Translate/ተርጉም

Wednesday, November 7, 2018

ኪነጥበብ ዜና


ኪነጥበብ ዜና
ሰምና ወርቅ የኪነጥበብ ምሽት ሐሙስ ይካሄዳል
በየወሩ የመጨረሻው ሐሙስ ቀን የሚካሄደው ሰምና ወርቅ የኪነጥበብ ምሽት አስራ አንደኛው ዝግጅት በያዝነው ወር ማብቂያ ጥቅምት 29 ቀን 2011. ይካሄዳል።
ማምሻውን 1130 ጀምሮ በቫምዳስ የመዝናኛ ማዕከል በሚካሄደው በዚህ ምሽት፤ ዶክተር ምህረት ደበበ፣ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፣ መምህር የሻው ተሰማ /የኮተቤው/ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አዜብ ወርቁ፣ ሶሎሞን ቦጋለ እንዲሁም ደራሲት ሕይወተ እምሻውና መምህርት እጸገነት ከበደ ይገኛሉ ተብሏል። ገጣምያን ሙሉዓለም ተገኘወርቅ/ዶክተር/ እና በክሪ አሕመዲንም ከመሶብ የባህል ቡድን ጋር ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። ለመግቢያ 50ብር ያስፈልጋል።

«ማምሻ» ስምንተኛው ምሽት ከነገ በስቲያ ይከወናል
«ማምሻ» የመድረክ ትርኢት ስምንተኛ ምሽቱ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2011. «የከበሮ ማታ» በሚል ርዕስ ተዘጋጅቷል።
በወሩ ዝግጅት የከበሮ ጥንተ ነገር፣ ከበሮ እንደ ሕይወት እና የሀገረሰብ ጨዋታ በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ማለትም በግጥም፣ በተውኔት፣ በሙዚቃ፣ በንግግርና በእንቅስቃሴ ይቀርብበታል። የዚህ ወር «ማምሻ» እንደወትሮው ምሽት 11:30 በላፍቶ ሞል ይካሄዳል፤ መግቢያውም አንድ መቶ ብር ነው ተብሏል። ዝግጅቱ ወር በገባ የመጨረሻው ማክሰኞ እንደሚካሄድ ይታወቃል።

«ኢትዮጵያ በምናቦች አጽናፍ» በሚል ርዕስ የፊታችን ሐሙስ ገለጻ አለ
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በየወሩ የሚያዘጋጀው የመጻሕፍት ላይ ገለጻና ውይይት መርሃ ግብር ቀጥሎ፤ የፊታችን ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2011. «ኢትዮጵያ በምናቦች አጽናፍ» በሚል ርዕስ ገለጻ ይደረጋል ተብሏል።
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ (5 ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም ግቢ) ማምሻውን 1100 ጀምሮ በሚኖረው በዚህ ዝግጅት ላይ ገለጻ የሚያደርጉት ደግሞ የቤተመዛግብተና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ናቸው።

«የፊልም አዘገጃጀት» መጽሐፍ የዛሬ ሳምንት ያወያያል
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብና ውይይት ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የዛሬ ሳምንት እሁድ ህዳር 2 ቀን 2011. ከቀኑ 800 ሰዓት ጀምሮ በሰለሞን በቀለ ወያ በተጻፈ «የፊልም አዘገጃጀት» መጽሐፍ ላይ ውይይት ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ (ወመዘክር) በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የመነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ጳውሎስ አእምሮ መሆናቸውን ከሚዩዚክ ሜይዴይ ስንታየሁ በቀለ መረጃውን አድርሶናል።

«ኪነጥበብ ለሕዝቦች አንድነት እና ሰላም» የኪነጥበብ ምሽት ትናንት ተካሄደ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትናንት ጥቅምት 24 ቀን 2011. «ኪነጥበብ ለሕዝቦች አንድነት እና ሰላም» በሚል መሪ ሃሳብ የኪነጥበብ ምሽት አካሂዷል።
ላምበረት አዲሱ መናኽሪያ በሚገኘው «ማነራ ሸዋ» ሆቴል የተዘጋጀው ይህ የኪነጥበብ ድግስ፤ የኪነጥበብ ዘርፉን ለማሳደግና ኪነጥበብ ለሰላም፣ ለእድገት እና ለብልጽግና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማሰብ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። በዚህ ዝግጅት፤ ከሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ጀማሪ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል። በመድረክ ላይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል በልጠው የተገኙትም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።