልና ብታስቸግሩም በእርግጥ
ግድ የለም! እና
ምን ልላችሁ ነው...ነገራችሁ
ጥሩ ሆኖ ሳለ...አያያዛችሁ
ግን እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኖ
እንዳንከፋባችሁ...እናውቃለን
አትበሉን...እኛ
ያውቃሉ እንድንላችሁ ሥሩና
አሳዩን...ማን
ነው ይሄ? ባለፈው
እዚህ በምን ነበር ተሹሞ የነበረው...»
ተመቻቸው
መሰለኝ፤ እትዬ የሻሽ፤ ንግግራቸውን ሊቀጥሉት
ነበር፤ ጭብጨባው አስቆማቸው።
«ገብቶናል...እኛ
እንደዛ አላልንም፤ አብረን ለወረዳችን እንሥራ።
ለውጡን መደገፍ የምንችለው መግባባት ስንችል
ነው» አንዱ
ተናገረ። «እሱማ
ጥሩ ነው...እንደግፋለን
እያላችሁ እየገደፋችሁ እንዳይሆን እንጂ...እየው
ብቻ በእናንተ ችግር የሿሚው ስም በክፉ ይነሳና!»
አሁንም
ሰው ሳቀ፤ እትዬ የሻሽወርቅ ልክ ልብ አንጠልጣይ
ፊልም ላይ ደራሲው ይሁን ብሎ እንደሚያካትተው
ማረፊያ ገጸ ባህሪ፤ ለተጨነቀ ስብሰባ መተንፈሻ
ናቸው። እርሳቸው ባይኖሩ ስብሰባው አይማርክም
ነበር።
በዚህኛው
ንግግራቸው ሰብሳቢው ሳይቀር ስቋል። «እኛ
እዚህ የመጣነው ልናገለግላችሁ
ነው። ይመኑን እናታችን...ለወረዳው
አዲስ ነገር እናመጣለን። ይህን የምናደርገው
ግን ከእናንተ ጋር አብረን በመሆን ነው።
ካለተጋገዝን አይሆንም!» አለ።
እትዬ የሻሽ ንግግሩ ለምን እንዳልተዋጠላቸው
አላውቅም፤ ወደቤት ስንመለስ ሳልጠይቃቸው
አልቀርም።
«ይሁን!
ለውጡን እንደግፋለን
እያላችሁ፤ ያገኘነውን ተስፋ እንዳታስገድፉን
ሰግቼ ነው። ይሁን! አሁን
ስብሰባውን መቀጠል ትችላላችሁ»
ተሰብሳቢው ሰው
ሳቅና ጭብጨባን ቀላቅሎ አሰማ። የልባቸውን
የተናገሩት እትዬ የሻሽ ዞር ብለው በፈገግታ
አዩኝ፤ አጸፋውን መለስኩ። በገፃቸውና
በዓይናቸው ውስጥ ያለውን ለወረዳቸው ያላቸውን
ተቆርቋሪነት፣ የእኔነት መንፈስና ድፍረት
ሳይ ቀናሁ። አዎን! በተለይ
መሥሪያ ቤቴ ትዝ አለኝ፤ እንዲህ ብዬ እኔም
መናገር ብችል! ተመኘሁ።
ሠላም!
No comments:
Post a Comment